የሰሜን ዕዝን መገናኛ በመቁረጥ ሠራዊቱን በማስጨፍጨፍ የተጠረጠረው ጄኔራል ተያዘ
በአገር ክህደት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋለው ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ)፣ (መኻል ላይ ቀይ ያደረገው)
ከጄኔራሉ በተጨማሪ 16 ተባባሪ ግብረአበሮቹም ተይዘዋል
ኢዛ (ማክሰኞ ኅዳር ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 10, 2020)፦ በሰሜን ኢትዮጵያ መቀሌ የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር እንዳይገናኝና የመገናኛ ሥርዓቱ እንዲቋረጥ በማድረግ፤ በጁንታው የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ሲያመቻቹ የነበሩ ጄኔራል መኮንኖች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
የፌዴራል ፖሊስ ማምሻውን እንዳስታወቀው የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ኾነው ከጁንታው ሕወሓት ጋር በመጣመር፤ የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ የተቀነባበረውን ሴራ በመከወንና ግንኙነት እንዲቋረጥ ሁኔታዎችን በዋናነት ያመቻቹ ናቸው ከተባሉት ውስጥ በዋናነት ተጥርጥሮ የተያዘው ሜጀር ጄኔራል ገብረመድኅን ፈቃዱ (ወዲ ነጮ) ነው።
ከወዲ ነጮ በተጨማሪ 16 ግብረአበሮቹም ተይዘዋል። በተባባሪነት የተያዙት ጄኔራሎች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች መኮንኖች ናቸው። 17ቱም በአገር ክህደት ተጠርጥረው በፌዴራልና በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ውለዋል። (ኢዛ)



