Mulu Nega

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ

የመንግሥት ሠራተኞች ሰኞ ሥራ እንዲጀምሩ ጥሪ ተደርጓል
በሥራ ገበታው ላይ ያልተገኘ በፈቃዱ እንደለቀቀ ይቆጠራል

ኢዛ (ቅዳሜ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 12, 2020)፦ የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ከነገ ታኅሣሥ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባና ከታኅሣሥ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በሥራ ገበታው ላይ የማይገኝ ሠራተኛ በገዛ ፈቃዱ ሥራውን እንደለቀቀ የሚቆጠር መኾኑን ገለጸ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ቅዳሜ ታኅሣሥ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሰጡት መግለጫ መገንዘብ እንደተቻለው፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ የተዋቀረ በመኾኑ ከነገ ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገባ መኾኑን ነው።

ለዚህም ሁሉም የክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደኾነ አስታውቀው፤ አገልግሎት ተቋማት ለሕዝብ ክፍት እንዲኾኑ፤ ነዋሪዎችም ደኅንነታቸው ተጠብቆ ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ አስታውቀዋል።

በሕወሓት ጁንታ ተግባር አገልግሎት ያቆሙ የመንግሥት ሠራተኞች ከሰኞ ጀምሮ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ያሳሰቡት ዶ/ር ሙሉ፤ በሥራ ገበታው ላይ የማይገኝ ሠራተኛ ካለ በገዛ ፈቃዱ ሥራውን እንደለቀቀ የሚቆጠር መኾኑንም አስታውቀዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ የመንግሥት ሠራተኞች ሕዝብ አገልጋይ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አጀንዳ አስፈጻሚዎች ባለመኾናቸው፤ ሠራተኞች ይህንን ተገንዝበው በሥራ ገበታቸው ላይ መገኘት የሚኖርባቸውና ሞያዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የንግድ ድርጅቶችም ከነገ ጀምሮ ወደ መደበኛ አገልግሎታቸው ይመለሱ ዘንድም ጥሪ አስተላልፈዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!