ሙያ ሲጋለጥ! (መልካም አዲስ ዓመት)

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ውዷ ባለቤቴ - እመይቴ ስንዱ

አበደች ለየላት - አለሽ ሴቱ ወንዱ፤

ዛሬ በአዲስ ዓመት - ዛሬ በበዓሉ

ያቀረብሸው ድግስ - ምስክር ነው አሉ።

 

ባንድነት ማቅረብን - ቀላቅሎ ድግስን

ከትናንት ጀምሮ - ስናየው ሙያሽን

አበደች ነው ያልኩኝ - አወከሽ ጤናሽን።

 

ማ ይሙት! ባንድዬ! እንዲያው በየት አርጎ

በአንድነት ይቀርባል - ጠላ ተልባና እርጎ?

ምን አርገሽ ብትፈጭው - እንዴትስ ተቦክቶ

በርበሬ ከስንዴ - ጤፉ ከቡና ጋር - በአንድ ተዘጋጅቶ

ምን አይነት እንጀራ - ሊጋገር ነው ከቶ

ማን ፊት ነው እሚቀርበው - ይህ የአንች አነባብሮ?

እንጀራም አይመስል - በግዳጅ አንድ ሆኖ።

 

ትናንትም በአንድነት - ዛሬም በአንድ ጋግረሽ

ጤፍን በበርበሬ - መልክ ታሳጫለሽ

ሙያሽ ወፈፌ እንጅ - ጤነኛ አላሰኘሽ!

 

እባክሽ ተማሪ - ሙያ ከጎረቤት

ባለፈው ካየሽው - ከእነማሚቴ ቤት

ጤፉ እንጀራ ቢሆን - ለብቻው ተጋግሮ

በርበሬ ወጥ ቢሆን - ክሽን ብሎ አምሮ

ለብቻው በዓይነቱ - በመልኩ ተሠርቶ

ሙያ እንዲያ ነው እሚያምር - የሚታይ ውበቱ

አንድ ላይ በማብሰል - አያምርም ውጤቱ

አንድነት አንድነት - አትበይ በከንቱ።


ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

መስከረም 2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ