የሚያልፍ ይለፍ እንጅ! ….

ፊልጶስ

የሰው - ሰውነቴ፣ የ’ኔ ማንነቴ

የልቤ ትርታ - የሰራ አከላቴ፤

መጠሪያ ቋንቋዬ፣ ጌጤና ውበቴ

ኢትዮጵያ ነሽ እኮ ክብርና ሕይወቴ። …

 

ባልዋልኩበት ውሏል፣ ብለው ቢከሱኝም

ያለህግ - ያለፍርድ ቢወነጅሉኝም፤

ወህኒ-ቤት - ከርቸሌ፣ ቢያወርዱኝ ዘብጥያ

ቢገርፉ - ቢወግሩኝ፣ ከምሽት እስከ አጥቢያ፤

እኔ እንደሁ ወይ ፍንክች! የመጣው ቢመጣ

ከበጎ አላማዬ፣ ከእውነቱ ላልወጣ።

 

ከሰው ንብረት አልፈው ደም የሚጠማቸው

አሳር ቢያሳዩኝም በእኩይ ምግባራቸው፤

የህይወት ጉዞዬን ቢያደርጉት መራራ

በላዬ ቢከመር፣ ሀዘን - ከመከራ፤

በድን አያደርጉት ቆራጥ ህሊናዬን

አያቆሽሹትም ንፁህ - ብሩህ ልቤን።

 

ሀገር - ወገን ማለት ጠፍቶ ከውስጣቸው

ቢያሳክራቸው የስልጣን ጥማቸው፤

ምንም ምን ቢያደርጉኝ፣ ምንም ምን ብሆን

እኔ እንደሁ ወይ ፍንክች!.... አልሰጥም እጄን።

ተስፋና ምኞቴን ከግብ ሳላደርስ

የሚያግደኝ የለም አፈር እስክለብስ።

 

የሰው - ሰውነቴ፣ የ’ኔ ማንነቴ

የልቤ ትርታ - የሰራ አከላቴ

መጠሪያ ቋንቋዬ፣ ጌጤና ውበቴ

ኢትዮጵያ ነሽ እኮ ክብርና ህይወቴ። …

 

ልታረዝ - ልጠማ፣ ልዋረድ በዓለም ላይ

እንቅልፌ ይሁን መከራና ስቃይ፤

ልታደን እንደ አውሬ፣ ልሁን ምፃአተኛ

ልግረፍ - ልታሰር እንደ ወንጀለኛ፤

እጅ - እግሬ ይቸንከር፣ ይመታ ‘በካስማ’

ልጎተት በመሬት፣ እኔስ ልቁሰል ልድማ፤

ልወርወር ጫካ ውስጥ፣ ጥቅጥቅ ካለ ደን

የአውሬ መጫዎቻ፣ ምግባቸው ልሁን።

 

ደሜ እንደጎርፍ ውሀ ይውረድ እንደ ጅረት

ስጋዬም ይዘልዘል፣ ይጠበስ በእሳት፤

ወይም ካሰፈለገ፣ ቆዳዬ ይገፈፍ ስልቻ ይሰፋ

አጥንቴም ይፈጭ አንደ አመድ ይደፋ፤

ገሀነም - ሲኦል ትሁን ምድር ለ’ኔ ሕይወት

ብቻ … … …

ብቻ … አልይ ውድቀትሽን፣ እኔ ያ’ችን ውርደት።

የሚያልፍ ይለፍ እንጂ፣ አ’ች አትለፊብኝ

ዛሬም … ለዘላዓለም … ኢትዮጵያ ኑሪልኝ!!!

------//------


ፊልጶስ / This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. /

 

መታሰቢያነቱ፤ ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለሰው ለጆች እኩልነትና ለሀገራቸው ለዕልናና ክብር ብለው በእሥር ቤት ለሚማቅቁና በትግል ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ