Libb Yimar by Abera Lemma, ልብ ይማር - አበራ ለማ

አየሁት ደግ ልብህን፣

እያየ እማያየውን ውስጥህን፣

አየሁት ደግ ልብህን፣

ተትርፉ መስጠት ያልቻለውን፣

አየሁት ደግ ልብህን፣

የንፉግ ንፉግ እልቅናህን

... ደሞም ደሞም ...

በጎ በጎ መርገጫህን፤

 

አየሁት ያን ውርስህን፣

ያያት አያት ቅሪትህን፤

የተራበ እንዳይበላ፣

የተጠማ እንዳይጠጣ

የታወከ እንዳያርፍ፣

የታሰረ እንዳይወጣ

ወጥመድ መረብ ማገጃህን፣

አየሁት ያን ውስጥህን፤

 

አየሁት ደግ ልብህን፣

ጨካኝ ጥርሶቹን ነክሶ

በክፋት ጭምብል ጨምብሶ፣

ባሉባልታ መንበር ነግሦ፤

አየሁህ ወዳጄ፣

እያለህ የለሁም ብለህ

እያየህ ላታየኝ፣

ከምቅ ጓዳ ተጨንቡለህ፤

ወገን ሞረሽ ሲልህ፣

ጆሮህን ተለጉመህ

አየሁህ ስታየኝ፣

ተመንገዴ ልታነቅፈኝ፤

 

አየሁት ደግ ልብህን፣

እውነትን ማየት ፈግሞ

አየሁት ቋንጂል መስሎ፣

ሳይወደኝ ወዶኝ ታሞ፤

አየሁት የውስጥ ውስጥህን፣

ለቁርጥ ቀን ያኖርኩትን

ሳይኖር ኑሮ፣

ታልኖርበት ያሻሁትን፤

 

አየሁት ያን ልብህን፣

አጋም ተቀጋ አሽቶ

እንደር’ደ ምድር ሲንቀረቀብ፣

ቁልቁል ምስለ’ኔን ወግቶ፤

አየሁት አዞኛ ሲያለቅስ

ሱናሚኛ ሲርመሰመስ ...

እግዚኦ ልብ ይማር! ...

የልብ አምላክ የ’ጅ አይነፍግ

ታጎበር ቢሸሸጉ፣

ገልጦ መውጋቱን አይገድፍ ...


አበራ ለማ

የገጣሚው የግርጌ ማስታወሻ፦

በግጥም ጥበብ ውስጥ እንደጌጠኛ ፈርጥ ከሚታዩ ግባቶች መካከል ዘይቤ (FIGURATIVE LANGUAGE) አንዱ ነው። ካንድ አሥርት በላይ ከሚሆኑት ዘይቤዎችም መካከል አያዎ (PARADOX) አንዱ ነው። የማይመስል የሚመስለውን እውነት የምናመስልበት ማለፊያ መንገድ ነው። የዚህ ዘይቤ ብርቱ ፀባይ ምርምርን መጋበዙና የራስንም ውስጠት ደህና አድርጎ ማያ መስታወት መሆኑ ነው። አዎን እራስን እንደማየትና እንደማወቅ ደግሞ ማለፊያ ብርታት የለም። እናም መጻዒውን ሰንበት እየራሳችንን እያየን ከዘይቤው ጋር እናንጎራጉር ዘንድ እንሆኝ ... ብያለሁ። (ዓርብ መጋቢት 3 ቀን 2002 ዓ.ም.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ