ክንፉ አሰፋ - ከአምስተርዳም

Teza; A film by Haile Gerimaዳይሬክተር - ኃይሌ ገሪማ

ርዝመት - 140 ደቂቃ

ቋንቋ - አማርኛ

ሰብታይትል - እንግሊዝኛ / ፈረንሳይኛ / ዳች

እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ከሀገሩ በተሰደደው ኢትዮጵያዊ ምሁር በዶ/ር አንበርብር (አሮን አረፈ-ዓይኔ) ሕይወት (narratives) ላይ የተመሰረተ ታሪክ ቀመስ - እውነት ቀመስ - ፊልም ነው ጤዛ።

 

በዚህ ፊልም ዶ/ር አንበርብር በስደት ይኖር ከነበረበት ከምስራቅ ጀርመን ወደ አዛውንት እናቱ ተመልሶ ይመጣል። ከጀርመን ናዚ ርዝራዦች በደረሰበት ክፉኛ ድብደባ አንበርብር አንድ እግሩን አጥቷል። ከብዙ ዓመታት የምዕራቡ ዓለም ቆይታ በኋላ፣ የገጠር ሕይወትን መግፋቱ ለአንበርብር እንደሰመመን ይሆንበታል። አማራጭ ግን አልነበረውም። ወደ ኋላም እየተመለሰ የጥንቱን በትውስታ (flashback) ይቃኛል።

 

በምስልና ድምፅ ጥራት፣ በሙዚቃ አመራረጥና አገባብ፣ በሲኒማቶግራፊና ስክሪን-ፕሌይ እስካሁን ካየናቸው የአፍሪካ ፊልሞች ሁሉ ጤዛ አቻ የሌለው ፊልም ነው ከማለት ውጪ ምንም የምጨምረው የለም።

 

እንደ ፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ኃይሌ ገሪማ አባባል ፊልሙን ለመስራት 14 ዓመታት ፈጅቷል።

 

ፍቅርን፣ ፖለቲካን፣ ኃይማኖትን፣ ባህልን ... ሁሉንም በየፈርጁ ይዳሥሳል። ተመልካቹን፤ ከምስራቅ ጀርመን አዲስ አበባ ... ከአዲስ አበባ ደግሞ ጎንደር አያለ የገጠሩንና የከተሜውን የሕይወት ስንክሳር እያነጻጸረ ያስቃኘናል።

 

Teza; A film by Haile Gerimaአንበርብር በምስራቅ ጀርመን ሕክምና ተምሮ እንደተመለሰ ከአንባገነኑ ስርዓት ጋር ሲጋፈጥ ይታያል። ሰቆቃ በነገሰበት በዚያ ዘመን የስርዓቱ ካድሬዎች ሁለቱን ጓደኞቹን ይገድሉበታል - እሱንም ስቃዩን ያሳዩታል።

 

ዶ/ር አንበርብር ከፖለቲካው ራሱን አርቋል፣ ከአንዳቸው ቡድን ውስጥም የለበትም። ከፖለቲካ ነጻ መሆኑ ግን ከአደጋው አላዳነውም፣ - “መሃል ሰፋሪ በሁለት አቅጣጫ ይመታል” - የሚለው የሟች ጓደኛው ምክርም የገባው አይመስልም።

 

ጓደኞቹ በደርግ ካድሬዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብደበው ከተገደሉ በኋላ፣ ደርግ ዶ/ር አንበርብርን እንደገና ወደ ምስራቅ ጀርመን ይልከዋል። ጀርመን እንደገባም ሰላም አላገኘም፤ እዚያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በሰላይነት ይጠረጠራል። ከሁሉም ደግሞ የቸገረው የጓደኛውን መርዶ ለቤተሰቦቹ ማርዳት ነበር። ከነጭ ወልዶ አዲስ አበባ የተመለሰው ጓደኛው ለዳግም ስደት ሲዘጋጅ በጥይት ተደብደቦ ተገድሏል።

 

ጤዛ፤ ከነጭና ከጥቁር የሚወለዱ ልጆች፣ ነብስ ሲዘሩ የሚደርስባቸውን የስነ-ልቦና ቀውስ ለመዳሰስ ይሞክራል። ከካሜሩንና ከጀርመን የምትወለደውን የካሳንድራን አስቸጋሪና የሰቆቃ ሕይወት በተምሳሌትነት ያሳያል። ራሳቸውን ተራማጆች (progressieve) ነን የሚሉ እነዚህ ሰዎች የልጆቻቸውን ሕይወት ምን ያህል ለመከራ እንደሚድርጉ የሟች ልጅ ምስክር ነው።

 

አንበርብር ይህን መርዶ ለሟች ልጅና ለጀርመናዊት እናቱ ለመንገር በመቸገር እያመነታ ሳለ ነው በዘረኞች ተደብደቦና አንድ እግሩን አጥቶ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው።

 

 

Teza; A film by Haile Gerima
 

 

ወደሀገሩ ሲመለስ ከመጻሕፍቶች በቀር ምንም የያዘው ነገር የለም። የተወለደባት መንደር ሲገባ ያገኘው የሙሶሎኒን ኃውልት በቻ ነው። ለማስታወሻ የቀረ ሌላ አንዳችም አልነበረም። ከረጅም ዓመት የውጭ ቆይታ በኋላ የገጠሩን ሕይወት ለመልመድ ባይቸግረውም፤ ሰው ሰራሹ ችግር አዲስ ይሆንበታል፣ የማያልቀው ጦርነትና የጦርነት ወሬ፣ ካድረዎቹ ወጣቱን ሲያሳደዱና ሲገድሉ ... በራሱም ተስፋ ይቆጥርጣል።

 

ፊልሙ ባህላችን፣ እምነታችንና ማኅበራዊ ሕይወታችን - በተለይ በገጠሩ አካባቢ -በእያንዳንዳችን ኑሮና ሕይወት ላይ፣ ምን ያህል ተጽእኖ እንዳለውም ያሳየናል። ዶ/ር አንበርብር በሁኔታዎች ተደናግሮ፣ ገራ ገብቶትና ፈዞ፣ የተመለከቱት የአካባቢው ነዋሪዎች ችግሩን ሊረዱለት አልቻሉም። መረበሹንና መፍዘዙን ያዩ ሁሉ ይልቁንም በላዩ ላይ አንዳች ነገር ሰፍሯል ይሉ ጀመር። ወደ ጸበልም ሄዶ እንዲጠመቅ ተገደደ። ቀሳውስቱም ጸበል እየረጩ በዶ/ር አንበርብር ላይ ያለውን ርኩስ መንፈስ ገሰጹት።

 

አንበርብር የደህና ቤተሰብ የሆነችን ኮረዳ እንዲያገባ ቢጠየቅም ቀልቡ ግን ያረፈው በቤት ሠራተኛቸው - በአዛሉ ላይ ነበር። አዛሉና አንበርብር ተዋደዱ ... ለዚህም ከፈሉበት።

 

አዛሉ በዶ/ር አንበርብር እናጥ ቤት ተጠልላ አዛውንትዋን እያገዘች የምትኖር ውብ እመበለት ናት። ዶ/ር አንበርብርን በጀልባ እየቀዘፈች የግሌ ወዳለችው ደሴት ትወስደውና - ከደሴቱ ያለችን አንዲት ግማሽ ጎንዋ የሞተ - ግማሽ ጎንዋ ደግሞ ሕይወት ያላት ዛፍ ጋር ሕይወትዋን እያመሳሰለች ትነግረዋለች። አዛሉ ከዶ/ር አንበርብር ጋር ፍቅር መጀመርዋን የሰማ ወግ አጥባቂው የአካባቢው ህዝብ ዝም አላለም። በመንደሩ ነውር እንደሰራችም ፈረዱባት።

 

በመጨረሻ አዛሉም ትሰደዳለች - ወጣቶች ከአፈሳ ሸሽተው ወደሚደበቁበት ዋሻ። እዚያው ከዶ/ር አንበርብር የጸነሰችውን ወንድ ልጅ ትወልዳለች። ስሙንም ተስፋዬ ብለውታል።

 

Teza; A film by Haile Gerimaየተስፋዬ ተስፋ ግን አሁንም የጨለመ ነው የሚመስለው። የደርግን ኮምኒዝም በአልባንያው ኮምኒዝም ለመተካት በየጫካው ህዝቡን እየሰበኩ ሎሎች ብቅ እያሉ እንደሆነም ፊልሙ ጠቆም ያደርጋል። እዚህ ላይ ያሁኖቹን ኮሚኒስቶች ነካ የሚያደርጋቸው።

 

አንበርብር በስደት ላይ ተሰቃይቷል፣ ተቀጥቅጧል፣ እግሩንም አጥቷል። ይህ በኔ ላይ ለምን ሆነ ብሎ አይጨነቅም። ከዚህ በላይ የሚያስጨንቀው፣ በሀገሩ ወገን - ወገኑን ሲያሳደድ - እያሳደደም ሲገድለው ማየቱ ነው።

 

ፊልሙን የሚመለከቱ ብዙዎች ያለቅሱ ነበር። አንዳንዶች በትዝታ ባህር ውስጥ ተዘፍቀው በህሊናቸው ለዓመታት ወደ ኋላ ሲጓዙና ያለፉበትን ሕይወት በህሊናቸው ሲቃኙ አስተዋልኩ። በተለይ በስደት ላይ ያለነው ኢትዮጵያውያን፣ እያንዳንዳችንን በፊልሙ ወስጥ እናገኛለን።

 

የፊልሙ ዲያሬክተር በፊልም ኢንዱስትሪ ስሙ የገነነ ይሁን እንጂ በገጠር አካባቢ የተቀረጹት የፊልሙ ተዋንያን - እንኳን የፊልም ሞያ ሊማሩ - ፊልም አይተው የሚያውቁ አይመስለኝም። ደራሲ የፈጠራቸው የጥበብ ሰዎችም አይደሉም። ቀሳወስቱ፣ አባወራው፣ ባልቴቷና፣ ወጣቶቹ ያሳለፉትን እውነታና የለት-ተዕለት ኑሯቸውን ሲኖሩ ነው ካሜራው ይቀርጻቸው የነበረው። የገጠሬው ወግ፣ የአንጋገር ለዛና ትወና (አክቲንግ) ... እንደወረደ መሆኑ ታሪኩም ምንም ያልተቀየጠ እውነታ ... ለፊልሙ ውበትን ችሮታል። የአዛሉ ዜማዎችም መንፈስን የሚያስደስቱ፣ ትዝታን የሚቀሰቅሱ ትርጉም ያላቸው የሙዚቃ ቃናዎች ናቸው።

 

የቀይ ሽብርን ይልቁንም የኢትዮጵያን የአስርት-ዓመታት ሰቆቃ በደንብ ላላጤነው፣ ጤዛ ፊልም ሲጀምር በእንካ-ሰላምቲያ ነው ሲጨርም ግን በእንቆቅልሽ። በዛ ውስጥ ላለፉት ግን በትዝታ ለዓመታት ወደ ኋላ ይዞ ይጨልጣል።

 

ፊልሙን ቀድሞ ላልተመለከተው በፊልሙና በፊልሙ ዳይሬክተር ይወርድ የነበረው የወያኔ ቴለቭዥን ውርጅብኝ ግራ ሊያጋባ ይችላል። እነዚህ ጋዜጠኞች ኃይሌ ገሪማን ከፊልሙ ዋና ተዋናይ ከዶ/ር አንበርብር ጋርም ሳይቀር እያመሳሰሉ ነበር በጤዛና በኃይሌ ላይ የዘመቱት።

 

ይህ በሆነ በሣምንቱ ግን ከወደ ቡርኪና-ፋሶ የወያኔን ጋዜጠኞች የሚያሸማቅቅ አንድ ዜና ተሰማ፣ ጤዛ የፌስፓኮ 21ኛው የፓን አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ኦስካር ተሸላሚ ነው ተባለ። የአውሮፓው የልማት ሚኒስትር ሉዊ ሚሼል ሳይቀሩ ጤዛ የኦስካር ተሸላሚ በመሆኑ የደስታ መግለጫቸውን አሰሙ። ... ይገባዋል! በርግጥ ጤዛ ሁሉም ሰው ማየት የሚገባው ድንቅ ፊልም ነው።


ክንፉ አሰፋ - ከአምስተርዳም

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!