አልጠብቅም ሞትን ተኝቼ ባልጋዬ ፤

እኔው እሄዳልለሁ ፈረሴን ቼ ! ብዬ ፤

በ’ንባ አልታጠብም ቁጭ ብዬ አላለቅስም ፤

ጉልበቴን አጥፌ አልንበረከክም ፤

አልጠብቅም እሱን ወደኔ እስቲመጣ ፤

እኔው እሄዳለሁ ወደሱ እንዳይመጣ ፤

ኩራቴን ይረዳው ድፍረቴን ይወቀው ፤

ተጋድሜ አልሞትም ቆሜነው እምሞተው !!


አልፈልግም ዋሻ የምደበቅበት ፤

አያሻኝም ጢሻ የምሸሸግበት ፤

አልሰብርም አንገቴን አላዞርም ፊቴን ፤

አይዝልም ጉልበቴ አላጥፈውም ክንዴን ፤

እጠብቀዋለሁ ደረቴን ነፍቼ ፤

በኩራት በድፍረት ጋሻዬን መክቼ ፤

አልንበረከክም ቆሜነው እምሞተው ፤

የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!

አልጠብቅም ሞትን ማታ በጨለማ ፤


እንዲወስደኝ ብዬ ሰው ሳያይ ሳይሰማ ፤

አለምንም ከቶ ዛሬን እንዲተወኝ ፤

ዘግይቶ እንዲመጣ ዕድሜ እንዲለግሰኝ ፤

ያልጋ ቁራኛ አርጎ እያጨማለቀ፤

ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ እያመናጨቀ ::

ጭራሹን !

እጠብቀዋለሁ በጠራራ ፀሐይ ፤

መሃላዬ ይሁን ቃል ለምድር ለሰማይ ፤

ቆሜነው እምሞተው እንደ ክርስቶስ

ዳግም ድል አድርጌ እስክነሳ ድረስ ::


ይጥልልኝ ብዬ ትርፍራፊ እድሜ ፤

አልጠብቅም ሞትን እኔ ተጋድሜ ፤

እሄዳለሁ እኔ ወደሱ እንዳይመጣ ፤

ግንባሬን አላጥፍም የመጣው ቢመጣ ፤

ተኝቼ አልጠብቅም ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ ፤

እኔው እሄዳለሁ በቁሜ እንዲያገኘኝ ፤

ለመኖር ጓጉቼ አልንበረከክም ፤

ዛሬን ተወኝ ብዬ አልለማመጥም ፤

አልንበረከክም ቆሜነው እምሞተው ፤

የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!

አንድ ቀን

ለወጣት መምህር የኔሰው ገብሬ :

እንዲሁም ፤

የአገራቸውን ውድቀት፤ የወገናቸውን ድቀት፤ እንቢ በማለት : ለእኩልነት፤ ለአንድነት፤ ለዲሞክራሲና ለፍትህ መከበር በመታገል ለወደቁ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በሙሉ መታሰቢያ ትሁንልኝ ::

To Remember the young Ethiopian Teacher Yenesew Gebré and  Ethiopian Martyrs of June and November 2005.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ