ኤጀንሲው የፓስፖርት አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ ማቆሙን አስታወቀ
የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ
ለአዲስ ፓስፖርት ፈላጊዎችም ኾነ የማደስ አገልግሎት ቆሟል
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 25, 2020)፦ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ፓስፖርት የመሥጠትና የማደስ አገልግሎቱን ማቋረጡን አስታውቋል።
ኤጀንሲው አገልግሎቱን ያቋረጠው ላልተወሰነ ጊዜ ሲሆን፣ የኢ-ቪዛና ተደራሽ ኦንላይን ቪዛ አገልግሎትን ከትናንት መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተቋረጠ መኾኑን አክሎ ገልጿል።
ነገር ግን ቁልፍ ለኾኑ የመንግሥት ሥራዎችና ለሕመም ብቻ አስቸኳይ ፓስፖርት እንደሚሠጥ ተገልጿል።
ይህ የአስቸኳይ ፓስፖርት ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳይበር በተከለከለባቸው 30 አገራት ተግባራዊ አይኾንም ተብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኤጀንሲው ያሳለፈው ውሳኔ የመኖሪያ ፈቃድና የትውልደ ኢትዮጵያውያን የመታወቂያ አገልግሎት በጊዜያዊነት መቋረጡን ያመለክታል።
ከዛሬ ጀምሮ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው ወደሥራ ገበታ እንዳይገቡና የተወሰኑ ሠራተኞች ብቻ እንዲገቡ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን፤ ይህ ውሳኔ ግን እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኤሌትሪክ ኃይልን አይመለከተም ተብሏል። (ኢዛ)



