ወ/ሮ ሕይወት ሞሲሳ እና ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሃምዛ

ወ/ሮ ሕይወት ሞሲሳ እና ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሃምዛ

ሜቴክን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ወይዘሮ ሕይወት ሞሲሳ ተሾሙ

ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 12, 2020)፦ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ ሕይወት ሞሲሳ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር በመኾን እንዲያገለግሉ ተሾሙ።

ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሁለት ሹመቶችን የሠጡ ሲሆን፤ ወ/ሮ ሕይወት ሞሲሳን ከትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታነታቸው ወደ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን በዋና ዳይሬክተርነት ተመድበው እንዲሠሩ ሹመዋቸዋል።

ከወይዘሮ ሕይወት ሞሲሳ ሌላ ዛሬ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ሹመት የተሠጣቸው እስካሁን የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ለነበሩት ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሃምዛ ነው።

ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ዛሬ የተሠጣቸው ሹመት፤ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ኾነው እንዲሠሩ ነው።

ወ/ሮ ሕይወት ከዚህ ቀደም “የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ” ዋና ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽንና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እንደሠሩ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ፤ ሜቴክ ተብሎ ይጠራ የነበረውን የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለሁለት በመክፈል አንዱን የንግድ ሁለተኛውን ደግሞ በመከላከያ ስር እንዲኾን ማድረጋቸው ይታወቃል። የንግድ ኾኖ እንዲቀጥል የተደረገው “የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን” ተብሎ ሲጠራ፤ በመከላከያ ስር የኾነው ደግሞ “የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን” መባሉ አይዘነጋም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው 78ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም። በዕለቱ ምክር ቤቱ የመከላከያ ኢንጂነየሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ነበር። በአገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የተጀመረው የሪፎርም ሥራዎች አንድ አካል የኾነውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 መሠረት ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችን ቀደም ሲል ከነበሩበት ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እንዲዛወሩ ተወስኗል።

በዚሁ መሠረት የደጀን አቪየሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የጋፋት አርማመንት ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የሆሚቾ አሚውኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና የፊውል/ነዳጅ እና ፕሮፒላንት ንዑስ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በአንድ ኮርፖሬሽን ስር በማደራጀት ብቁና ተወዳዳሪ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች መገንባት ይቻል ዘንድ፤ የመከላከያ ሚኒስቴር “የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን” ማቁቋሚያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል። ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቆ ነበር። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ