በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር 14 ደረሰ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
የተጠቂዎች ቁጥር ወደ 1,344 ከፍ ብሏል
ኢዛ (ማክሰኞ ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 2, 2020)፦ በኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ቁጥር አሥራ አራት መድረሱንና ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ ምርመራ 87 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስትር አስታውቋል።
በዛሬው (ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም.) የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ ሪፖርት፤ 87 አዳዲስ ተጠቂዎች የተገኙት ለ3,932 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጐላቸው ነው።
ሰሞኑን በተከታታይ እንደተሰማው በዛሬው ዕለት ሁለት ሰዎች በቫይረሱ በመሞታቸው አጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 14 አድርሷል።
ከዛሬው ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው ሁለት ወጣቶች የ30 እና የ56 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው።
ግለሰቦቹ በኮሮና ቫይረስ መሞታቸው የታወቀው በአስክሬን ምርመራ ሲሆን፤ በተጓዳኝ በሽታ ሕክምና ላይ የነበሩ ናቸው ተብሏል።
በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፤ በዛሬው ዕለት ከተገኙት 87 አዳዲስ ተጠቂዎች ውስጥ 67 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ ሁለቱ ከትግራይ ክልል፣ 6ቱ ከኦሮሚያ፣ 7ቱ ከአማራ ክልል፣ 4ቱ ከሶማሌ ክልል፣ አንድ ሰው ደግሞ ከሐረሪ ክልል የተገኙ ናቸው።
ከ10 - 70 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ከእነዚህ አዳዲስ ተጠቂዎች ውስጥ 41 የሚኾኑት የውጭ ጉዞ ታሪክና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ናቸው። 28ቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 18ቱ ደግሞ ከቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው መኾኑን ታውቋል።
እስከዛሬው ዕለት ድረስ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገባቸው ሰዎች 116,309 ናቸው። ከዚህ ውስጥ 1,344 የሚኾኑት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 231 ደርሷል። በሕክምና ላይ የሚገኙት ተጠቂዎች ቁጥር 1,097 ናቸው። (ኢዛ)



