የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

ክልሎች ድንበራቸውን መዝጋት ብቸኛ መፍትሔ አይደለም

ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 31, 2020)፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የክልል መንግሥታት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በክልሎች መካከል ያለውን ድንበር መዝጋት ሳይሆን በመግቢያ ድንበሮች ምርመራ ማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ዛሬ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክረ ሐሳብ ደረጃ ይፋ ባደረገው መልእክቱ አስታውቋል።

ከዚህም ሌላ የፌዴራል መንግሥቱ ባሳለፈው ውሳኔና በሠጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት የተወሰኑ እስረኞችን መልቀቅ ያልተከናወነባቸው ክልሎች በአስቸኳይ በሥራ ላይ ሊያውሉት እንደሚገባም አሳስቧል።

ኮሚሽኑ ስለኮሮና ቫይረስ መከላከልና ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ይፋ ያደረገው ሙሉ ምክረ ሐሳብ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ስለ ኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) መከላከል እና ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተሠጠ ምክረ ሐሳብ

አዲስ አበባ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም.

ስለ ኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) የመከላከል እርምጃዎች እና ተያያዥ ስለሆነው መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ኮሚሽኑ በቅርበት ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

በተለይም ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፣ እስረኞችን፣ የተፈናቀሉ ሰዎችን፣ የመረጃ መረብ መቋረጥና ሥርጭትን የመሰሉ ጉዳዮችን ከየሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲያደርግ የነበረውን ምክክርና ክትትል የሚቀጥል ሲሆን፤ እስከ አሁን መንግሥት ለጉዳዩ በሠጠው ትኩረትና እየተወሰዱ ባሉት ተከታታይ እርምጃዎችም ለታየው ቀና ምላሽ ኮሚሽኑ እውቅና ይሠጣል።

ይህን የመሰለ መጠነ ሰፊ እና ዓለም ዓቀፋዊ የሆነ የወረርሽኝ ሥጋት መደበኛ ያልኾኑ እርምጃዎች (Extra-ordinary Measures) ለመውሰድ እንደሚያስገድድ ቢታወቅም፤ ሁሉም ዐይነት እርምጃዎች በሕጋዊና ሰብአዊ መብቶች መርሆዎች የተመሩ ኾነው እንዲቀጥሉ ኮሚሽኑ የሚከተሉትን የሰብአዊ መብት፣ የሰብአዊነት እና የኃላፊነት ስሜት መርሆዎች ለመንግሥታዊ አካላት እንዲሁም ለሁሉም ሕብረተሰብ ክፍሎች ያሳስባል።

• የወረርሽኝ በሽታውን የመከላከል ሥራ የመጨረሻ ግቡ የሰዎችን በጤንነትና በሕይወት የመኖር ሰብአዊ መብት ማክበር እና ማስከበር ነው።

• መሠረታዊ የሆነ የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ለማክበር እና ለማስከበር የሚደረግ ማናቸውም እርምጃም፤ በሰብአዊ መብቶች መከበር ላይ የተመሰረተ እና በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ የሚከናወን መሆን ይገባዋል።

• የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ሲባል ለምርመራ በተለየ ማቆያ ስፍራ የሚገኙ ሰዎች አያያዝ ሰብአዊ መብቶችንና ሰብአዊ ክብርን በሚጠብቅ መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እንዲሁም ከበሽታው አገግመው የሚወጡ ሰዎችም ለመገለልና የአድሎ ጥቃት እንዳይጋለጡ አስፈላጊውን ትምህርት መስጠትና ጥበቃ ማድረግ ይገባል።

• መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የመናገር ነፃነትን ባከበረ መልኩ የተሳሳቱ መረጃዎችን መመከት፣ የበሽታው ተጠቂዎችን ወይም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመገለልና መድልዎ እንዲሁም ለጥቃት የሚያጋልጡ ንግግሮችና ወይም ድርጊቶችን መከላከል ይገባል።

• የክልል መንግሥታት የወረርሽኝ በሽታው ሥርጭት ለመከላከል የሚወስዱት እርምጃዎች በክልሎች መካከል ያለውን ድንበር መዝጋት ሳይሆን በመግቢያ ድንበሮች ላይ የተፈቀደውን የጤንነት ምርመራ ማድረግ እና ልዩ ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በሰብአዊ ክብር ወደ ለይቶ ማቆያ የክትትል ጣቢያ መውሰድ ይሆናል።

• የፌዴራሉ መንግሥት በአሳለፈው ውሳኔ እና በሠጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት የተወሰኑ እስረኞችን መልቀቅ ያልተከናወነባቸው ክልሎች በአስቸኳይ በሥራ ላይ ሊያውሉት ይገባል።

• የወረርሽኝ በሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ሲባል ምናልባት የሁሉም ሰው ለተወሰነ ጊዜ በቤት ውስጥ መቆየት የግድ አስፈላጊ ሆኖ መንግሥት ይህን እርምጃ የሚወስድ ቢሆን፤ አፈጻጻሙ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት፣ የኃይል እርምጃ የሌለበት፣ እጅግ በርካታ ሰዎች ለሕይወታቸው አቅርቦት ፍለጋ በተወሰነ መጠን ሊንቀሳቀሱ የሚችሉና የሚገባ መኾኑን ከግምት ያስገባ ሊሆን ይገባል። በተለይም የሕግ አስፈጻሚ አካላት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ከመንቀሳቀስ አልፎ ወደ ኃይል እርምጃ ከመግባት ሊቆጠቡ ያስፈልጋል። እንዲሁም የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች አቅም በፈቀደ መጠን መንግሥት በቀጥታና ሌሎችንም በማስተባበር መሠረታዊ አቅርቦት ሊያሟላበት የሚያስችል ዝግጅት ያስፈልጋል።

• በሌላ በኩል በዚህ ዐይነት አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቆየት ሁኔታ ውስጥ በተለይ በሴቶችና ሕጻናት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የመብት ጥሰት ተጋላጭነት ከግምት በማስገባት የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን የመፍትሔ መንገድ ማመቻቸት ይገባል።

• የበሽታውን ሥርጭትና አደጋ መከላከል የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት ስላልሆነ ሁሉም ሕብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግና በተለየ ሁኔታ ለችግር የሚጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እና የጐዳና ላይ ተዳዳሪዎችን ጨምሮ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ እና የድጋፍ እርምጃ ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ የሁላችንም ደህንነት በሁላችንም ጥረት ሊረጋገጥ ይገባል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ