የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስትራዜኒካ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ሲረከቡ

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የመጀመሪያውን የአስትራዜኒካ የኮሮና ቫይረስ ክትባቱን በተረከቡበት ወቅት

ኢትዮጵያ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የአስትራዜኒካ ክትባት ተረከበች

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 8, 2021)፦ በየዕለቱ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ (ኮሮና ቫይረስ) የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በቀን እንደገና ከአንድ ሺሕ በላይ እየኾነ መጥቷል። እስከ ዛሬ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 167,133 ደርሷል።

ከሰሞኑ በተከታታይ እየወጡ ካሉ መረጃዎች መገንዘብ እንደተቻለውም፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ ከአንድ ሺሕ በላይ ኾኗል። ትናንት የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በወጣው መረጃ መሠረት በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ምርመራ ከተደረገላቸው 6,490 ሰዎች ውስጥ 1,109 ቫይረሱ የተገኘባቸው ኾነዋል። በዛሬ ዕለት ደግሞ ምርመራ ከተደረገላቸው 6,342 ሰዎች ውስጥ 995ቱ በቫይረሱ የተያዙ ናቸው።

ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺሕ በላይ እየኾነ የመጣ ሲሆን፣ ይህም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የቫይረሱ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች 2,184,745 የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 167,133 ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ሕይወታቸው ያለፈ ደግሞ 2,442 ናቸው። 138,639 ከበሽታው ያገገሙ መኾኑን የዛሬው የካቲት 29 ቀን 2013 ዕለታዊ መረጃ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ጥምረት 2.2 ሚሊዮን መጠን የያዘ የመጀመሪያውን የኮቪድ 19 ክትባት የተረከበች ሲሆን፣ የኮሮና ቫይረስ ክትባቱ አስትራዜኒካ የሚል መጠሪያ ያለው ነው። ይህ ክትባት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ደረጃ በደረጃ ለመስጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ያጠናቀቀ መኾኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የክትባት መርኀ ግብሩም በቀጣይ ሳምንታት ይፋ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚያመላክተው የጤና ሚኒስቴር መረጃ፤ ክትባቱ ወደ ማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲኾን የሚያስፈልጉ ወጪዎቹን ለመመደብ የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመኾን እየሠራም ነው ተብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ