20210302 adwa

ልዩ ሪፖርት

ኹከትና ግጭቱን ተከትሎ በአገሪቱ የነበረውን ውጥረት የበዛበት ሳምንት በተመለክት የተዘጋጀ ልዩ ሪፖርት

ይህ ግጭት የሃይማኖትና የብሔር ቅርፅ ወደ ያዘ አደገኛ ጥፋት ይደርስ ነበር

ኢዛ (ከጥቅምት 17 - 23 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ውስጥ ውጥረት የነገሠበት፣ ኀዘን ያጠላበት፣ ቀጣዩስ ምን ይሆን? በሚል ብዙዎች ሥጋታቸውን በተለያዩ መንገዶች የገለጹበት ነበር። በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተፈጠረው ኹከት አነሳስ አጀማመርና ዓላማው ምን እንደነበር ለማወቅም የተዘበራረቀ ስሜት ያሳደረ ነበር።

ይህ ጉዳይ የሳምንቱ ዐበይት ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ከለውጡ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የፈተነ ያልተጠበቀ ሁኔታ ተደርጐ ሊወሰድ የሚችሉ ክስተቶችን ያስተናገደበት ነው ማለትም ይቻላል። በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው ኹከት ወደ 78 የሚሆኑ ዜጐችን ሕይወት ቀጥፏል (እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሠጡት መግለጫ የሟቾች ቁጥር 86 ደርሷል)። ንብረት አውድሟል። ጃዋር መሐመድ አስተላለፈ የተባለውን ጥሪ ተከትሎ መቀስቀሱ የሚነገርለት ይህ ድርጊት፤ የሃይማኖትና የብሔር ቅርፅ ወደ ያዘ አደገኛ ጥፋት ይደርስ እንደነበርም በተለያዩ መንገዶች ተገልጿል። አንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በዚህ ጥሪ ብቻ የተፈፀሙ ናቸው ወይስ ሌላ ነገር ነበር? የሚልም ጥርጣሬ ያስነሳ ነው። አሁንም የዚህ ኹከት ያሳረፈው ጠባሳ እንዲህ በቀላሉ ተዳፍኖ ይቀራል ተብሎ አይታመንም። በአጭር ጊዜ ይህ ሁሉ ውድመት እንዴት ሊከሰት ቻለ? የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት የቸገረ ሆኗል። ለጥፋቱ መድረስ ምክንያት የሆኑና የተሳተፉ ለፍርድ ይቅረቡ የሚለው ድምፅ ግን አሁንም ጐልቶ እየተሰማ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በአገር በሌሉበት ወቅት የተፈጠረው ኹከት አገሪቷ ቀጣይ ጉዞ ምን ሊመስል እንደሚችል ለመገመት ያስቸገረ ቢሆንም፤ ኹከቱ ያስከተለው ጥፋት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በየአቅጣጫው ወዴት እያመራ ነው? የሚለውን ጥያቄ ከማጫር አልፎ በተለያዩ ወገኖች ውግዘት ያስከተለ ጉዳይ ሆኗል። ከለውጡ ወዲህ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የመንግሥት የተለያዩ ተቋማት በአንድና በዚህ ሰሞናዊ ጉዳይ አቋማቸውን በተከታይ ያንፀባረቁበት የተለየ ሳምንት አድርጐታል።

የሃይማኖት አባቶች መልእክት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያ ርዕሰ ሊቃነጳጳስ አቡነ ማትያስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያ ርዕሰ ሊቃነጳጳስ አቡነ ማትያስ በተገኙበት የሲኖዶሱ መግለጫ ሲነበብ

በዶክተር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት አገሪቷን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በዚህ ደረጃ መግለጫ የተሰጠበት ጉዳይ አልነበረም። የሃይማኖት አባቶች ጠንክረው የወጡበት ሲሆን፣ በሰሞኑ ኹከት መግለጫ በማውጣትና ድርጊቱን በመኮነን፤ እንዲሁም ለተጐዱ ወገኖች መፅናናትን በመመኘት አቋማቸውን ካሳወቁት መካከል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች ቅድሚያ ይይዛል። ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አባል የሆኑበት ይህ ሕብረት፤ በአንድ ላይ ሆነው ባወጡት መግለጫ ድርጊቶቹን በእጅጉ ኮንነው፣ መንግሥት ሕዝብ የሚዲያ ተቋማትና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ሊወስዱ ይገባቸዋል ያሏቸውን አቋማቸውን አንፀባርቀዋል። በተለይ ግን መንግሥት ሕግ ያስከብር የሚለውን አቋማቸውን አጉልተው ጠቅሰዋል። ሰላም እና እርቅ እንዲፈጠር ጠይቋል። ችግሮችን በመነጋገርና በሰላም መፍታት እየተቻለ ወዳልተገባ ተግባር መግባት እንደማያስፈልግም አስታውሷል።

ባሳለፍነው ሳምንት በአገሪቱ የተፈጠረው አለመረጋጋት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም በማለትም የጉባዔው መግለጫ አስታውቋል። ችግሩን ሽፋን በማድረግ ወደ ሃይማኖት ግጭት ለመቀየር የተደረገው ጥረትም በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም በመጥቀስ፤ ድርጊቱ የየሃይማኖቶችን መሠረታዊ አስተምሮ ካለመገንዘብ ወይም ከጭፍን ወገንተኝነት የመነጨ ስሜት መሆኑን በመረዳት፤ ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ እርስ በርስ በመደጋገፍ አገራቸውንና አካባቢያቸውን ሰላም በጋራ ነቅተው ይጠብቁ ብሏል። ይኸው መግለጫ በወጣበት ዕለት የየሃይማኖቱ መሪኦውች በተናጠልም ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያ ርዕሰ ሊቃነጳጳስ አቡነ ማትያስ የተፈጠረውን ድርጊት በመኮነን፤ “በቃ! እንላችኋለን ትሰሙን እንደሆነ፣ ትቀበሉን እንደሆነ ነፍስ አትግደሉ!” በማለት አያይዘውም የሃይማኖት አባቶች ይህንን ስንላችሁ ሁላችሁም ጆሯችሁን ከፍታችሁ እንድትሰሙ እንጠይቃለን ያሉት ብፁእነታቸው፤ "ሰው ሰውን መግደል የለበትም። ወንደም ወንድሙን ለምን ይገድላል? ይሄ በጣም ያሳዝናል" ብለዋል። አንዴ በሃይማኖት ሌላ ጊዜ በፖለቲካ ምክንያት እየተደረገ የሰውን ሕይወት ማጥፋትና አገር እንዲበጠበጥ ማድረግ ኩነኔ፣ ኃጢአትና በደል መሆኑን በማስገንዘብ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና አንድነታችንን እንፈልጋለን፣ አብረን መኖር፣ ሠርተን መኖር እንፈልጋለን ነው የሚለው፤ ይህ ሊጠበቅለት ይገባል ብለዋል። አያይዘውም መንግሥትም ቢሆን የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅና ማስጠበቅ ይኖርበታል በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። መንግሥት ሊዳኝ መሆኑን፣ አጥፊውን ሊቀጣ ደኅናውን ሊሸልም ነው የተቀመጠው፤ በትክክልና በእኩልነት ሊያስተዳድር እንደሚገባም ብጹዕነታቸው ተናግረዋል። ስለዚህ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት በማመልከት አሁን የተፈጠረው ችግር የልቦች መከፋፈል ነው ብለዋል። መጀመሪያ የመንግሥት ኃላፊዎች አንድ ሁኑ፣ ልባችሁ አንድ ይሁን፣ አእምሯችሁን ሰብስቡ አንድ ላይ ተሰለፉ። ለሕዝባችሁና ለአገራችሁ አስቡ ብለዋል። አያይዘውም ለመንግሥት ኃላፊዎች ባስተላለፉት መልእክት፤ "የመንግሥት ኃላፊዎችን አደራ የምንለው ሕጉን ጠብቁ፤ በሕግ አስተዳድሩ፤ ኃላፊነት አለባችሁ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

ሕዝቡም በትክክለኛ መንገድ ሲመሩት መመራት አለበት የሚል መልእክት ብፁዕነታቸው አስተላልፈዋል። ከሰሞኑ የተፈጠረው ነገር እጅግ ያሳዘናቸውና እንዲህ ያለነገር ከየት ነው የመጣብን? በማለት ጭምር በመጠየቅ ሐሳባቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲሕ ዑመር እንድሪስ ናቸው።

እንዴት እርስ በእርሳችን እንጋደላለን። እንደ እንስሳ ሰው እንዴት ያርዳል፣ ይህ የሰው ጠባይ አይደለም የአውሬ ፀባይ ስለመኾኑ ተናግረዋል በማለት የተፈፀመውን ድርጊት አምርረው የኮነኑት ቀዳሚ ሙፍቲሕ፤ አያይዘውም የተፈጠረውን ነገር እያዩ መሪዎችስ ዝም ማለታቸው ምንድነው? ያሉት ሼሕ እንድሪስ ሁሉም ለሰላም እንዲቆረቆር፣ ወደ ሰላም እንመጣ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን

"የትኛውም ብሔር ብቻውን ሌሎቹን ሁሉ አሸንፎ በሰላም ሊኖር አይችልም፤ የትኛውም ሃይማኖት ብቻውን ሌሎቹን ጨቁኖ አይኖርም" በማለት በሰሞኑ ድርጊት ሐሳባቸውን የሠጡት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ሕብረት ፕሬዝዳንት መጋቢ ጻድቅ አብዶ ናቸው። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያንን በተለያዩ መንገዶች ለማጋጨት ብዙ መሞከሩን፤ ነገር ግን እንዲህ ያለው ነገር ብዙ ተሞክሮ አለመሳካቱን ጠቅሰዋል። “ሆኖም አንዱ ነፃነት ከሌለው ሁላችንም ነፃነት የለንም። የአንዱ ሃይማኖት ተከታይ የሚበዛበት አካባቢ በሌላው ላይ ጥቃት የሚያደርስ ከሆነ፤ ሌላውም በሚበዛበት ቦታ ጥቃት ያደርሳል” በማለት እንዲህ ያሉ ድርጉቶች አደገኝነታቸውን ተናግረዋል።

ብልህ ሰው ከጐረቤቱ ይማራልና እንደ ሶሪያ ካሉ መማር እንደሚገባም አሳስበዋል። መጋቢ ጻድቁ በንግግራቸው መሃልም ሲቃ ተናንቋቸው "እኔ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ በጣም አዝኛለሁ። አንድም ቀን ስለስደት አስቤ አላውቅም፤ በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ፤ ነገር ግን እንደ አሁን አልተሰማኝም" በማለት በሰሞኑ አሰቃቂ ድርጊት ልባቸው ስለመነካቱ ገልጸዋል።

እንዴት ሰው ሰውን እንዲህ ይገላል? በማለት ወለቴ አካባቢ የቤተክርስቲያናቸው አገልጋዮች ላይ የተፈፀመባቸውን አረመኔያዊ ግድያ ከአእምሯቸው በላይ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች

በሰሞኑ ኹከት የድርጊቱን አሳዛኝነት በመጥቀስ መግለጫ ካወጡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ኢሰመጉ ይገኙበታል።

በተለይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የመጀመሪያ ተብሎ ሊገለጽ የሚችለውን መግለጫ የሰጡበት ነበር። በዚህ መግለጫቸው ከ70 – 80 የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸውን አስረድተዋል። ድርጊቱ የተፈፀመበት መንገድ አግባባ አለመሆኑንም ተናግረዋል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት በዚሁ መግለጫ፤ ሐሳብን መግለጽ ባልተከለከለበት በዚህ ወቅት፣ በእንዲህ ያለው መልክ ስሜትን መግለጽ ተገቢ እንዳልነበር አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ በተከሰቱት ኹከቶች የተሳተፉ አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ያሳሰበ ሲሆን፤ በኹከቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በሕግ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል ብሏል።

በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥና ተሃድሶ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች እንዳስመዘገበ ሁሉ ውስብስብ ተግዳሮቶችም እየገጠሙት እንደሚገኝ የሚጠቁመው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ኹከቱ ካስከተለው ጥፋት ባሻገር የሕግ የበላይነትን በእጅጉ የተፈታተነ መኾኑ እንዳሳሰበው የሚጠቀስ ነው።

ኢዜማና ፕሮፌሠር ብርሃኑ

የኢዜማ አመራሮች
የኢዜማ አመራሮች

ክስተቱ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ከፍተኛ አደጋና ሥጋት ላይ የጣለ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነም በማመልከት፤ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ረገድ በመግለጫ አቋሙን በማሳወቅና በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመሥጠት ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጐች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ነው። ኢዜማ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በሠጠው መግለጫ ላይ፤ ድርጊቱን አውግዞ የሁኔታውን ሳሳቢነት በዝርዝር አስቀምጧል። በጉዳዩ ላይ አመራሮቹም ሰፊ ማብራሪያ ሠጥተዋል።

በተለይ የኢዜማ ሊቀመንበር ፕሮፌሠር ብርሃኑ ነጋ የኹከቱ አነሳስን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያዎች የሰጡበት ነበር። እንዲህ ያሉ ግጭቶች ከጀርባ ያለውን ነገር መመርመር እንደሚያስፈልግና የሚፈለገውም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሒደት ለመግታት የታሰበ ሴራ ስለመሆኑም አመልክተዋል።

ይሄ ነገር የሆነበት ምክንያት ምንድነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ወጣ ያለ ሐሳብ መሥጠት እንደሚፈልጉ የገለጹት ፕሮፌሠር ብርሃኑ ነጋ፤ እንዲህ ዐይነት ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉት ሆን ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይኑን ከዋናው ጉዳይ ላይ እንዲያሳ ነው።

ይህንን ያሉበትን ምክንያት ሲያብራሩም፤ "ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠርና ራሱ በመረጠው መተዳደር የመፈለጉን ሒደት ረስቶ፤ በደመነፍስ ራሱን ከመከላከል ጋር ብቻ አይቶ ያንን ቁምነገር እንዲተወው የታሰበ ጉዳይ ነው ብዬም አስባለሁ።” በማለት ገለጸዋል።

ይህንንም የሚሉት ዝም ብለው ከመሬት ተነስተው ያለመሆኑን የገለጹት ፕሮፌሠር ብርሃኑ፤ ይሄ ነገር መነሳት ከጀመረ ወዲህ የነበሩትን አንዳንድ ድርጅቶች የሚያወጡት መግለጫም ሲታይ የሚያሳየው ነገር እንደሚኖር አመልክተዋል።

እንደምሳሌ ያነሱትም የኢሕአዴግ መዋኀድ ሲነሳ፤ ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲ ከሆነ ኢሕአዴግ ትፈርሳለች እያሉ የሚያወጡትን መግለጫ ነው። በምን አግባብ አንድ ፓርቲ ከፈረሰ አገር ይፈርሳል የሚለው ነገር ማኅበረሰቡ መጠየቅ የሚኖርበት ሲሆን፣ ይሄ ለ27 ዓመት ከብሔር ማንነት ጋር የተዘራው የፖለቲካ ውጤት መኾኑን ጠቁመዋል።

የዘር ፖለቲካ ያመጣውን አደጋ በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ የነበሩ ኃይሎች፤ ለሁሉም እኩል የኾነ ሥርዓተ መንግሥት መፍጠር ይሻላል በሚል በሚሔዱበት ጊዜ ነው፤ እነዚህ በዘውግ ብሔርተኛነት የሚነግዱ ኃይሎች “ኢሕአዴግ ከፈረሠ አገር ይፈርሳል” በማለት የሚፈጥሩት ውዥንብር አሁን ላለው ችግር አንድ ማሳያ መኾኑን ጠቅሰዋል። “አንድ አገራዊ ፓርቲ ይቋቋም ማለት፤ ፌዴራሊዝሙን ማፍረስ ነው” በማለት በፍጹም የሌለ ነገር በመንዛት ማኅበረሰቡን ወደ ግጭት ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት እንደሆነና፤ እንዲህ ያለው ጥረት በጋራ ሲታይ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ጥረት ለማስተጓጐል የታለመ ስለመኾኑ የሚያሳይ ነው ሲሉ ፕሮፌሠር ብርሃኑ ተናግረዋል። ምርጫ ካልተደረገ አገር ይፈርሳል ሲሉ እንዳልነበር፤ አሁን ደግሞ ምርጫ መደረግ የለበትም ወደሚል መሸጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንዲያየው የምፈልገው በአጠቃላይ ይህ ዓላማ በጨበጣ “እኔ እወክልሃለሁ” የሚለው ነገር ቆሞ፤ በእርግጠኝነት ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ወደሚችልበት ሥርዓት ሲመጣ፤ ያኔ ደግሞ ሕብረተሰቡ አንዴ ምርጫውን ካደረገ በኋላ በጨበጣ “እኔ እወክልሃለሁ” የሚል ነገር እንደማይኖር ስለገባቸው፤ ያ እንዳይመጣ ለመከላከል የሚደረግ ሙከራ ነው ብለው እንደሚያምኑ ፕሮፌሠሩ በሠጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም ዐይነት ሁኔታ ለዝንተ ዓለም ዴሞክራሲ ለማምጣት የታገለበትን ሒደት አገሪቱን በማተራመስ ውስጥ እንዳይገባም ፕሮፌሠሩ አሳስበዋል። ይልቅ በጣም ብዙ በደል ደርሶበት፤ ያንን በደል ሁሉ የፈፀሙትመውን ሥርዓትና ያንን በደል የፈፀሙትን ሁሉ ጋር ይቅርታ ተባብለን ወደፊት እንሒድ፤ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንሒድ፣ ሲባል “የለም” ብሎ እንደገና ማኅበረሰቡን ወደ ግጭት መክተት በኋላ ጣጣው ሁሉም ላይ የሚመጣ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ እንዲያውቀው እፈልጋለሁ ብለው የተናገሩት ነጥብ ደግሞ፤ በምንም ዐይነት መልኩ በየቦታው በሚለኩሷቸው ክስተቶች ተዘናግቶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በምንም ዐይነት መገደብ የሌለበት መኾኑን ነው።

ይሄ የሰሞኑ ድርጊት አሁን ፊታችን ላይ ስለመጣ እንጂ፤ ብዙ ቦታ የሚደረግ የነበረ መሆኑንም በመጠቀስ፤ ዴሞክራሲ መሬት ላይ እንዳይረግጥ በነፃነት እንዳይመርጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለመኾኑ የሚገልጽ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። አሁን ላለው ሁኔታ መፍትሔው ሁለት ስለመኾኑ ያመለከቱት ፕሮፌሠር ብርሃኑ፤ አንዱ በየአካባቢው ራሱን የሚከላከልበት እንደ ኮሚኒቲ ፖሊሲ አደራጅቶ ራሱን መከላከል መኾኑን ገልጸዋል።

ከምንም በላይ ግን መንግሥት የዜጐች ደኅንነት መጠበቅ ላይ ኃላፊነት አለበት። ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ካልቻለ፤ ሰውን ወደ አውሬነት ተመለስ ማለት ነው ብለዋል። መንግሥት ኃላፊነቱን የሚወጣበት ጊዜ በመሆኑ፤ እንደ ኢዜማ ከኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በላይ ምንም የሚመለከተን ነገር የለም። በዚህ ጉዳይ ላይ በምንም መልኩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም እንተባበራለን። መንግሥት ሰላም ለማስጠበቅ በሚወስዳቸው እርምጃዎች እንተባበራለንም በማለት ለየት ባለ መልኩ ማብራሪያ ሠጥተዋል።

መፈክሮችና ጥሪዎች

ሰሞናዊውን ድርጊት በመቃወም በዋሽንግተን ዲሲ (አሜሪካ) ተቃውሞ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም “ሕግ ይከበር!” የሚለው ድምፅ የተሰማበት ነው። በሳምንቱ ውስጥ የወጡ መግለጫዎች በሙሉ ጥፋቱን ያደረሱ “ለፍርድ ይቅረቡ!” የሚል አንደምታ ያለው ነው። 71 ፓርቲዎችን ያሰባሰበ ነው የተባለውም የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች፤ የተፈፀመው ድርጊት ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት አለ ወይ? የሚያስብል ነው ብለዋል። “የድርጊቱ ተሳታፊዎች ለሕግ ይቅረቡ!" የሚለውን አቋም እነርሱም የሚጋሩት መሆኑን የሚያመለክት አቋም በመግለጫቸው ውስጥ አካተዋል።

የመንግሥት አቋምና የውይይት መድረኮች

የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ከሰጡ በኋላ፤ የኦዴፓ (የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ) አባላት በተለያዩ ከተሞች በመሄድ ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ አቶ ለማ መገርሳና ሌሎች ከፍተኛ የኦዴፓ አመራር አባላት ያደረጉትን ውይይት በዝርዝር የሚያስረዱ መረጃዎች ባይወጡም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በአምቦ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር ተመልክቷል። ሆኖም የኦዴፓ አመራሮች የተመረጡ ከተሞች በመሔድ ሕብረተሰቡን እያወያዩ ነው። “ለምን ውይይቱ ይፋ አይደረግም?” የሚለው ጥያቄ መልስ ባላገኘበት ሰዓት እሁድ ዕለት (ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም.) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመንግሥትን አቋም የሚያንፀባርቅ መግለጫ ሠጥተዋል።

"ሕግ ይከበር!”

ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ፤ በሰሞኑ ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 78 (እሁድ ዕለት ጠ/ሚ/ሩ በተሠጡት መግለጫ ቁጥሩ 86 ደርሷል) መሆኑንና ግጭቱን በመቀስቀስ የተጠረጠሩ 409 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል። ማንም ሰው ከኢትዮጵያ ሕግ በታች መሆኑንም በመግለጽ መጠየቅ ካለበት ይጠየቃል የሚል መግለጫቸውን ሠጥተዋል።

በየትኛውም ደረጃ የሚገኘ አካል በግጭት ውስጥ መሳተፉ እስከተረጋገጠ ድረስ በሕግ የሚጠየቁ መሆኑንም ተናግረዋል። የሰሞኑ ግጭት ቀስ በቀስ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት እየታየበትና እየሰፋ የመሄድ ምልክት ታይቶበት እንደነበር በማስታወስ ነገር ግን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባገዳዎችና ምሁራን እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉ ባደረጉት ጥረት ጥቃቱን የማስቆም ሥራ እንደሠሩም ከአቶ ንጉሡ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። ይህ ባይሆን ጉዳቱ የከፋ ይሆን ነበርም ብለዋል።

አሁንም ቢሆን በየትኛውም ደረጃ ግንኙነት ያላቸው ጥፋት ውስጥ የተሰማሩ በየትኛውም ደረጃ እየተጣራ የእርምት እርምጃ የሚወስድና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ የሚሠራ መሆኑን በመግለጽም ማብራሪያ የሠጡት አቶ ንጉሡ፤ ሕግ የማስከበሩ ሥራ ላይ መንግሥት ጠንካራ አቋም አለው ብለዋል።

አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረቡ ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብ ያመለከቱት ኃላፊው፤ "ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ማናችንም ከኢትዮጵያ ሕግ በታች ነን። ማንም ሰው ከኢትዮጵያ ሕግ በታች ነው። ማንም ሰው ከኢትዮጵያ ሕግ በታች በመኾኑ በሕግ እንደሕጉ አግባብ ይጠይቃል።” በማለት በሰሞኑ ጉዳይ መንግሥት ያለውን አቋም አንፀባርቀዋል። ይህ ሁኔታ የአገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት በመጨመር በሕብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ አመለካከቶች እንዲንፀባረቁ እያደረገ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!