Ethiopia Zare's weekly news digest, week 5th, 2013 Ethiopian calendar

ከጥቅምት 2 - 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አምስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጥቅምት 2 - ጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም.) በኢትየጵያ ከሚስተዋለው የፖለቲካ ትኩሳት አንጻር የሚከሰቱ ግጭቶችና ኹከቶች ለዜጐች ሕይወት መጥፋት፣ ንብረት መውደምና የመፈናቀል መንሥኤ የኾኑ ተደጋጋሚ ክስተቶች ታይተዋል። ከጥቂት ወራት ወዲህ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተፈጸመ ያለው አሰቃቂ ድርጊት የወቅቱ የፖለቲካ አጀንዳ ኾኖ ዘልቋል። ባሳለፍነው ሳምንት በዚህ አካባቢ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። በመከላከያ ሠራዊትና በታጣቂዎች መካከል ከሌላው ጊዜ በተለየ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል።

በፖለቲካ ፍትጊያዎች እየፈጠሩ ካሉት ቀውሶች ባሻገር የተፈጥሮ አደጋዎች ለአገሪቱ ራስ ምታት ለዜጐች መከራ ኾነዋል። በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአንበጣ መንጋ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን የደረሰ ማሳ ዶግ አመድ አድርጐ ከአሁኑ እጃቸውን ለምፅዋት አዘርግቷቸዋል።

ከብር ለውጡ ጋር ተያይዞ የሐሰተኛ የብር ኖት ሕትመት እየተስተዋለ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት በዚህ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች እስከነማተሚያቸው ተይዘዋል። ሐሰተኛ የብር ኖት ማተሚያዎች በአማራ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉልና በአዲስ አበባ ተገኝተዋል።

ዛሬም ሙስና ነቀርሳዋ የኾነባት ኢትዮጵያ 9.2 ቢሊዮን ብር የሙስና ጉዳዮችን እየመረመረ መኾን ፖሊስ ያስታወቀው በሳለፍነው ሳምንት ነው። 96 በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎች በፖሊስ እጅ ገብተዋል። ሀብት አላስመዘግብም ያሉ ቱባ ባለሥልጣናት በቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ስለመወሰኑ የተነገረውም በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በወላይታ 4 ሺህ የሚኾኑ የቀድሞ የጸጥታ አባላት ተደራጅተው እየፈጸሙ ነው የተባለው አደገኛ ተግባር ጆሮ እንዲሰጠው የተደረገውም ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በሳምንቱ ዐቢይ ዜናዎች የተወሰኑት በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ተጠናክረው እንደሚከተለው ቀርበዋል። መልካም ንባብ!

በቤንሻንጉል ጉሙዝ በተፈጸመው አሰቃቂ ተግባር እጃቸው አለበት የተባሉ ተያዙ

እንደ ቀድሞው ሳምንታት ሁሉ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት በቤንሻንጉል ጉሙዝ እየተፈጸመ ያለው አሰቃቂ ተግባር ትልቅ ትኩረት የተሰጠው አገራዊ ጉዳይ ኾኗል። በክልሉ በመተከል ዞን የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸመው ጥቃት የመንግሥትን የማያዳግም እርምጃ የሚሻ ኾኗል። የድርጊቱ አሳሳቢነት ላይ ተመርኩዞ ከሰሞኑ እንደተሰማው መንግሥት ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረጉ ሒደት ላይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በተለይ ከዚህ ግጭት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ ባለሥልጣናትም እጃቸው ያለበት ከመኾኑ ጋር ተያይዞ እስካሁን 504 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ የፖለቲካም፣ የሕግም እርምጃዎች እየተወሰዱ መኾኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ለጥቃት ተጋላጭ የኾኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በሚሊሻ በማደራጀት ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እንደሚደረግ በመጥቀስ፤ በክልሉ ለተፈጸሙት ጥቃቶች በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተጠያቂ መደረጋቸውን አውስተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከአማራ ክልል ጋር በመኾን ጠንካራ ሥራ እንዲሠራ እና ያጋጠሙትን ችግሮች ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ አቅጣጫ መሰጠቱ በመግለጫው ላይ ተነስቷል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተፈጠረ ያለውን ችግር በተመለከተ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሰው ልጅን አሰቃቂ ሕልፈት በተደጋጋሚ እያስተዋሉ የሚያልፉ ጭንቅላት የላቸውም በማለት አቋማቸውን ያንጸባረቁ ሲሆን፤ ለጥቃት ተጋላጭ የኾኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ በሕብረተሰቡ ተመልምለውና ሥልጠና ወስደው በአካባቢ ሚሊሺያነት ተደራጅተው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

“የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ሳይሆን፤ በአጥፊዎች የሚፈጸም ጥቃት ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቀደም ሲል ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ከ20 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች መመለሳቸውንም አስታውቀዋል። “የሕዝባችንን በየትኛውም የአገሪቷ ክፍል በሰላም የመኖር መብት እናረጋግጣለን” ያሉት አቶ ተመስገን፤ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ከአማራ ክልል ጋር በመኾን ጠንካራ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የቅርብ ክትትል በማድረግ ማንም በተላላኪነትም ኾነ በውክልና ጦርነት አካባቢውን ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመመከት የክልሉ መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል። በዚህ ጉዳይ በማኅበራዊ ገጻቸው ያሠፈሩትን አቋማቸውን የቋጩትም፤ “የትኛውም ሕገወጥ እንቅስቃሴ በትዕግሥት እንደማይታለፍ ለወዳጅም ለጠላትም አረጋግጣለሁ” በማለት ነው። (ኢዛ)

በ3 ወር ከማዕድን 178 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ
ወርቅ ከእቅድ በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኘ

ባለፉት ሦስት ወራት ከማዕድን ዘርፍ ከ178 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኘ። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የሦስት ወራት አፈጻጸም በተመለከተ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢ/ር ታከለ ኡማ ለመገናኛ ብዙኀን መግለጫ ሰጥተዋል። ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሬ ካስገኙት ማዕድናት መካከል፤ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ኳርትዝ፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር እና እምነበረድ ተጠቃሾች ናቸው።

ወርቅን በተመለከተ በባህላዊ መንገድ ከሚያቀርቡ አቅራቢዎች 2,241 ኪ.ግ ወርቅ ለውጭ ገበያ ቀርቧል። በእቅድነት ተይዞ የነበረው 251 ኪ.ግ ወርቅ ለውጭ ለማቅረብ ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል የተደረገው የወርቅ ማሻሻያ ዋጋ የወርቅ አቅራቢዎችን በመሳቡ ምክንያት ከታቀደው በ298.9 በመቶ በላይ ወርቅ ለውጭ ገበያ ቀርቧል።

በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ወራት የተቋሙ የ10 ዓመት እቅድ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ለሚመለከታቸው አካላትም ተልኳል። የማዕድንና ነዳጅ ዘርፉ የፖሊሲ ማሻሻያ እንደተደረገ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስረድተዋል።

በአገሪቷ የሌለውን የወርቅ ቤተ ሙከራ ለማቋቋም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በማዕድንም ይሁን በነዳጅ ዘርፍ ላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲኾን የሕግና ተግባራዊ ማሻሻያዎች እየተተገበሩ መኾኑን ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።

ኢንጂነር ታከለ፤ በቀጣይ ጊዜያትም የተጀመሩ የሰነድ ሥራዎች የሚጠናቀቁበትና ተቋማዊ ግንባታው ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ይኾናል ብለዋል። (ኢዛ)

ሐሰተኛ የብር ኖት ሲያትሙና ሲያሠረጩ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

መንግሥት የብር ኖት ለውጥ ከጀመረ ወዲህ አልፎ አልፎም ቢኾን እየታየ ያለው ሐሰተኛ ገንዘብ ጉዳይ አሳሳቢ መኾኑ አልቀረም። ባሳለፍነው ሳምንት ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ከተሰጠው መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው የሐሰተኛ የብር ኖት ይታተምባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን በመለየት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ታተሙባቸው የተባሉና ምልክት ከታየባቸው አካባቢዎች በአማራ ክልል በጐንደርና ጐጃም፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ክልልና አዲስ አበባ መኾናቸው ተጠቁሟል። ከሰሞኑ እንደተሰማውም ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው ዞኖች ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጸጥታ ተቋማት መካከል አጠቃላይ 830,000 ሐሰተኛ ብር ከነሕትመት ማሽኑ ተይዟል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ እንደገለጹት ሐሰተኛ የብር ኖት ሲያትሙ ከነበሩት ውስጥ አንዳንዶቹን ከነማሽናቸው መያዛቸውን ገልጸው፤ አሁንም በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለመቆጣጠር ሠራዊቱ እየተንቀሳቀሰ ነው። (ኢዛ)

ኢሕአፓና የሊቀመንበሩ ስንብት

ከለውጡ በኋላ ከውጭ ወደ አገር ከገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የኾነው ኢሕአፓ፤ ፓርቲውን በሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩን አቶ ጳውሎስ ሶርሳን ከኃላፊነት ማንሳቱ የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

በዚሁ ጉዳይ የፓርቲው ምክር ቤት ባወጣው መረጃ፤ አቶ ጳውሎስ ከሊቀመንበርነታቸው በይፋ እንዲነሱ ከማድረጉ ቀደም ብሎ በጊዜያዊነት አግዷቸው እንደነበር ያመለክታል። ባሳለፍነው ሳምንት በተካሔደው የምክር ቤቱ ስብሰባ ደግሞ አቶ ጳውሎስ ከሊቀመንበርነታቸው እንዲነሱ ውሳኔ አሳልፏል ተብሏል።

የፓርቲው አገራዊ ምክር ቤት በሰሞኑ ስብሰባው የፓርቲውን ሊቀመንበር ስለማገዱ ያስታውቅ እንጂ፤ አቶ ጳውሎስን ማን እንደተካቸው የገለጸው ነገር የለም። (ኢዛ)

በ9.4 ቢሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ላይ ክስ ሊመሠረት ነው

ከ9.4 ቢሊዮን ብር በላይ የሙስና ወንጀል ላይ ክስ ለመመሥረት የኦዲት ሪፖርት እየተጠበቀ መኾኑን የፌዴራል ፖሊስ ያስታወቀው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ የተፈጸመውን ይህንን ከፍተኛ ምዝበራ በመመርመር የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እየሠራ ስለመኾኑ የኮሚሽነሩ ምክትል ኮምሽነር አስታውቀዋል። በዚህ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር እያዋለ መኾኑን አስታውቀዋል።

በመንግሥት ተቋማት ላይ እየተደረገ ካለ ምዝበራ ጋር በተያያዘ በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጸመው ምዝበራ ተገልጿል። ኮምሽኑ ባደረገው ምርመራ በትምህርት ሚኒስቴር ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ ዝርፊያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ እንደተመሠረተ ተገልጿል። (ኢዛ)

እንቢተኞቹ ባለሥልጣናት በፖሊስ ሊጠየቁ ነው

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተደጋጋሚ ሲቀርቡ ከነበሩ መረጃዎች አንዱ፤ አንዳንድ ባለሥልጣናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚቀርብላቸውን ጥያቄ አልቀበል አሉኝ የሚል ነው። ሀብትና ንብረታቸውን ያላስመዘገቡ 100 የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መኾናቸውን አመልክቷል።

እነዚህ በሕግ የተቀመጠን ድንጋጌ በመፃረር ሀብትና ንብረታቸውን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ባለመኾናቸው፤ ኮምሽኑ አስፈላጊው የሕግ ማጣራት እንዲደረግባቸው ስም ዝርዝርራቸውን ለፌዴራል ፖሊስ እንዲተላለፍ አድርጓል።

ኮሚሽኑ እነዚህን እንቢተኛ ባለሥልጣናት 1000 ብር እየተቀጡ ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ድረስ ጊዜ ገደብ አስቀምጦ የነበረ ቢኾንም፤ ይህ ባለመፈጸሙ ጉዳዩን ለፖሊስ ለማስታወቅ ተገዷል።

የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ተጠቅመው ሀብትና ንብረታቸውን ያላስመዘገቡ ናቸው የተባሉት 180 የሚኾኑ በፌደራልና አዲስ አበባ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው። ከ180 የሥራ ኃላፊዎች ውስጥ 80 የሚኾኑት የሥራ ኃላፊዎች እየተቀጡ ሀብትና ንብረታቸውን ማስመዝገብ መቻላቸውን ኮምሽኑ አስታውቋ።

ቀሪዎች 100 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ባለማስመዝገባቸው አስፈላጊው የሕግ ማጣራት እንዲደረግባቸው ለፌደራል ፖሊስ ስም ዝርዝራቸው ተላልፏል። (ኢዛ)

ረሃብ በአንድ ጀምበር

ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የተፈራረቁባት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ደግሞ የበረሃ አንበጣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ማሳ ዶግ አመድ እያደረገ ነው። በተለይ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ሳምንታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አንበጣ መንጋ ያደረሰው ጉዳት ከዚህ ቀደም ከታየው ሁሉ የከፋ መኾኑን አመልክቷል። የአንበጣ መንጋው ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በኾነው በሰሜን ወሎ ዞን ብቻ ከ286 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች አስቸኳይ እርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል።

ይህ የኾነው ደግሞ የበረሃ አንበጣ የደረሰ ሰብላቸውንና የከብት መኗቸውን ጭምር በማውደሙ ነው።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ማጭዳቸውን አስተካክለው ለአጨዳ በተዘጋጁበት ወቅት፤ አንበጣው ቀድሞ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች አንዲት ፍሬ ጐተራቸው እንዳይከቱ አድርጓል። እንዲህ ያለው አሳዛኝ ገጠመኝ ከደረሰባቸው ወረዳዎች ውስጥ በራያ ቆቦ አንዱ ነው። በዚህ ወረዳ በ15 ቀበሌዎች አንበጣው 16,900 ሔክታር ላይ የነበረ ሰብል ሲያወድም፤ በ30 ሔክታር መኖ ላይ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ገልጿል። በራያ ቆቦ ወረዳ እንደደረሰው ውድመት ሁሉ በሌሎች የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የትግራይ፣ የሐረሪና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ የአርሶ አደሮች ማሳ በአንበጣው ተበልቷል።

በዚህ በደረሰ ሰብል ላይ ተስፋ ያደረጉ የእነዚህ አርሶ አደሮች ቁጥር መንጋውን መቆጣጠር ካልተቻለ በመቶ ሺህ አርሶ አደሮች ላይ የረደሰው ጥፋት ውሎ አድሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐች በዚሁ የአንበጣ መንጋ ምክንያት እጃቸውን ለልመና እንዲዘረጉ ያደርጋል የሚል ሥጋት አሳድሯል። ችግሩን የበለጠ አስከፊ ያደረገው ደግሞ፤ የደረሰ ሰብላቸውን ያጡ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ዛሬ እንኳን የሚልሱት የሚቀምሱት የሌላቸው በመኾኑ ገና ከአሁኑ የእርዳታ ያለህ ማለታቸው ነው።

መንግሥት አውሮፕላን ተከራይቶ መንጋውን ለማጥፋት እየሞከረ ሲሆን፣ አብዛኛው አርሶ አደር ግን እስካሁን በባህላዊ መንገድ ለማባረር አልቦዘነም። ቀድሞ ምርታቸውን ያጡት ግን የሌሎችን እገዛ እየጠበቁ ነው።

አንበጣው አሁን እየተደረገ ባለው ጥረት ቢጠፋ እንኳን፤ የደረሰው ጥፋት ብዙዎችን ባዶ እጅ ያስቀረ በመኾኑ፤ በመንግሥት ደረጃም ኾነ እንደ ሕዝብ እነዚህ ወገኖች ጋር መድረስ የግድ መኾኑን የሚያመለክት ኾኗል። ድርቅ ሳይኖር ረሃብ የፈጠረው የአንበጣ መንጋ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ቀድሞ ባለመዘጋጀትና የቅንጅት ጉድለት ጉዳቱን ማባሱ ግን የሁሉም ቁጭት ነው። አሁን ባለው ደረጃ መንግሥት ወደ አሥር የሚኾኑ አውሮፕላኖችን በመከራየት ኬሚካል እየረጨ እንደሚገኝና መርጨቱንም እንደሚቀጥል የገለጸ ቢኾንም፤ ችግሩ ባለበት በሙሉ እየደረሰ መድረስ አልቻለም።

ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልል መንግሥታትና ሌሎች አካላት መንጋውን ለማባረር ባህላዊ በኾነ መንገድ ጥረት እያደጉ ነው። ችግሩ አሳሳቢ ነውና የመከላከያ ሠራዊት ጭምር የትግራይ ክልል ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር በመኾን የአንበጣ መንጋን በማባረር ሥራ ውስጥ መግባቱ የችግሩን አስከፊነት አሳይቷል።

ለመሰብሰብ የደረሰ ሰብል ላይ የደረሰው ውድመት እንዲህ በቀላሉ ስለማይታይ፤ በአገር ደረጃ በምርት ዘመኑ ይጠበቅ የነበረውን ያህል ምርት እንዳይገኝ ስለሚያደርግ የምርት እጥረት ይኖራል ተብሎ ተሰግቷል። (ኢዛ)

ማፍያ መሰል እንቅስቃሴ በወላይታ

በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን መስማት እንግዳ ባይኾንም፤ ባሳለፍነው ሳምንት የተሰማው አንድ ዜና ግን በሕገወጥ ተግባርነቱ የተለየ ሊባል የሚችል ነው። ይህም በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን ተፈጸመ የተባለው ተግባር ሲሆን፤ ድርጊቱን ከማስጠንቀቂያ ጋር የገለጸው ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ነው።

የፌዴራል ፖሊስ የሦስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ምክትል ኮምሽነር ጌታቸው መንግሥቴ እንደገለጹት፤ በወላይታ ዞን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከተለያዩ የጸጥታ ተቋማት የተሰናበቱ የጸጥታ ኃይሎች በመደራጀት ተፈጸመ የተባለው ሕገወጥ ተግባር ነው።

ይህ ጉዳይ በብዙዎች አዲስ ክስተት ተደርጐ የታየ ሲሆን፤ የድርጊቱን አፈጻጸም በተመለከተ ምክትል ኮምሽነሩ የሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ያልተለመደና አደገኛ የሚባል መኾኑን ያመለከተ ነው።

ኮምሽነሩ በዞኑ የተፈጸመውን ሕገወጥ ተግባር ሲያብራሩ፤ በሕገ መንግሥቱ ሥልጣንና ኃላፊነት ከተሰጠው የጸጥታ ኃይል በተፃራሪ በወላይታ ዞን ከአራት ሺህ በላይ የሚኾኑ የቀድሞ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ እንዲሁም ከደቡብ ክልል የፖሊስና ልዩ ኃይል የተሰናበቱትን ሁሉ በማሰባሰብና በማደራጀት የዞኑን ጸጥታ እናሰከብራለን እስከማለት ሲንቀሳቀሱ ነበር። በዞኑ ሁለት ሦስት ጊዜ አራት ሺህ የሚኾን ኃይል ሕገወጥ ሰልፎች ስለማድረጋቸው የሚያመለክተው መረጃ፤ በተለይ ዋናውን በሕገ መንግሥቱ ኃላፊነት የተሰጠውን ኃይል በመተካት በከተማው ውስጥ የጸጥታ ተግባር እናስፈጽማለን በማለት ፍጹም ሕገወጥ ተግባር እየተፈጸመ ነው ተብሏል።

ከዚህም ሌላ የተወሰኑ አካላትን በመለየት መኖሪያና ቀለብ በማመቻቸት በተለያዩ አካላት ላይ ተፅእኖ እንዲያሳድሩ፣ እንዲያስፈራሩና ከዚያም ያለፈ እርምጃ እንዲወስዱ በልዩ ሁኔታ የተቀለበ ኃይል የማዘጋጀትም ሥራ እስከ መሥራት መድረሳቸውን ይኸው የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመልክቷል። የእነዚህን አካላት ድርጊት ምክትል ኮምሽነሩ የጋንግስተር ወይም የማፍያ ሥራ የተሠራበት ሁኔታ መስተዋሉንም ጠቅሰዋል።

ይሄ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር መኾኑን በመግለጽ፤ ምንም ኃይል የፖሊስንና የጸጥታውን ኃይል ተክቶ የሚሠራ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ከዚህ በኋላ ተቀባይነት እንደሌለው አስጠንቅቀዋል። በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ አንዳንዶች ስለመያዛቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ በዋናነት ግን ከዚህ በኋላ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ተቀባይነት እንደማይኖረው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!