Ethiopian Election 2021 result

የምርጫ 2013 ውጤት

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 410 ወንበሮችን አሸንፏል
ኢዜማ አራት፣ አብን አምስት፣ ጌሕዴፓ ሁለት ወንበሮች አግኝተዋል

ኢዛ (ቅዳሜ ሐምሌ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 10, 2021)፦ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ የኾነ የምርጫ ውጤቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ብልጽግና ፕርቲ አሸናፊ መኾኑን አረጋግጧል። ብልጽግና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 410 ወንበሮች አግኝቷል።

አሁን በተገለጸው ውጤት መሠረት በአዲስ አበባ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ23ቱ የምርጫ ክልሎች ብልጽግና 22ቱን ማሸነፍ ችሏል። አንድ የምርጫ ክልል ደግሞ አንድ የግል ተወዳዳሪ (የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢያ አሕመድ ልዩ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት) አሸናፊ መኾን መቻላቸው ታውቋል። በዚህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ አሸናፊ መኾን አልቻለም።

ብልጽግና በአፋር ክልል ስድስት፣ በአማራ ክልል 114፣ በቤንሻንጉል ሦስት፣ በድሬዳዋ አንድ፣ በጋምቤላ ሦስት፣ በኦሮሚያ 167፣ በሲዳማ 19 እና በደቡብ 75 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን አሸንፏል። ይህም እስካሁን የምርጫ ውጤታቸው ከተገለጹት 436 ወንበሮች ውስት ብልጽግና 410 ያህሉን ማሸነፍ መቻሉ ነው።

በዛሬው የቦርዱ ውጤት መሠረት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በደቡብ ክልል ኢዜማ አራት እጩዎቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸናፊ የኾኑበትን ወንበር ያገኘ ሲሆን፤ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሁለት ወንበር ማግኘት ችሏል።

በአማራ ክልል ደግሞ አብን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት ወንበሮች አግኝቷል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ሌላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ያገኙ አራት የግል ተወዳዳሪዎች አሸናፊ የኾኑ ሲሆን፤ ይህም ከአዲስ አበባ አንድ፣ ከኦሮሚያ ሦስት የግል ተወዳዳሪዎች አሸናፊ ኾነዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ