20210302 adwa

ከኅዳር 1 - 7 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

ከኅዳር 1 - 7 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

በዩኒቨርሲቲዎች የፈጠረው ግጭትና የዶ/ር ዐቢይ ማስጠንቀቂያ

ኢዛ (ከኅዳር 1 - 7 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሁለት ተማሪዎች ሞት ከተሰማ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ያለመረጋጋት ተፈጥሮ ሰንብቷል። በደንቢ ዶሎም የአንድ ተማሪ ሞት መሰማቱ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የፈጠረው ውጥረት የሳምንቱ መሪ ዜና ነበር። በጅማና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠረው ሥጋት ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ዶርማቸውን (ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኝ ማደሪያቸውን) ለቀው በቤተ እምነቶች እንዲጠለሉ አስገድዷቸዋል።

ለደኅንነታችን እንሰጋለን ያሉ ተማሪዎች ቤተ እምነቶችን መሸሸጊያ ማድረጋቸው ሊደርስብን ይችላል ያሉትን ጥቃት ለመከላከል ነበር። እንዲህ ያለው ክስተት በጅማ፣ በወልዲያ፣ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲዎች ታይቷል። የመማር ማስተማር ሒደቱንም አስተጓጉሏል። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተፈጠረው ድባብ ወላጆችን ያስጨነቀ፣ መምህራን የወጠረ የአገር መሪዎችንም ያሳሰበ ከመሆን አልፎ፤ እውቀት መገብያ ተብለው በተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲህ ያለው ግጭትና ጠብ መልሶ መላልሶ የመደጋገሙ ነገር ደግሞ ከምንም በላይ ማሳሰቡ አልቀረም። ይሁንና በመማሪያ ግቢ ውስጥ ደም አፋሳሽ የሆነ ጠብ የሚፈጠርበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ቢሆንም፤ ችግሩ የአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት ነፀብራቅ ስለመኾኑ ግን አይታበልም።

ሆን ተብሎ ቦታውን የፖለቲካ መሻኮቻ ለማድረግ ታስቦና ታቅዶ ስለመቀነባበሩ አመላካችም ነው። እንዲህ ያለው ችግር እንዳይፈጠር እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኝባቸው ከተማ ነዋሪዎች ጋር ኾነው፣ ከመላው ኢትዮጵያ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቹ የመጡ ተማሪዎች በወግና በማዕረግ የተቀበሉበት ምክንያት እንዲህ ያለው ችግር እንዳይፈጠር ነበር። ይሁንና ችግሩን ከመፈጠር ያገደው ነገር አልነበረም። እንማራለን ብለው ዩኒቨርሲቲ የገቡ ወጣቶችን ሕይወት ቀጠፈ፣ የመቁሰል አደጋ ደረሰ፣ የመማር ማስተማር ሒደቱን አስተጓጐለ።

አሁንም ስጋቱ ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም። ዩኒቨርሲቲዎችን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግና አለመረጋጋቱ ከዚህም የከፋ እንዲኾን የሚሹ ወገኖች ከአድራጐታቸው እንዲቆጠቡ ካልሆነ ተማሪዎች ቢሰጉ ላይፈረድባቸው ይችላል። ነገር ግን ሽማግሌዎችና የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ተማሪዎችን በማረጋጋት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ እያደረጉ ነው። በቤተ እምነቶች የተጠለሉ ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ግቢ የመመለስ ሥራዎች በከተማ ነዋሪዎችና በዩኒቨርሲቲው አመራር እየተሠራ ነው። ይህ ችግር ከተከሰተ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ ከከፍተኛ የፀጥታ እና የመከላከያ አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጉት ምክክር ላይ፤ ይህ ድርጊት ከቀጠለ ዩኒቨርሲቲዎችን እስከመዝጋት የሚያደርስ እርምጃ ይወሰዳል የሚል መረር ያለ ንግግር አድርገዋል።

ኅዳር 5 ቀን 2012 ምሽት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት፣ "ወቅታዊው የዩኒቨርሲቲዎች ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ እስከመዘጋት ድረስ እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል።

ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ ውጤት አምጥቶ የሚገባ የድሃ ልጅ በማያውቀው ጉዳይ እየተጐዳና የእሳት ራት እየሆነ ስለመሆኑ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንዲህ ያለውን ድርጊት ለማስቆም ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።

ሆኖም አሥርና ሃያ ሰው ማግለለ የሚያስፈልግ ከሆነ የሚያገሉ መኾኑን፣ ሁሉም የሚታወክ ከሆነ ግን ዩኒቨርሲቲውን እስከ መዝገት የሚደርሱ ስለመሆኑ ያስጠነቀቁበት መድረክ ነበር።

ችግሩ የሚፈጠረው የፖለቲካ ትርፍ በሚሹ ውጫዊ ኃይሎች መኾኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ "የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እነሱ ሳይሞቱ ከሚያጋድሏቸው አጥፊዎች ራሳቸውን ማቀብ አለባቸው" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ትምህርት ከጀመሩ አንድ ወር ተኩል የሆናቸው ሲሆን፣ እስከሳምንቱ መጀመሪያ ድረስ በሰላም የነበረ ሲሆን፤ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሁለት ተማሪዎችን መሞ ተከትሎ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም።

በዓርቡ ስብሰባ ላይ የተከሰቱት ግጭቶች ምክንያታዊ ያልኾኑ ስለመሆናቸው የተጠቀሰበትም ነበር። ሚዛናዊ ያልሆኑ አመለካከቶችም እንደ ችግር የሚታይ ነው። ዩኒቨርሲቲዎቹ በሚገኙበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ለዩኒቨርሲቲዎቹ ሰላም መሥራት የሚጠበቅባቸው እንደሆነም ተገልጿል።

በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከፌዴራል እስከታች ድረስ ያሉ የፌዴራል የፀጥታ መዋቅሮች ከዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት ሠላም የማስፈን ሥራ እንዲሠሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በዚህ ውይይት ላይ የፀጥታ፣ የመከላከያ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የክልል አመራሮች ጭምር የተገኙበት ሲሆን፣ የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱበትና አስተያየቶች የተሰነዘሩበት ነበር። አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች “ሕግ ይከበር! እኛም ሥጋት አለብን” ያሉ መኖራቸው ታውቋል።

በዚህ መድረክ ላይ ሰሞናዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ጽሑፍም ቀርቦ ነበር። በዚህ ውይይት መምህራን ጭምር ለደኅንነታችን እንሰጋለን የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል። ይሁንና በሳምንቱ የነበረውን ያህል ውጥረት አሁን ላይ ረግቧል። (ኢዛ)

የኢሕአዴግ ውሕደትና የማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ

ለየት ባለ መንገድ ሳምንቱን በሙሉ በተለይ በመንግሥት የመገናኛ ብዙኀን ያለማቋረጥ ትንታኔ ሲሰጥበት የነበረው አንኳር ጉዳይ፤ የኢሕአዴግ ውሕደት ከጫፍ መድረሱን የሚመለከቱ ዘገባዎች ናቸው። የግል መገናኛ ክዙሃንም ይህ ጉዳይ ተቀዳሚ ዜና ሆኖ ሰንብቷል።

በተለይ ውሕደቱን በተመለከተ የተዘገቡ ሪፖርቶች ውስጥ ጐልተው የወጡት በእስከዛሬው የኢሕአዴግ ቆይታ አጋር ፓርቲዎች ተገልለው የቆዩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነበር። አጋር ድርጅቶች እንደማንኛውም የግንባሩ እኅት ድርጅቶች እኩልነታቸው መጠበቅ አለበት የሚለውን በማጉላት፣ ውሕደቱ ለእርነሱ የመጣ ስለመኾኑ ጭምር ለማሳየት ከዓመታት በፊት በኢሕአዴግ ጉባዔዎች ላይ ስለውሕደቱ ሲነገሩ የነበሩ ንግግሮችን በመቀንጨብ በማስታወቂያ መልክ ተደጋግሞ መስተጋባቱም የሳምንቱ የተለየ ክስተት ነበር።

የውሕደቱ አስፈላጊነትን ለማሳየት ሲባል የቀደሙ ፋይሎችን በማውጣት ሕዝብ እንዲያውቃቸው ከተደረጉት ግለሰቦች ውስጥ፣ ከለውጡ ወዲህ እምብዛም በመገናኛ ብዙኀን ምስላቸው የማይታዩት ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንዱ ናቸው። ሌሎችም ቀድሞ የኢሕአዴግ አመራሮች የተናገሩትን በማስተጋባትም አጋር ፓርቲዎች ተገልለው መቆየታቸውን አመላክቷል።

በተለይ አቶ መለስ አጋር ድርጅቶች ለምን የኢሕአዴግ አባል ድርጅት አልሆኑም የሚለውን የገለጹበት መንገድ ግን እንደ አዲስ ብዙዎችን ያስደመመ ነበር።

“አጋር ድርጅቶቻችን ኢሕአዴግን የማይቀላቀሉበት አንድ መሠረታዊ ምክንያት አለ። እነዚህ አጋር ድርጅቶች የሚሠሩባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች አብዛኛው አርብቶ አደር አካባቢዎች ናቸው። የአርብቶ አደር አካባቢዎች ከመኾናቸው ጋር ተያይዞ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚኾን ማኅበራዊ መሠረት የለም። ማኅበራዊ መሠረቱ በሌለበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ይኾናል ብለን መገመት አንችልም። ማኅበራዊ መሠረቱ እስኪፈጠር ድረስ በዚህ አካባቢ አጋሮች እንጂ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ድርጅት ሊኖሩን አይችሉም።” ነበር ያሉት።

ይህ አቶ መለስ በ2003 ዓ.ም. ያደረጉት ንግግር ሳምንቱን ሙሉ ተደጋግሞ ተሰምቷል። የቀድሞ ሚኒስትር ዶ/ር አብዱልመጅድ ሁሴን በ1993 ዓ.ም. ስለ ኢሕአዴግ ውሕደት የተናገሩት ደግሞ፤ “የምናቀርበው አንድ ጥያቄ በሚቀጥለው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ አጀንዳችሁ ላይ የእነዚህ የአጋሮችን ጥያቄ እንድትጨምሩ እንጠይቃችኋለን።” የሚል ነበር።

የኢሕአዴግ ውሕደት ጉዳይ ዛሬ ሳይሆን ቀድሞ የተጀመረ መኾኑን ለማመላከትም አቶ ስዩም መስፍን በ2003 ዓ.ም. የተናገሩት ንግግር ከፋይል ወጥቶ፤ “ከአጋር ድርጅቶች ጋር አጋር ድርጅቶች የሚለውስ እስከመቼ ድረስ ነው? ኢሕአዴግን ወደ ውሑድ ፓርቲ የማሸጋገሩ ጉዳይ ማን ያንሳው? የሚለው ነው። ግን ይሔ ጉዳይ 22 ዓመት አልፎናል። በአጋርነት የያዝናቸውን እንቀፍ ስንል አሁን ያለውን የኢሕአዴግ ፕሮግራም ይዞ መሔድ ማለት ላይኾን ይችላል። ብዙ አማራጮቹ ሊታዩ ይችላሉ።” ማለታቸው እንዲታወቅ ተደርጓል።

እንዲህ ባለው ትውስታ የዘለቀው የሳምንቱ ጉዞ አሁን ላይ ኢሕእዴግን ለማዋሐድ እየተደረገ ያለው ጥረት በሁሉም የግንባሩ አባላትና አጋር ድርጅቶች የተደገፈ መሆኑ በይፋ የተገለጸበት ሲሆን፤ እንዲህ ያለው ውሳኔ ላይ ግን ሕወሓት በተቃራኒው ቆሞ ውሕደቱ የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ መስመሩን የሳተ ነው በማለት ተቃውሞውን እየገለጸ ነው። በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ምሁራን፣ የፖለቲካ ምሁራን ይህ ውሕደት መልካም መኾኑን የገለጹበት አስተያየቶች በተደጋጋማ የቀረቡበትም ነው። ወደ ሳምንቱ መጨረሻም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለብርቱ አገራዊ ጉዳይ ስብሰባ ተቀምጧል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ይካሄዳል የሚለው መረጃ ከተሠራጨ ወዲህ የስብሰባው አጀንዳ የኢሕአዴግ የውሕደት ጉዳይ እንደሆነ እርግጥ ነበር።

እንደታሰበውም ይኸው የውሕደቱ ጉዳይ አጀንዳ ኾኖ የግንባሩን ውሕደት አጽድቋል። የግንባሩ ውሕደት በስድስት ተቃውሞና በ27 ድጋፍ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።

ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስምምነት ላይ የደረሰበትን ውጤት በተመለከተ ጠቅላይ ማኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው፤ ዛሬ የፓርቲ ውሕደቱን በተመለተ ያደረግነው ወሳኝ ስብሰባ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል።” በማለት ገልጸውታል። ውሕደቱ የኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ተሰሚነት ላልነበራቸው አጋር ድርጅቶች እኩል ድምፅ የሚሠጥ ሕብረ ብሔራዊ ውክልናን የሚያረጋግጥ፣ ኹነኛ አቅጣጫ መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ዐቢይ፤ “የፓርቲው ውሕደት አገራዊ አንድነትን ከሕብረ ብሔራዊነት ጋር አስተሳስሮ ለመጓዝ እድል የሚሠጥ ነው።” በማለት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በኢሕአዴግ ውሕደት ላይ የደረሰበትና ውጤታማ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።

በኅዳር 6ቱ ስብሰባ ላይ በውሕደቱ ላይ ተቋውሞዋቸውን የገለጹት ስድስቱ የሥራ አስፈፃሚ አባላት የሕወሓቶች ናቸው። ውይይቱ ኅዳር 7 ቀን የቀጠለ ነው። (ኢዛ)

በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክክር

በዚህ ሳምንት ሌላው ፖለቲካዊ ክንውን በኦሮሚያና በአማራ ክልል ውስጥ የሚንቀሰቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማነጋገራቸው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በሁለቱ ክልሎች ያሉ ባለሀብቶችም በአንድ አዳራሽ ኾነው ስለመምከራቸው የተሰማው በዚህ ሳምንት ነው። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አብንና ኦፌኮ ይገኙበታል። በተለይ የኦፌኮ ሊቀመንበር በዚያን ዕለት የተደረገውን ውይይት እስከ ዛሬ ያልተደረገ ተስፋ ሰጪ ብለውታል።

"ቁጭ ብለን በግልጽ ቋንቋ ለመናገር ሞክረናል። ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ከተሳካልን ይህ ታሪካዊ እርምጃ ሊሆን ይችላል" ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ መንግሥት እንደ መንግሥት ድርሻውን፣ በሁለቱ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች እነዚያን ችግሮች አብሮ በመለየት መፍታት አለባቸው የሚለው ስምምነት የመጀመሪያው ታሪካዊ እርምጃ ስለመሆኑም ገልጸዋል። የገጠመንን ታሪካዊ ፈተና ለማለፍ ጠቃሚ ስለመሆኑም ፕሮፌሰር መራራ ተናግረዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከነበሩት የአዴፓ ተወካይ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩትን ግጭቶች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ማስቆም ሁላችንም የየበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ስምምነት የተደረሰበት ስለመሆኑ ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻችን በዚሁ ጉዳይ ማግባባትና ማስተማር፣ መመካከር እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው።

በሁለቱ ክልሎች በተከሰቱት ችግሮች በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የመሥጠት ሥራዎችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሠሩ ስምምነት ላይ ስለመደረሱም አቶ ንጉሡ ገልጸዋል።

"ከዚህ በፊት በተማሪዎች እንቅስቃሴ በተለያዩ መድረኮች ያልተነሡ ጥያቄዎች የሉም" ያሉት ደግሞ የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ናቸው። “ከዚህ በፊት በተማሪዎችም እንቅስቃሴ በመድረኮች በዩኒቨርሲቲዎች ያልተነሱ ጥያቄዎች የሚነሳ ነገር የለም እዚህ፤ ያኔም ተነስቷል። ያኔ ሰው አይሞትም፤ በብሔር እርስ በእርሱ አይጋጭም። ያኔ ያልተነሱ ጥያቄዎች አሁን የሚነሱ ነገሮች የሉም።” ያሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ፤ አሁን ግን ለምንድን ነው ይህ የኾነው? ትንሽ ውስጣችንን መፈተሽ ይፈልጋል ብለዋል። ይህንን የትኛው ኃይል ነው ወደዚያ እየወሰደው ያለው? በእኛ ውስጥ ወይም ከእኛ ውጭ ያሉ አክተሮች የሚለው ጉዳይ መፈተሽም እንዳለበት ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት፣ አክቲቪስቶች፣ ሚዲያ በንግግርም ኾነ በጽሁፍ አሁን እንደሚታየው ሕዝብና ሕዝብን የሚያጋጭ አቅጣጫ የሚወስድ ተግባር ተቀባይነት እንደማይኖረውና የእርሳቸውም ፓርቲ ይሁን ሌሎች ፓርቲዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ስለመስማማታቸው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአማራና በትግራይ ሕዝቦች ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያግዝ የምሁራን ውይይት የተካሄደውም በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ይህ የምክክር መድረክ በሰላም ሚኒስቴር ከዩ.ኤስ.አይ.ዲ (USID) ጋር በመተባበር የተዘጋጁ ሲሆን፣ የምክክር መድረኩ ዐቢይ ርዕስ “በሰላም ጊዜ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ቃል የተካሔደ ነው። በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለውን ውጥረትና ሽኩቻ ለማስቀረት የመፍትሔ ሐሳቦች ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል። ይኸው ውይይት እስከ ኅዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚቀጥል ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ የአብን ሊቀመንበርም ከመንግሥት ጋር ለመሥራት ዝግጁ መኾኑን ያንፀባረቁበት ሳምንት ነበር። የአብን ሊቀመንበር በበኩላቸው አንዳንዴ በጣም የሚያባብሱ ንግግሮች ከፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች፣ ከአክቲቪስቶች፣ ከሚዲያ አካላት ሲወጣ በየጊዜው የሕዝቦቻችንን አንድነት እየሸረሸረ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

እንዲህ ዐይነቱ ተግባር ብዙ ንጹሐንን እንዲጎዱብን ያደረገ ነውና ከእንዲህ ያለው ድርጊት ራሳቸውን ለማቀብ ፓርቲዎቹ ስለመስማማታቸው ገልጸዋል። የአማራም ኾነ የኦሮሞ ሕዝብ አንዱ የአንዱን ጥያቄና ፍላጎት እንዲገነዘብ የማድረግና ወደፊት የምናስባትን ኢትዮጵያ በሠለጠነ ድርድር በዲሲፕሊን ለመሥራት ዓላማ ያደረገ ሥራ እንዲሠራ የሚያስችል ውይይት እንደነበር ዶ/ር ጫኔ ጠቁመዋል።

ከዚህም ሌላ ግጭቶችን የሚያባብሱ ንግግሮችን፣ ጽሑፎችንና ዘገባዎችን የሚሠሩ ሚዲያዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችና መሪዎች፤ እንዲሁም አክቲቪስቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግም ፓርቲዎቹ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ተገልጿል።

እንዲህ ያሉ የምክክር መድረኮች በቀጣይነት የሚቀጥሉ ሲሆን፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወስዳቸውን ሕጋዊ እርምጃዎች ፓርቲዎቹ እንደሚደግፉ መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)

የሰኔ 15ቱ ግድያና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

ከሳምንቱ ዐበይት ዜናዎች ውስጥ ኅዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተሰጠው መግለጫ ተጠቃሽ ነው። በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች መሠረት በማድረግ የተሠጠው ይህ መግለጫ፤ ጥቃቶቹ በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ የተመራ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መኾኑን በይፋ የገለጹበት ነው።

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህርዳር በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም በወቅቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቅቆ በጉዳዩ ላይ ቀጥታ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩትን ለሕግ የሚያቀርብ ስለመሆኑ ያሳወቀበት መግለጫ ነው። በአማራ ክልል ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ አቶ አዘዝ ዋሴና አቶ ምግባሩ ከበደ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ባልደረቦቻቸው ለመፈንቅለ መንግሥት ተልዕኮ በተሠጣቸው አካላት የተፈፀመ መኾኑን በምርመራ ማረጋገጡንም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ጸጋዬ ገልጸዋል።

ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ዓቃቤ ሕጉ በሠጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፤ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ለመፈንቅለ መንግሥት ተልዕኮ በተሠጣቸው አካላት ከክልሉ ልዩ ኃይል የተውጣጡ ሰዎች በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ላይ የነበሩትን ዶክተር አምባቸው መኮንን በጥይት በመደብደብ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጋቸውና በአቶ እዘዝ ዋሴ ላይ በተመሳሳይ ጥቃት ሕይወታቸውን እንዳለፈም ገልጸዋል። በወቅቱ ጥቃት የተፈጸመባቸው አቶ ምግባሩ ከበደ ደግሞ ሕክምና ላይ በነበሩበት ወቅት ሕይወታቸው እንዳለፈ የሚያመለክተው የዓቃቤ ሕጉ መረጃ፤ ይህንንም ጉዳይ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማረጋገጥ እንደተቻለ ነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የተናገሩት። ይህ ጥቃት ከሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግበት እንደነበረ በምርመራው መረጋገጡን የተናገሩት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና በአክቲቪስቶች ዝግጅት የተካሄደበት ነው ብለዋል።

ለተፈጸመው ጥቃት ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች መመልመላቸውን ጠቁመው፣ ሥልጠናና ስምሪት ተሠጥቷቸው መሳተፋቸውንም የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መግለጫ አስታውቋል። በዚህ ድርጊት ተሳታፊ ከሆኑት ውስጥ በሥነ ምግባርና መሰል ሁኔታዎች ከአገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ መዋቅር የተሰናበቱ አባላት ጭምር ተመልምለው የድርጊቱ ተሳታፊ ስለመሆናቸው ይኸው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማብራሪያ ያመለክታል። በሰኔ 15ቱ ጥቃት የ15 ሰዎች ላይ ሞት፣ በ20 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ማጋጠሙን መግለጫው በተሠጠበት ወቅት ተገልጿል።

በአዲስ አበባ በቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጄር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ላይ የተፈጸመው ጥቃትም፤ በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ የተመራው መፈንቅለ መንግሥት አካል ስለመሆኑም ለማወቅ የተቻለበት የዚህ ሳምንት የዓቃቤ ሕግ መግለጫ፤ ዓላማው በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖችን ለመግደል ያመላከተ ነበር ተብሏል። ይህም ጄኔራል ሰዓረ ላይ ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ጥቃቱን ተከትሎ በሥፍራው ይገኛሉ ተብለው በተገመቱት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላንም በመግደል በሠራዊቱ ውስጥ መከፋፈል ለመፍጠር መኾኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል። ለዚህም በባህር ዳር በከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ላይ ግድያው ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ በጄኔራል ሰዓረና አብረዋቸው በነበሩት ሜጄር ጀኔራል ገዛኢ ላይ በግል ጠባቂያቸው ግድያ ሊፈጸም እንደቻለ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ደረስኩበት ያለው የምርመራ ውጤት ይጠቁማል።

ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ ሲካሄድ በነበረው ምርመራ በባህር ዳር 277 እንዲሁም፣ አዲስ አበባ ደግሞ 140 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ታውቋል። በተጨማሪም እንዲያዙ ማዘዣ ከወጣባቸው 70 ግለሰቦች ውስጥ 31 በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል። በ55ቱ ላይም ክስ እንደሚመሠረትባቸው በመጥቀስ፤ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ 22 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳብም እንዲዘጋ ተደርጓል ነው ያሉት።

የሰኔ 15ቱ ጥቃትን ተከትሎ በተደረገ ምርመራ በተጠርጣሪዎቹና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ወገኖች ተይዘው የነበሩና በጥራጥሬ 114 ክላሽንኮቭ፣ ሦስት ብሬንና ሌሎች መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ ሲሆን፤ ከጥቃቱ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው መሣሪያዎች ተለይተዋል ብለዋል። ከተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት፣ መኪና፣ ፍላሽ ዲስክና ኮምፒውተሮች የተገኙ መረጃዎች በኤግዚቢትነት መያዛቸውንም ነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የገለጹ ሲሆን፣ በተካሄደው ምርመራም ከባህር ዳር ከተያዙት ውስጥ 45ቱ የወንጀል ተሳትፏቸው አነስተኛ በመኾኑ በምስክርነት ተለይተዋል ተብሏል።

በአዲስ አበባ ተይዘው ከነበሩት 140 ተጠርጣሪዎች ውስጥ 61ዱ በዋስትና ስለመፈታታቸው የገለጹት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፤ 5ቱ ደግሞ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ውጭ ከጦር መሣሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው እየታየ እንደሆነም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከተሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመገንዘብ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት የሰነድና የሰው ማስረጃ የተጠናቀቀባቸው ከባህር ዳር 55 እና ከአዲስ አበባ 13 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመሥረት ዝግጅት መጠናቀቁን ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል። በተጠርጣሪዎቹ ላይም ክስ ይመሠረታል ተብሏል። (ኢዛ)

ከዋሽንግተን አዲስ አበባ የደረሰው የህዳሴ ግድብ ውይይት፤ ቀጣዩ ካይሮ ላይ ይደረጋል

የታላቁ ህዳሴ ግድብና የሦስቱ የተፋሰስ አገሮች ጉዳይ ባሳለፍነውም ሳምንት አጀንዳ ነበር። በዋሽንግተን ነጩ ቤተመንግሥት የተደረገው ውይይት በኋላ ሦስቱ አገሮች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኅዳር 5 እና 6 ቀነ 2012 ዓ.ም. ያካሄዱት ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ በተሠጠው መግለጫ፤ የተሻለ መግባባት የተቻለበት እንደሆነ አመልክቷል። ይህንን ውይይት አስመልክቶ መግለጫ የሠጡት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ፤ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተደረገው የውይይት መድረኮች በእጅጉ መሻሻል የታየበት መኾኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባው ውይይት ዋነኛ አጀንዳ የግድቡ ውኃ አያያዝና አለቃቀቅ ዙሪያ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰው፤ የተስማሙባቸው ነጥቦች የመኖራቸውን ያህል ያልተስማሙባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፤ ያልተሰማሙባቸውን እያንዳንዱ አገር ማብራሪያ እንዲሠጥበት በማድረግ ሰፊ ውይይት ስለመካሔዱ ይጠቁሟል።

በቀጣይ ለሚደረጉ ድርድሮች ሦስቱ አገራት የሚመሩበት ሰነድ ስለመዘጋጀቱም ታውቋል። ዋሽንግተን ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በአዲስ አበባ ላይ በተደረገው ውይይት ላይ ከዓለም ባንክና ከአሜሪካ የተወከሉ ታዛቢዎች ተሳትፈውበታል። ቀጣዩ የሦስትዮሽ ውይይት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በግብጽ ርዕሰ ከተማ ካይሮ ይካሄዳል። (ኢዛ)

የገቢዎች ሚኒስቴርና በቀዳሚው ዓመት ብልጫ ያለው የግብር ገቢ

ከሳምንቱ ኢኮኖሚያዊ ክዋኔዎች ውስጥ በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችለው የአገሪቱ ዋነኛ የግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብራቸውን ከፍለው የሚያጠናቅቁበት መኾኑ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት አራት ወራት ከግብር ያገኘው ገቢ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወቅት አሰባስቦት ከነበረው ሁሉ ብልጫ ያለው መኾኑን ገልጿል።

እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገለጻ፤ በዚህ አራት ወር ማሰባሰብ የቻለው የግብር ገቢ 90 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የገቢ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ታስቦ ከነበረው በ32 በመቶ ወይም በ21.39 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተቀዛቀዘ በሚል እዚህም እዚያ የሚሰማው እሮሮ እየተሰማ ባለበት ወቅት የመንግሥት የገቢ ግብር መጠን ከፍ ብሏል።

የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም፤ ግብር ከፋዩ በዚህ ወቅት በፈቃደኝነት ግብሩን በአግባቡ በመክፈሉና እየከፈለ በመኾኑ፤ እነዚህን ኃላፊነታቸውን በሚገባ የተወጡት ግብር ከፋዮችን በይፋ አመሥግነዋል። እግረ መንገዳቸውንም የአገሪቱን የታክስ ሥርዓት ለማዘመንና የተሻለ አገልግሎት ለመሥጠት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣዩ ወር 10 ሺህዎች በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት ግብራቸውን መክፈል ይጀምራሉ።

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት አራት ወራት በየወሩ ያገኘውን ገቢ የተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንደሚያሳየው፤ የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ወር በኾነው ሐምሌ 2011 ዓ.ም. 17.9 ቢሊዮን ብር፤ በነሐሴ 2011 ዓ.ም. ደግሞ 20.1 ቢሊዮን ብር፣ በመስከረም 2012 ዓ.ም. 19.42 ቢሊዮን ብር፤ በጥቅምት 2012 ዓ.ም. ደግሞ 32.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል።

ይህም ሚኒስቴሩ በአራት ወር እሰበስባለሁ ብሎ ያቀደው 89.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ክንውኑ 90.2 ቢሊዮን ብር በመኾኑ ከእቅድ በላይ ሰብስቧል። (ኢዛ)

ሁለተኛው ከወለድ ነፃ ባንክ የሚፈለገውን ካፒታል አሟላ

ባሳለፍነው ሳምንት በተለየ ሊጠቀስ የሚችለው ኢኮኖሚያዊና ቢዝነስ ክዋኔ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለመሥጠት አክሲዮን ሲሸጡ ከነበሩ ባንኮች ውስጥ “ሒጅራ ባንክ” ለማቋቋም የሚያስችለውን ካፒታል ማሟላቱን ይፋ ማድረጉ ነው።

ባንኩ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሟላቱን ማሳወቁ ነው። ከተከፈለው 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሌላ ቃል የተገባ ወይም የተፈረመ ካፒታሉ ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ አስታውቋል። ይህም በአገሪቱ ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለመሥጠት ካፒታሉን በማሟላት ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ ያለ ሁለተኛው ባንክ አድርጐታል።

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መሥጠት እንደሚችል መፈቀዱን ተከትሎ ከሒጅራ ባንክ ቀደም ብሎ ምዘም ባንክ የሚፈለገውን ካፒታል አሟልቶ ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጀ መኾኑን በኢትዮጵያ ዛሬ መዘገቡ አይዘነጋም(ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!