ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታወቁ
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በወታደራዊ ዩኒፎርም ሰላምታ ሲሰጡ
የኮሮና ቫይረስ እስኪወገድና ምርጫ እስኪደረግ አገር የማስተዳደሩ ኃላፊነት የብልጽግና መኾኑንም ገልጸዋል
ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 7, 2020)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአገርንና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ሕገ መንግሥቱን የሚጥሱ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚገደድ መኾኑን አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልእክት ላይ ነው።
በአሁኑ ወቅት በአገር ላይ የኮሮና ቫይረስ ሥጋት በተጋረጠበትና የአገር ሉዓላዊነትና ደኅንነት ለአደጋ ተጋልጦ ባለበት ጊዜ ሥልጣንን ያለ ምርጫ እና ከሕግ አግባብ ውጪ በሁከትና በብጥብጥ ካልሰጣችሁኝ አገር አተራምሳለሁ የሚል ማንኛውንም ኃይልን ግን መንግሥት እንደማይታገስ አሳስበዋል። ለዚህም በሁሉም ረገድ ዝግጁ ነን ሲሉም ዶክተር ዐቢይ የመንግሥታቸውን አቋም አሳውቀዋል።
በተለይ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰነዘሩ ያሉ ሕገ መንግሥታዊ ያልኾነ አመለካከቶችና ከሕገመንግሥቱ ከተደነገገው ውጭ በሕገወጥ ምርጫ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴም ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መኾኑን አስታውሰው፤ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል። ሕጋዊ በኾነ አግባብ የኮቪድ 19 ሥጋት እስኪቀረፍ እና ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሔድ ድረስ ደግሞ፤ አገር የማስተዳደር ኃላፊነት ያለው ፓርቲ ብልጽግና መኾኑንም በማስታወቅ፤ ያለ ምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ሥልጣን የመከፋፈል ሕጋዊም ኾነ ሕገ መንግሥታዊ አግባብ እንደሌለው፤ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ይገባኛል የሚለው ፈሊጥ ዴሞክራሲያዊም ሕገ መንግሥታዊም ያለመኾኑን ገልጸዋል። ሕገ መንግሥቱ ከተደነገገው ውጪ በሕገወጥ ምርጫ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ካልኾነ በስተቀር የጨረባ ምርጫ ለማድረግ መነሳት፤ አገርንና ሕዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመኾኑ፤ መንግሥት አገርንና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳልም ብለዋል።
በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት መንግሥታቸው ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅና የመከላከል ኃላፊነት ያለበት በመኾኑም፤ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ስለመኾናቸውም በዛሬው መግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በርካቶች ምርጫውን በጉጉት ሲጠብቁት ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ አንዳንድ ፓርቲዎችና ልሂቃን ምርጫው መደረግ የለበትም የሚል አቋም በያዙበት ጊዜ፤ መንግሥት ግን አገራዊ ፋይዳውን በመረዳት ምርጫው በጊዜው መካሔድ እንዳለበት አምኖ ሲዘጋጅ እንደነበር አስታውሰዋል።
እንዲህ ያለውን አቋም ሲያራምድ የነበረው መንግሥታቸው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማካሔድ እንደማይችል ከገለጸበት ጊዜ ጀምሮ፤ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን በሕግ ባለሙያዎች ሲያስጠና መቆየቱን ገልጸዋል። የሕግ ባለሙያዎችም ምርጫው መተላለፍ የሚችልበትን የሕግ አማራጮችን ማቅረባቸውንና በዚህም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ስለመደረጉ ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕገ መንግሥታዊው አማራጭ ላይ ውሳኔ ተሰጥቶ ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ እንዲሰጥ የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የኾነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ እንዲሰጥበት ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መምራቱንም ገልጸዋል።
ከሰሞኑ ሕገ መንግሥቱ መተርጐም አይችልም የሚል መከራከሪያ የሚያነሱ ወገኖችን በተመለከተ፤ ሕገ መንግሥቱ የሚተረጎም አንቀጽ የለውም የሚለው ክርክር አውቆ ላለማወቅ ከወሰነ አካል ወይም ጥልቅ የኾነ አላዋቂነት ውስጥ ከተዘፈቀ ሰው የሚቀርብ ሐሳብ መኾኑን በማመልከት፤ ሐሳቡ ተቀባይነት እንደሌለውም በዚሁ መልእክታቸው አስታውቀዋል። ሕጋዊ መንግሥት በመኾኑና ብልጽግና ፓርቲም በመላ አገሪቱ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መዋቅር ያለው፣ አገራዊ ለውጡን በመምራት የበርካቶችን ድጋፍ ያገኘ ግዙፍ ፓርቲ ነው በማለት፤ ወረርሽኙ እስኪቀረፍ ድረስ አገርን መምራት ኃላፊነት አለበት ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሙሉ መግለጫ አስነብበኝ! (ኢዛ)



