Ethiopian Citizens for Social Justice

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)

ፓርቲው ነገም ቀጣይ ፓርቲ ኾኖ የሚዘልቅ ስለመኾኑ ገልጿል

ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 24, 2021)፦ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 14 ቀን በተካሔድው ምርጫ 2013፣ ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትንና ለምርጫ ቦርድ ያሳወቃቸውን በርካታ ተግዳሮቶችን ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከኾነ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንወስዳለን አለ።

ፓርቲው ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የምርጫው ውጤት እስኪገለጽ ድረስ የሚጠብቅ ሲሆን፤ ነገር ግን “ቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትንና “በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅናቸው በርካታ ተግዳሮቶችን በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥ ከኾነ፤ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካላት ይዘን የምንሔድበትን ሁኔታ ቀድመን ለሕዝብ የምናሳውቅ ይኾናል” በማለት ገልጿል።

በዚህ ምርጫ የኢዜማ ሚና ምን ድረስ እንደነበረ በሰፊው ያተተው የፓርቲው መግለጫ፤ ፓርቲው መፍትሔ ሰጪ ፖሊሲዎችን የነደፈ ጭምር መኾኑንም አስታውሷል።

በሌላ በኩል ግን ፓርቲው ነገም ቀጣይ ፓርቲ ኾኖ የሚዘልቅ ስለመኾኑ በዚሁ መግለጫው ላይ አመላክቷል።

ይህንንም “ነገም ኢትዮጵያ አገራችን ሉዓላዊ ግዛቷን የሕዝብን ደኅንነት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርስባት ጠንካራ አገር እንድትኾን ኢዜማ ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ኾኖ በጥንካሬ እንደሚቀጥል እንገልጻለን” ብሏል።

ኢዜማ ዛሬ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን መሠረት ለመጣል የሚጠይቀው መሥዋእትነት እጅግ ረጅምና መራር ነው። በተለይም እንደ አፍሪካ ውስጥ ባሉ በበርካታ ውስብስብ አሠራሮች በተተበተቡ አገሮች ውስጥ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ጥበት፣ ከፍተኛ የሥልጣን ጉጉትና የመሳሰሉት እንቅፋቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ቀይደው ይይዙታል። ድህነቱ፣ ኋላቀርነቱ፤ የዜጎች የፖለቲካ አረዳድ ወዘተ ችግሮቹን ይበልጥ ያባብሱታል።

በተለይም በዘውግና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የአገራችን የፖለቲካ ትርክት ላለፉት 30 ዓመታት ከአንድነት ይልቅ ልዩነቶቻችንን አግዝፎ በትውልዱ ላይ ቁርሾን ዘርቷል። ዛሬም ከዚህ የማንነት የፖለቲካ አዙሪት ለመላቀቅ አልቻልንም። ከዚህ የችግር አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የዜግነት ፖለቲካው ብርቱ ዋጋ የሚያስከፍል ቢኾንም ነገም ብቸኛው አማራጭ መኾኑ ሊታመን ይገባል።

አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ በተለያዩ የመንግሥት ቅርጽና የፖለቲካ ፍልስፍና በየጊዜው ሥልጣን ላይ በወጡ ኃይሎች ስትመራ መቆየቷ ይታወቃል። ላለፉት 30 ዓመታት እስከ 6ኛው ዙር ምርጫ ድረስ በምርጫ ብቻ ሥልጣን ለመያዝ የተሞከረው ሒደት ተስፋ ሰጪ ባይኾንም ዜጎች የምርጫ ተሳትፎ ማድረጋቸው አንድ ጥሩ እርምጃ ነው ሊባል ይችላል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሒደቱ እና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለጸ ባይኾንም በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር። ለዚህ ምርጫ ሰላማዊነትና የአገሪቱን የነገን ቀጣይነት በምርጫ ለማረጋገጥ፣ ዜጎች በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ኢዜማ የበኩሉን ድርሻ በኃላፊነት ተወጥቷል የሚል የጸና እምነት አለን። ከምንም በላይ ለአገር መረጋጋትና ለሕዝብ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነትም በተግባር አስመስክሯል።

በመኾኑም ለቀጣይ የኢዜማ መዋቅር አደረጃጀት ለፓርቲያችን ደጋፊዎች፣ አባላትና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች የሚከተሉትን ማሳወቅ ይኖርብናል።

1ኛ/ ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው የ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት እስከሚገለጽ የምንጠብቅ ሲሆን፤ ቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳደረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙትንና በየሰዓቱ ለምርጫ ቦርድ ያሳወቅናቸው በርካታ ተግዳሮቶችን በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥባቸው ከኾነ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካላት ይዘን የምንሔድበትን ሁኔታ ቀድመን ለሕዝብ የምናሳውቅ ይኾናል።

2ኛ/ ኢዜማ የምርጫ 2013 አጠቃላይ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ የሚያስተባብር የምርጫ ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ኮሚቴ ከዓመት በፊት አዋቅሮ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ይታወቃል። ይህ ኮሚቴ አጠቃላይ የምርጫውን ሒደት በተመለከተ ከሚያዘጋጀው የግምገማ አጠቃላይ ሪፖርት፣ በድርጅት በኩል፣ በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተቋቋመ ቡድንና ከፓርቲው ውጪ በተመረጡ ገለልተኛ አካላት ከሚቀርበው ግምገማ ተነስተን አጠቃላይ ሁኔታውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንገልጻለን።

3ኛ/ እንደሚታወቀው የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ትግል ቀጣይነት ያለውና ከምርጫ በኋላም ቢኾን ተጠናክሮ የሚቀጥል መኾኑ እሙን ነው። በዚህ ረገድ ኢዜማ ጊዜያዊ ፓርቲ ሳይኾን ገና ከመነሻው ከምርጫ ወረዳ ጀምሮ ሲዋቀር ሩቅ ተጓዥና ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ኾኖ ነው። ከዚህ አንጻር በምርጫው ሒደት ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በሕግ አግባብ እየጠየቅን ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የድርጅቱን መዋቅር ይበልጥ በማጠናከር ወደ ሥራ የገባን መኾኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

4ኛ/ ኢዜማ በተቋቋመ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከየትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ በላቀ መልኩ በመላው አገሪቱ 455 የምርጫ ወረዳ መዋቅሮችን አደራጅቶ በጥንካሬ እየተንቀሳቀሰና በምርጫ 2013 ገዢውን ፓርቲ በብርቱ የሞገተ ፓርቲ ነው፤ ሕዝባዊ መሠረቱም ሰፊና ጠንካራ ነው።

ከዚህ አንጻር የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በምርጫ ሒደት የተገኘውን ውጤት፣ ልምድ፣ የሰው ኃይል፣ ልዩ ልዩ ግብዓቶች እና ወዘተ የመሳሰሉትን ፓርቲውን ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀምና ድርጅቱን በጥንካሬ ለመምራት በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከዚህ ምርጫ ማግስት ጀምሮ ብርቱ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና በቀጣይ ለሚያጋጥሙን አገራዊ ጉዳዮችና ሰላማዊ ለኾኑ የትግል እንቅስቃሴዎች ራሳችንን እንድናዘጋጅ የከበረ ጥሪ ማስተላለፍ እንሻለን።

ኢዜማ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም ከምርጫ መቃረብ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መፍትሔ ሰጪ ፖሊሲዎችን የነደፈ፣ ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ያሳወቀ፣ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በሰለጠነ መንገድ ያካሔደ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን መሠረቱን ዜግነት ላይ ያደረገ ፓርቲ መኾኑንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ የራሱን ተሳትፎ እንዳደረገ እናምናለን።

በመጨረሻም ነገም ኢትዮጵያ አገራችን ሉዓላዊ ግዛቷና የሕዝብን ደህንነት ተጠብቆ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳት ጠንካራ አገር እንድትኾን ኢዜማ ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ ኾኖ በጥንካሬ እንደሚቀጥል እየገለጽን በፀሐይና በዝናብ ወስጥ፤ ቀንና ለሊት ተሰልፋችሁና በብርቱ ጫናና መዋከብ ውስጥ ኾናችሁ ድምጻችሁን ለኢዜማ የሰጣችሁትን ከልብ እያመሰገንን ያልመረጣችሁንንም ውሳኔያችሁን የምናከብር መኾኑን እንገልጻለን።

ኢዜማ
ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ