Total coronavirus cases in Ethiopia, June 13, 2020

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ቅዳሜ ሰኔ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.)

የሟቾች ቁጥር ወደ 55 ከፍ ብሏል

ኢዛ (ቅዳሜ ሰኔ ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 13, 2020)፦ በኢትዮጵያ አድማሱን እያሰፋ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ በ513 ሰዎች ላይ መገኘቱንና አጠቃላይ በአገሪቱ በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 3,166 ደረሰ። የሟቾች ቁጥርም እየጨመረ በመምጣቱ 55 ኾኗል።

ትናንትና ዛሬ ይፋ በተደረጉት የጤና ሚኒስቴር መረጃዎች ባለፉት ሦስት ወራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጠቂዎች የተመዘገቡበት ኾኗል።

የትናንቱ ሪፖርት 5,709 ሰዎች ተመርምረው 245 ተጠቂዎች ሲገኙ፤ የዛሬው (ቅዳሜ ሰኔ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.) መረጃ ደግሞ ባለፉት 24 ሰዓታት 5,644 ሰዎች ተመርምረው 268 የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸው ታውቋል።

በእነዚህ ሁለት ቀናት ለመጀመሪያ ጊዜ በ24 ሰዓታት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው የተነገረበት ነው።

በሁለቱ ቀናት ሪፖርት መሠረት በድምሩ 513 አዳዲስ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች መገኘታቸውን ያመለክታል። ይህም እስካሁን በሦስት ወራት ውስጥ ከ176,504 የሚኾኑ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጐላቸው፤ 3,166 ያህል ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውንና አሁንም የቫይረሱ ሥርጭት እየሰፋ መኾኑን እያሳየ ነው።

እስከዛሬው ዕለት ድረስ በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 55 የደረሰ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሟች የተመዘገበውም ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ ነው። በአሁኑ ወቅትም በፅኑ ሕመም ውስጥ ያሉ 39 ናቸው ተብሏል። ከትናንትናና ከዛሬው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ መረዳት እንደተቻለውም በሁለት ቀናት ውስጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 15 መኾኑን ነው።

በትናንቱ ሪፖርት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሰባት የነበረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ስምንት መሞታቸው ተገልጿል።

ከሁለቱ ቀናት ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው ከሞቱት 15 ሰዎች መካከል አስሩ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ናቸው። አምስቱ ግን ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ሕክምና ላይ የነበሩ ስለመኾናቸው ተገልጿል። በዛሬው መረጃ መሠረት አጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 495 ደርሷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ