የትግራይ ክልል በነገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አልሳተፍም አለ
የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ (ሕወሓት) እና የፌዴራሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት
አጀንዳው ቀድሞ ሊደርሰኝ ይገባ ነበርም ብሏል
ኢዛ (ዓርብ ነኀሴ ፳፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 4, 2020)፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነገ የጠራው አስቸኳይ ስበሰባ አጀንዳ ቀድሞ ካልደረሰው፤ ክልሉን የሚወክሉ አባላት በስብሰባው ላይ እንደማይሳተፉ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ገለጸ።
የክልሉ ምክር ቤት ለፌዴራሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 1/1999 ዓ.ም. መሠረት ለነገ (ቅዳሜ ነኀሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም.) የተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ አጀንዳውን አስቀድሞ ስላላከ፤ የክልሉ ተወካዮች በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አይሳተፉም ብሏል።
ስለነገው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ስብሰባ አጀንዳ ምንነት በስልክ በተደጋጋሚ ስለመጠየቁም የክልሉ ባለሥልጣናት ገልጸዋል። የክልሉ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ላይም፤ ቀድመን ባለወቅነውና ባልተዘጋጀንበት አጀንዳ በሚታይበት ጉባዔ ላይ ለመሳትፍ እንደማንችል እናሳውቃለን ብሏል።
የነገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የክልሉ የፌዴሬሽን አባላት ጥሪ የተደረገላቸው መኾኑን የሚያመለክተው ይህ ደብዳቤ፤ በስብሰባው ላይ ለመገኘት የግድ አጀንዳው ሊደርሰን ይገባ ነበርም በማለት ይጠቅሳል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የነገ ስብሰባ በአስቸኳይ የተጠራ ሲሆን፤ አጀንዳው ባይገለጽም የትግራይ ክልል ከሚያካሒደው ምርጫ 2012 ጋር በተያያዘ ሊኾን እንደሚችል ሲጠቀስ ነበር። የክልል ምክር ቤቱ ደብዳቤ ከዚህ በታች ቀርቧል። (ኢዛ)




