ወይ እዳ ... ወይ ፈተና ...

አበራ ለማ

ዐይኖችህን ባይኖቼ ስምሳቸው

እሻት ምኞትክን ስቆጥር

ሕልሞችህን ስተረትር

አንተዬ ... ልመናህ ባሰኝ

ያልዋልክበትን ትናንት ስትጠይቀኝ

ተዌት አባቴ ላቀብልህ? ...

እባክህ በሌለኝ ... በሌለህ አትምጣብኝ፤

 

ወይ እዳ ...

ወይ ፈተና ...

 

ባሮጌ ትዝታ ዋግምት

ሕመም ሕመሜን እያደመጥኩ

ብርሃን ላጠጠው ተስፋ

በመርፌ ቀዳዳ እያጮለኩ

በችግሬ ችግሬን እየላጨሁ

አንተዬ ... ዐይኖችህን ባይኖቼ እስላለሁ፤

ተዛሬው ውስጥህ፣ የትናንት አንተን እሻለሁ።

 

ወይ እዳ ...

ወይ ፈተና ...

 

ታልበላሁት ብድርህ ልክስህ

ተሃች ሃች ሃች ወርጄ

ሽቅብ ጉዞን ጀምሬያለሁ ...

ግና ... ያልሰጠኸኝን ትናንት ስትጠይቀኝ

ተዌት አባቴ ላቀብልህ? ...

እባክህ በሌለኝ ... በሌለህ አትምጣብኝ፤

 

ወይ እዳ ...

ወይ ፈተና ...

 

ሽቅብ መውጣት ...

እንደ መውረድ ባይደላም

በርከን እርከኑ ተጓደድ፤

ዐይኖችህ ጨርሰው ...

እንዳሮጌ ጨርቅ ቢነትቡም

አንተዬ ... ቀሪህ ገና አልተነካም

ግዳይ ከመጣል አትቦዝን፤

ግና ... ያልዋልክበትን ትናንት ስትጠይቀኝ

ተዌት አባቴ ላቀብልህ? ...

እባክህ በሌለኝ ... በሌለህ አትምጣብኝ፤

 

ወይ እዳ ...

ወይ ፈተና ...

አቱንብኝ።


አበራ ለማ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ኅዳር 9 ቀን 2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ