Teddy Afro Concert 2020

“ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” ኮንሰርት ላይ ቴዲ አፍሮ ታዳሚዎቹን ሲያስደስት፣ ቅዳሜ የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ

መቶ ሃምሳ ሺሕ ታዳሚዎች የተገኙበት

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 24, 2020)፦ ባሳለፍነው ሳምንት ማለቂያ ላይ ቅዳሜ የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ ደምቃ ያመሸችበት ነበር። በመቶ ሃምሳ ሺሕ የሚቆጠሩ ታዳሚዎችን በአንድ ቦታ በማሰባሰብ የደመቀ የሙዚቃ ድግስ ያጣጣሙበትን ምሽት አሳልፈዋል። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የገነነ ስም ያለው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በመስቀል አደባባይ በተሰናዳው በልዩ ሁኔታ በታነፀው መድረክ ላይ፤ በቦታው የነበሩ የሙዚቃ አድናቂዎቹን አጀብ ባሰኘ የመድረክ አያያዝ ጭምር አስደስቷል።

በአጭር ጊዜ ዝገጅት በመስቀል አደባባይ “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” በሚል መሪ ርዕስ የተሰናዳው የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ድግስ፤ በዕለቱ ታዳሚዎችን ከማስደሰት ባሻገር በልዩ ሁኔታ በተለያዩ ምልከታዎች አስተዋጽኦው የበረከተ ነበር።

ለሙዚቃው ኢንዱስትሪና በአጠቃላይ ከዘርፉ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፤ እንዲህም መሥራት እንደሚቻል ያሳየ ነው። ከመድረክ ዝግጅቱ ጀምሮ መድረኩን ገጽታ ለማጉላትና ዝግጅቱን ዓይነ ግቡ ለማድረግ የመብራትና የመድረክ የማስጌጥ ሥራዎቹ ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲሠራ መደረጉ፤ ለተመሳሳይ ዝግጅቶች በአስተማሪነቱ የሚጠቀስ ነው። ይህም አድናቂዎችንና ጥበብን በማክበር መከበር የሚቻለበትን ያሳየበት ጥሩ አጋጣሚ ኾኗል።

ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ አንፃር የተደበተን አእምሮ በማፍታታት፤ መነቃቃት የፈጠረ ምርጥ ዝግጅት ስለመኾኑ ማሳያ ሲሆን፤ “ፍቅር አሸነፈ” የሚል አስተያየት የተሠጠበት መድረክ መኾኑንም አሳይቷል።

ሕዝብን ሊመጥን የሚችል ዝግጅት ካለ በየትኛውም ወቅት ትልልቅ የመድረክ ሥራዎችን ለመታደም የማይፈልግ ሕዝብ አለመኖሩን የቅዳሜው የቴዲ አፍሮ መሰናዶ በተለየ ልንመለከትበት ያስቻለ ነው።

የሙዚቃ ድግሱ በሰላም ከተጠናቀቀ በኋላ በኪነጥበብ ባለሙያዎችና ከሌሎች ከተሠጡ አስተያየቶች መረዳት እንደተቻለውም፤ ቴዲ አፍሮ ብቃቱን ያሳየበት ሥራ መሥራቱን በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ስሙን ጠብቆ እንዲጓዝና ወደፊትም በዘርፉ ብዙ ሊሠራ የሚችሉ ተግባራትን እንደሚፈጽም ያስመሰከረበት እንደኾነ ገልጸዋል።

ከ“ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” ኮንሰርት ታዳሚዎች አንዱ
ከ“ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” ኮንሰርት ታዳሚዎች አንዱ፣ ቅዳሜ የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ

ከሁሉም በላይ በአንድ አቀንቃኝ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በመቶ ሃምሳ ሺሕዎች የሚገመት ታዳሚ የተገኙበት ብቸኛው መድረክ በመኾን የሚመዘገብ እንደኾነ ብዙዎች እየገለጹ ሲሆን፣ እንደ ሪከርድ የሚያዝ ተግባር ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች እምነታቸውን ማንፀባረቃቸው የቅዳሜ ምሽቱን መሰናዶ በተለየ እንዲታይ አድርጓል።

የቴዎድሮስ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሌላው መገለጫ ተደርጐ ሊወሰድ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ በዚህ ኮንሰርት ዝግጅት በኮንሰርቱ ቀን ሊካሔድ የነበረ የእግር ኳስ ጨዋታና በማግሥቱ በመስቀል አደባባይ የሚካሔድ የሩጫ ፕሮግራም እንዲሰረዝ ተደርጓል። የጸጥታ ኃይሉ ጥበቃና የታዳሚውም መልካምነት ታክሎ ያለችግር መጠናቀቁ በመተባበር ሲሠራ ውጤታማ መኾን የሚቻል መኾኑን ነው። ከነበረው ሕዝብ አንፃር ይህ ትልቅ ስኬት መኾኑን ያሳየ ነው።

የቅዳሜውን ኮንሰርት በይበልጥ መነጋገሪያና በበጐ ጐኑ ሊታሰብ የሚችልበት ሌላው ገጽታ፤ ቴዎድሮስ ካሳሁን በአገር ውስጥ ኮንሰርቶችን ለማዘጋጀት ይገጥመው የነበረው ፈተና ቀርቶ ዛሬ በአደባባይ ያሻውን ዘፈን በፈለገው ሁኔታ መጫወቱ ለአርቲስቱ መልካም አጋጣሚ ነው። ከዚህ ቀደም ኮንሰርት ለማዘጋጀት የቦታ መረጣ ላይ ብቻ ሳይሆን “ይህንን ወይም እነዚህን ዘፈኖች አትዘፍንም” የሚለውን ጥምዝ ጥያቄዎች በቀረቡ ቁጥር ይህንን ጥያቄ ላለመቀበል ብዙ ኮንሰርቶችን እንዳያዘጋጅ ምክንያት ከመኾኑ አንፃር፤ ቅዳሜ ዝግጅቱ ላይ ያሻውን አድርጓል። ጃ ያስተሰርያልና ግርማዊነታቸው ከዚህ ሠረገላ ብሎ ዘፍኗል። እንዲህ ያሉ በነፃነት የሚሠሩ ሥራዎች ነገም መለመድ ያለባቸው፣ ክልከላዎች ሆድ ከማሻከርና ቅሬታ ከመፍጠር በቀር የሚፈይዱት ነገር ያለመኖሩን ያሳየ ስለመኾኑ አመላካች ኾኗል።

እንደ አገር ቱሪዝምን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መገኛ ለማድረግ ከተያዘው እቅድ አንፃር እንዲህ ያሉ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፤ የቱሪዝም ዘርፉ አንድ አካል ኾነው እንዲታዩ የጠቆመም ኾኗል። የአርቲስቱ አድናቂዎች እንዳሉት “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” ኮንሰርት በፍቅር አሸናፊነት ተጠናቋል። መታከል አለበት ያውም ብዙ ነገር አስተምሮ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ