የፌዴራል ፖሊስ ልዩ ኮማንዶና የወንጀል ምርመራ ቡድን መቀሌ ገባ
ቡድኑ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን ወንጀለኞችን ማደን ጀምሯል
ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 2, 2020)፦ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማምሻውን እንዳስታወቀው የኮሚሽኑ ልዩ የኮማንዶና የወንጀል ምርመራ ቡድን ዛሬ መቀሌ ገብቷል።
ዛሬ ኅዳር 23 ቀን 2013 ዓ.ም. መቀሌ የገባው ልዩ ኮማንዶ እና የወንጀል ምርመራ ቡድን መቀሌ ከሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ በመቀናጀት የጁንታውን ተፈላጊ ወንጀለኛ ቡድን ማደን መጀመሩንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የኮማንዶ ቡድኑ በከተማዋ በሚያደርጋቸው አሰሳዎችና የተለያዩ ኦፕሬሽኖች፤ እንዲሁም በወንጀል ምርመራ ቡድኑ የሚገኙ ውጤቶችን በቀጣይ ለሕዝብ እያሳወቀ የሚቀጥል መኾኑንም አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከትናንት በስቲያ የፓርላማ ማብራሪያቸው፤ በፖሊስ የሚሠሩ ሙያዊ ሥራዎችን፣ የቤት ለቤት ፍተሻን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊቱ የማይሠራ መኾኑንና በሙያተኞች (በፌዴራል ፖሊስ) እንዲሠሩ የሚደረግ መኾኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል። (ኢዛ)