ኢትዮጵያን ባለ ድል ያደረገው የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ
በደቂቃዎች ገለጻ እውነቱን በማሳወቅ የግብጽ ሴራን አክሽፏል
ከዚህ በኋላ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት በኩል ብቻ ይካሔዳል
ኢዛ (ዓርብ ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 9, 2021)፦ ከኢትየጵያ ወቅታዊ አጀንዳዎች መካከል አንዱ የኾነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በግብጽና በተባባሪዎቿ የጸጥታው ምክር ቤት ዘንድ ቢቀርብም፤ ከሳሾችዋ እንዳሰቡት ሳይኾን ኢትዮጵያ ድል ያደረገችበት ኾኗል።
ግብጽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፊት አውራሪነት ኒው ዮርክ ከትመው የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በጸጥታው ምክር ቤት እንዲታይና በስድስት ወር ውስጥ ኢትዮጵያን አጣሪና ቀፍዳጅ የኾነ ውል ይፈረም ዘንድ ሲያደርጉ የነበረው ሎቢ ከሽፎ፤ አንድ ራሳቸውን ይዘው የሔዱት የኢትዮጵያ ውኃና ኢነርጂ መስኖ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ ፍርዱን እንግዲህ ብለው በአጭር ደቂቃ የቀረበ ንግግራቸው ኢትዮጵያን ባለ ድል የሚያደርግ ውሳኔ ሊተላለፍ ችሏል።
ወትሮም ቢኾን ለጸጥታው ምክር ቤት መቅረብ ያልነበረበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በግብጽ እና በሱዳን ገፋፊነት፣ በዐረብ ሊግ አገሮች ተባባሪነት፣ በዘመቻ የተደረገው ኢትዮጵያን የማንበርከክ ተግባር እነርሱው በመረጡት መድረክ ላይ ታይቶ ውድቅ ተደርጐባቸው፤ ከዚህ በኋላ በግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር እዚያው በአፍሪካ ውስጥ አንድነት ድርጅት እንደተጀመረ ይቀጥል የሚል ውሳኔ ተወስኗል። ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ጉዳዩን ለመመልከት የተቀመጠው የጸጥታው ምክር ቤት አባላት፤ የግብጽን ጥያቄ ይዞ ከኢትዮጵያ ወገን ያለውን ከሰማ በኋላ ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እንደተጀመረ እዚያው ይለቅ የሚለውን ውሳኔ ከማሳረፉ በፊትም፤ በቦታው የነበሩ የአገራት ተወካዮችም የሰጡት ብይን የኢትዮጵያን እውነት ያረጋገጠ ኾኖ ተገኝቷል።
በዚህ ስብሰባ በአሜሪካና እንግሊዝ ሳይቀር ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ድርድራቸውን በአፍሪካ ሕብረት በኩል ያድርጉ በማለት የሰጡት ሐሳብ ለግብጻውያን የሚጐረብጥ ቢኾንም፤ የትናንቱ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ኢትዮጵያን ባለ ድል አድርጓል።
በተለይ የዶክተር ኢንጂንየር ስለሺ ንግግር ደግሞ የምክር ቤቱን አባላት ወደ የትም የማያላውስ ነበር።
“ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው የውኃ እንጂ የኒውክለር ማብለያ አይደለም።” በማለት ጉዳዩ እዚህ ምክር ቤት መምጣቱ በራሱ አግባብ እንዳልነበር ተናግረዋል።
ይህንኑ አባባላቸውን ለማጠናከር በዚህ ምክር ቤት ተገኝቶ ያስረዳ የመጀመሪያው የውኃ ሚኒስትር መኾናቸውን ጭምር የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለምክር ቤቱ አንድ ጥያቄ አቀረቡ። ኢትዮጵያውያን የዓባይ ውኃ መጠጣት ይችላሉ? የሚል ነበር።
ግብጽና ሱዳን የምንገነባውን ግድብ ባለመቀበላቸው በዕለቱ መድረክ ላይ እንድንመጣ ኾኗል ያሉት ዶክተር ኢንጂንየር ስለሺ፤ የሦስቱ አገራት ልዩነት የመጣው የቀኝ ግዛትና የመጠቅለል ፍላጎት ያላቸው መኾኑንም ልታውቁ ይገባልና አፍሪካውያን ችግሩን ለመፍታት አቅሙም ጥበቡም አላቸውና ድርድር በተጀመረበት መንገድ ይቀጥል ብለው አስገንዝበዋል።
ይህ ብቻ አይደለም የሁለተኛውን የውኃ ሙሌት ሲጀመር አስፈላጊውን ሞዳሊቱ እና መረጃ አሳውቀናል። አሁን ኢትዮጵያ ውኃውን እየሞላች ያለችው ሦስቱ አገራት እ.ኤ.አ. ማርች 2015 ላይ በተስማሙትና በፈረሙት ስምምነት ነው ብለውም ኢትዮጵያ እየሠራች ያለችው በአግባቡና በአገራቱ በተደረገ ስምምነት እንደኾነ አሳውቀዋል።
የሚኒስትሩ ንግግር እውነቱን በትክክል ከማስቀመጡም በላይ በዐረብ አገሮች ተጽእኖ በተለይም ከሳዑዲ ዐረብያ እንዲወጡ የተደረጉ ኢትዮጵያውያንንም ጉዳይ ጠቆም ያደረጉበት መንገድም ነበር። ይኸው ንግግራቸው ከግብጽ ያበሩ የዐረብ አገሮችንም የነካ ነበር። ይህንንም “ግድቡ ሰሞኑን በባዶ እግራቸው ከዐረብ አገሮች የሚያባርሯቸውን ዜጐቻችን ነፃ የሚያወጣ ነው” በማለት ገልጸውታል።
በአጭሩ ግን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይን ለመመልከት የጸጥታው ምክር ቤት የማየት ሥልጣን የለውም የሚለውን ቁርጥ ያለ የኢትዮጵያን አቋም በተገቢው መንገድ አስረድተው፤ በመጨረሻ የተሰጠው ውሳኔ፤ አዎ ትክክል ነው ወደሚል መሔዱ ግብጻውያንን ፀጉር ሲያስነጭ፤ ኢትዮጵያውያን ከትናንት እኩለ ለሊት ጀምሮ የተገኘውን ድል በተለያዩ መንገዶች እንዲገልጹ እያደረጋቸው ነው።
ይህንን ድል የበለጠ የሚያደርገው በምክር ቤቱ የተገኙት የተለያዩ አገራት ተወካዮች የሰጡት አስተያየት ግብጽን ብቻዋን ያስቀረ መኾኑን ነው።
የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበሩ “የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት መፍትሔ ይሰጥበታል” ማለቱና “የጸጥታው ምክር ቤት አስፈላጊ ከኾነ የአፍሪካ ሕብረትን ሊደግፍ ይችላል” ማለታቸው አንዱ ነው።
የሩሲያ፣ ኬንያ እና ሌሎች አገራት ተወካዮችም የኢትዮጵያን እውነታ ያዘለ ሐሳብ ተቀብለው፤ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተመልሶ ይታይ ብለዋል። እንግሊዝና አሜሪካ በአፍሪካ ሕብረት በኩል ለሚደረገው ድርድር ድጋፍ እንደሚሰጡ አመልክተዋል።
ከዚህ ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴም ለምክር ቤቱ የሰጡት ምላሽ ትናንት ለተገኘው ድል አስተዋጽኦ ነበረው።
ግብጽ ከዚህ በኋላ ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዳታመጣ የሚያደርግ ጭምር ነው የተባለው የትናንቱ ውሳኔ፤ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ራስዋንም ለምን ዓባይን እንደምትገድብ ዓለም እንዲያውቅላት ያደረገ ነው። ለዓመታት ኢትዮጵያ በዚህ ግድብ ዙሪያ ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሁሉ የበለጠ በደቂቃዎች ለዓለም እውነታውን እንዲያውቅ ያደረገ ኾኗል። (ኢዛ)