በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች በ179 ጨምሮ 3,345 ደረሰ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (እሁድ ሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
የሟቾች ቁጥር ወደ 57 ከፍ ብሏል
ጠቅላላ ያገገሙ 545 እንደደረሰም ተገልጿል
ኢዛ (እሁድ ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 14, 2020)፦ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር በየዕለቱ ከፍ እያለ የመጣ ሲሆን፤ ዛሬ እሁድ ሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ በተደረገውም የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት መሠረት 179 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች በመገኘታቸው አጠቃላይ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ቁጥር ወደ 3,345 አሳድጎታል።
ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 4,845 ሰዎች መካከል 179 ያህሉ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና ከነዚህም ውስጥ 111 ያህሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መኾናቸው ታውቋል።
ቀሪዎቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች ዘጠኙ ከትግራይ ክልል፣ 15ቱ ከኦሮሚያ ክልል፣ 23 ከአማራ ክልል፣ 11 ከአፋር ክልል፣ ሁለት ከድሬዳዋና አንዱ ደግሞ ከሐረሪ ክልል መኾናቸውን ያመልክታል።
ከ179 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ ሦስቱ የውጭ ዜጎች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የሚያመለክተው የዛሬው ሪፖርት፤ ይህም በኢትዮጵያ በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 57 ደርሷል። በአንፃሩ ግን 50 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን፤ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 545 ከፍ ብሏል። 30 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ሕመም ላይ ናቸው ተብሏል።
ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከሁለት ወር እስከ 80 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። (ኢዛ)



