አሪስ ታታሊስ

ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የአሜሪካው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሁላችንም የቅርብ ትዝታ ነው። የፓርቲ ዕጩነቱን ከማሸነፍ አንስቶ እስከ መጨረሻው የኖቬምበር 4 ምርጫ ድረስ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ የነበረ ምርጫ ነበር። ታዲያ በዚህ ምርጫ ወቅት ነበር አንዲት ኮረዳ ጎልታ የወጣችው። ስሟ አምበር ሊ ይባላል፤ አሁን ሁሉም በቅጽል ስሟ ”ኦባማ ገርል” እያለ ይጠራታል።

 

ይህዝ ወጣት “I got a Crush on Obama” በሚል በሰኔ ወር 2007 እ.ኤ.አ. በለቀቀችው ዜማ እራሷን ማስተዋወቅ ችላ ነበር። ታዲያ ኢትዮጵያውያን ወጉ እንዳይቀርብን ነው መሰለኝ፤ በምርጫ 2002 ዋዜማ አንድ ወደል “ኦባማ ገርል” ልናይ ችለናል - ሠሎሞን ተካልኝ። መቼም ሁለቱን በድፍረት ሳመሳስል በአንድ ተስፋ ነው - ኦባማ ገርል አማርኛ ስለማትችል ጽሑፌን አንብባ ስብዕናዬን አራከሰው ብላ እንደማትከሰኝ በመተማመን።

 

 

እርግጥ ነው ብዙ ልዩነቶች አሏቸው። ኦባማ ገርል ወጣት ኰረዳ ስትሆን፤ ይሄኛው ጠብደል የሁለት ልጆች አባት ነው። ኦባማ ገርል እየተሽኮረመመች ውበቱን ያደነቀችው ተቃራኒ ጾታዋ የሆነን ሰው ሲሆን፣ የኛው “ኬሻ” የዓይኑን ሽፋን ውበትና የቅንድቡን ማማር ያቀነቀነለት ሰው የሱ ቢጤ አዳም ነው። ሌላውና ዋነኛው ልዩነት “ኦባማ ገርል” ዜማዋን የለቀቀችው ሰዎችን ለማዝናናትና የተካረረው የፖለቲካ ድባብ ላይ ፈገግ የሚያሰኝ እስትንፋስ ለመዝራት ነበር። የኛው “መጋዣ” ሠሎሞን ተካልኝ ግን የምሩን ነው። ያውም ደረቱን ገልብጦ ያለማቅማማት። (ምናልባትም ደግሞ በአትላንታ ከተማ በገባበት ሻይ ቤት ሁሉ “ይሄ ሰጋቱራ መጣ - በሉ ከዚህ እንውጣ!” እስከማለት አንቅረው የተፉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቹን ለማበሳጨት - በእልህ ሊሆን ይችላል።)

 

 

አንባቢዎቼ ለጠንካራ ቃላቶቼ ይቅርታ አድርጉልኝና፤ አንዳንዱ ሰው ከበላዩ ላይ ለባርነት የተመቻቸ ነው ልበል?! እንዲህ ባይሆንማ እንዴት አንድ ግለሰብ ተሯሩጦና ተጋፍቶ የኢሳያስ አፈወርቂን እጅ በተሳለመበት ከናፍርቱ ስለ መለስ ዜናዊ ይዘፍናል? እንደው በጥቅሉ ባርነትን በራሱ ላይ ያወጀና ሁለት/ሦስት መቶ ዓመት ዘግይቶ በግድ ሳይሆን በውድ ወደ አሜሪካ የመጣ ወዶ ተገዥ ካልሆነ በቀር “እኛ ስንገባ መለስ ይወጣል” እያለ ባምባረቀበት ላንቃው እንዴት “ይቀጥል፣ ይቀጥል” እያለ 40 ግዜ ይጮሃል? በበላበት የሚጮህ … ካልሆነ በቀር እንዴት አንድ ሰው “እኔ ከእንግዲህ ሀገሬ ነፃ ሳትወጣ ፍቅርሽ፣ ሽንጥሽ፣ ዳሌሽ እያልኩ አልዘፍንም፣ …” ባለ አንደበቱ “የዓይንህ ውበት … የቅንድብህ ማማር …” እያለ ይዘፍናል? (የሌባ ዓይነ ደረቅ እንዲሉ “እኔ ስለሴት ውበት እንጂ ስለወንድ ውበት አልዘፍንም አላልኩም” ይለን ይሆናል እኮ ሶል - እውነትም ሶል … ስምን መልዓክ ያወጣዋል የሚባለው እኰ አንዳንዴ እውነት አለው።) ይሄ ጤንነት ነው ትላለህ ወገን? እንጃ! እኔ አይመስለኝም! ወይ የሆነ የላላ ቡሎን አለ፤ አሊያ ግለሰቡ እንደ ከርሱ ጭንቅላቱንም የሞላው ስብ ነው።

 

 

ይሄን ያክል ስለ “ኢትዮጵያዊው ኦባማ ገርል” ካልኩኝ በኋላ ግን አንድ ነገር አስረግጬ ማለፍ እፈልጋለሁ። ሠሎሞን ተካልኝ ወደ ወያኔ ጎራ መጠቃለሉ የቆየ ዜና ቢሆንም፤ ለተቃዋሚው ጎራ ግን ትልቅ ዕዳ የቀለለ ያክል የምስራች መሆኑን ዛሬም በሥራዎቹ እራሱ እያረጋገጠልን ነው። “ባቄላ ቀረ … ቀለለ” እንዲሉ ማለት ነው። በሄደ በአጭር ግዜ ይኸው ዕዳ ሆነባቸው። ኢትዮጵያን ለ24 ዓመታት ብቻ አስተዳድሬ እወርዳለሁ እያለ ቡራ ከረዩ የሚለው የሠሎሞን አሳዳሪ የወረደውን ያህል ቢወርድ ስለ ዓይኑ ወበት እንዲዘፈንለት የሚፈልግ አይመስለኝም - ያሳፍራላ! ያሸማቅቃል! (የያኔው ዕጩ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እንኳን በወቅቱ ስለኦባማ ገርል ዘፈን ሲጠየቁ እሳቸውም ልጆቻቸውም ደስ እንዳልተሰኙበት ተናግረው ነበር።) መለስም ደስ የሚለው አይመሰኝም። በዚህ ደስ ካለውማ ነገር ተበላሽቷል - እመቤት አዜብንስ በምን ዓይኑ ቀና ብሎ ሊያያት ነው?! (እኔ ድሮውንም በየአደባባዩ ሲገለማመጡና ሴትዮዋም ከርሱ ጋር በታየች ቁጥር ቆንጠር ቆንጠር ስትል ነገረ ሥራቸው አላማረኝም - እንኳን ይሄ ተጨምሮ …)

 

እርግጥኛ ነኝ መለስ እንዲዘፈንለት የሚፈልገው “ጀግናው”፣ “ቆራጡ”፣ “ብቸኛው”፣ … ምናምን እየተባለ ነው። ሰውም እንዲያስብ የሚፈልገው ስለጀግንነቱና ቆራጥነቱ እንጂ ስለ ዓይኑ ማማር አይመስለኝም። (መቼም ከዛሬ ጀምሮ ሰውየው ለህዝብ ሲታይ ጥቁር መነጽር ቢያደርግ አይገርመኝም - አሽኰረመመው እኰ ጃል!) እንደውም ሆን ተብሎ በተቃዋሚዎች የተላከ ነው የሚመስለው - መለስን ለማሸማቀቅ! ታዲያ ከዚህ በላይ ዕዳ አለ ለወያኔ? ከአንደበቱ ለሚወጣውም ሆነ ወደ አንደበቱ ለሚገባው ልክና መጠን አልባ የሆነ መጋዣ ነው ለወያኔ ያስታቀፍነው። (ሆዱን ከቻሉት ማለት ነው …)

 

እግረ መንገዴን ግን ለተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዲት ነገር ልበል - እባካችሁ ለቅስቀሳና ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚረዷችሁንና የቅስቀሳችሁ ማዕከል አድርጋችሁ የምትመርጧቸውን ሰዎች ስትመለምሉ ጥንቃቄ አድርጉ፤ ደግማችሁ ደጋግማችሁም ጥናት አድርጉ።

 

ረዥም ዕድሜና ጤና ለኢትዮጵያዊው ወደል - “ኦባማ ገርል!”


አሪስ ታታሊስ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ