ኢሕአዴግ አንድ ሲኾን ወይም ሲበተን፤ ኢትዮጵያ ትሞታለች የሚለው ሐሳብ ከድንቁርና የሚመነጭ ነው
በዛሬው ዕለት የተሰበሰበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የፓርቲ እሳቤ ሳይኖር ኢትዮጵያ ነበረች
ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 22, 2019)፦ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኢሕአዴግ ውሕደት ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ኢሕአዴግ አንድ ሲኾን ወይም ሲበተን፤ ኢትዮጵያ ትሞታለች የሚለው ሐሳብ ከድንቁርና የሚመነጭ ነው” በማለት ምላሽ ሠጥተዋል።
ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ አባት እንጂ፤ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም። እኛ ከሌለን አገር የለም፣ እኛ ከሌለን መንግሥት የለም የሚባል ነገር ስሕተት ነው። የፓርቲ እሳቤ ሳይኖር ኢትዮጵያ ነበረች። ፓርቲኮ 40 ዓመቱ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ። ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
የኢሕአዴግ ውሕደት ጉዳይ ላለፉት 10 ዓመታት ሲነገር የነበረ መኾኑንም አስታውሰዋል። ውሕደቱ አያስፈልግም የሚል ሐሳብ እስከዛሬ ያለመስማታቸውን ያመላከቱት ዶ/ር ዐቢይ፤ የውሕደቱ ጉዳይ ጥናቱ ከታየ በኋላ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የሚያጸድቀው ይኾናል ብለዋል።
አክለውም ኢሕአዴግ ከሌላ አገርና መንግሥት የለም የሚለውን አመለካከት ስሕተት መኾኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።
“እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ የለችም” የሚለውም ትክክል ያለመኾኑን ገልጸዋል። ፓርቲው 40 ዓመቱ መኾኑንም ያስታወሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢሕአዴግ ቢኖርም፤ ባይኖርም ኢትዮጵያ ትቀጥላለች የሚል መልስ ሰጥተዋል። (ኢዛ)



