አንዱዓለም በቀለ (ከስዊስ)
ግጥሙን በድምፅ ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!


ግሪኮች ናይሎስ ብለው ቢሰይሙህ፣
አኒል አኒል ... ብሎ ዐረብ ቢያሞካሽህ፣
ኢታሩ "ታላቅ ወንዝ" ... ሃፒ ሃፒ አሉህ፣
ደስታ ቢያገኙብህ ...
ጥንት ግብጻዊያን ... ሕይወት ቢዘሩብህ፤
በሰላሳ ስሞች ... ቢጠሩ ቢያጅቡህ፣
ዓባይ የኛን ዓባይ ... እኛ መች አጣንህ፤
ከላይ ከከፍታ ... ቁልቁል ተወርውረህ፣
ከአለት ተጋጭተህ ... ጢስ ሆነህ ተነስተህ፣
በፏፏቴህ ዜማ ... ልዩ ድምፅ አውጥተህ፣
ንገራቸው እስቲ ... ከረቂቅ ሚስጥርህ።

 

የኤደን ትሩፋት ... የፊሾን ተከታይ፣
የነ ኤፍራጥስ ...
የጤግሮስ ወንድም ... የተፈጥሮ ሲሳይ፣
እንዴት ሆኖ ባንተ ... ዛሬ እንለያይ?፣
ዓለም ስትፈጠር ... አብረህ ተፈጥረሃል፣
ሐዋርያት እንኳን ... ከትበውልሃል፣
በቅዱስ መጽሐፍ ... ስምህ ይጠቀሳል፣
የኤደን ስጦታ ... ግዮን ተብለሀል፣
እንኳን እኛ ሰዎች ... ፈጣሪም ያቅሃል፤
እንዴት ሆኖ ታዲያ ...
ዛሬ ስለ ክብርህ ... ሰዎች ይነግሩናል!፣
ሁለት አሥርት ዓመት ... መች ተፈልገሀል!፣
ተው ባክህን ግዮን ... ተው ባክህን ዓባይ፣
እነሱ ላንተ ሟች ... ሌላው አንተን ገዳይ?!
እነሱ አልሚዎች ... ሌላው አንተን በዳይ?!
ተወን እንጂ ግዮን ... እባክህን ዓባይ፣
በቂ ተዘርቶልን ... ጎሪጥ እሚያስተያይ፣
እየቦጠቦጠን የደም ... የዘር ተባይ፣
ደሞ ሁሉም ቀርቶ ... ባንተ ልንለያይ?!

አቤት ያንተ ያለህ! ... ባዋይ በመጀንህ!፣
ምሁራን ልሂቃን ... እንዳልመከሩብህ፣
የቀድሞ አባቶች ... እንዳልደከሙልህ፣
ጭራሽ እንዳልታየህ ... ድሮ እንደሌለህ፣
ከሃያ ዓመት በላይ ... ስትፈለግ ኖረህ፣
... ዛሬ ላይ ተገኝተህ!፣
የልማቶች ሁሉ ... ምሣሌ ተደርገህ፣
ጥፋት መሸፈኛ ... ማዘናጊያ ሆነህ፣
ዕድሜ ማራዘሚያ ... መዳኒት ተደርገህ፣
ሁሉም ተነሳና ... ዓባይ ዓባይ አለህ፤
የማውራት የመፃፍ ... የሃሳብ ነፃነት፣
በሕግ የመዳኘት ... የዲሞክራሲ መብት፣
የድህነት ማብቂያ ... የኢኮኖሚ እድገት፣
አጀብ ምኑ ቅጡ ... መቻሉን ከሰጠህ፣
የችግሮች ሁሉ ... መፍቻ ዘዴ ሆነህ፣
ጦስ ጥንቡሳስ ሁሉ ... ባንተ ተጥሎብህ፣
ከተፍ አልክልና ... ዓባይ ካባ ሆነህ!።

መች ከፋ ነበረ ... ስላንተ መጣሩ፣
ስላንተ ማዜሙ ... ባንተ መፎከሩ፣
ግራ ቢሆን እንጂ ... ቢጣረስ ነገሩ፣
ምሬት ቢበዛ እንጂ ... ሰው በገዛ አገሩ፤
እንዳንተ እንደ ወንዙ ... እንደ ፈሳሽ ጅረት፣
ሰው ሃገሩን ጠልቶ ... ሲጣደፍ ለስደት፣
በየ በረሃው ላይ ... እንደ በግ ሲበለት፣
ባህር ሰምጦ ሲቀር ... ሕይወት እንደዘበት፣
ሴቶች ሲሸቀጡ ... ለዐረብ በረከት፣
ተዋልዶ ተፋቅሮ ... ከተቀመጠበት፣
ማፈናቀል ይቅር ... ይከበር የሰው መብት፣
ከድንጋይ ከብረት ... ከአፈር ከአለት፣
ሥርዓት ይገደብ ... ይሄ ይቅደም ማለት፣
እንዴት ያስፈርጃል ... እንደ ልማት ጠላት?!

ፍጡራን ሲራቡ ... ንፁኀን ሲሞቱ፣
ዜጎች ያለ ጥፋት ... ወህኒ ሲከተቱ፣
መፃፍ ወንጀል ሲሆን ... ሰው በገዛ ጣቱ፣
አትናገር ሲባል ... በገዛ አንደበቱ፣
በመሳቀል እንጂ ... የሁዋላና ፊቱ፣
መቅደም የሚገባው ... የሰው ነፃነቱ፣
ፍጹም ተዘንግቶ ... ተደፍቶ ባናቱ፣
እንዲህ ቢሆን እንጂ ... ነገሮች ቢምታቱ፣
ደሞ የምን ገንዘብ ... ኧረ ምን አባቱ!፣
ይታወቅ የለ እንዴ ... በዓለም እውነቱ፣
የጥቁሮች ኩራት ... ኢትዮጵያዊነቱ፣
ጭራሽ ለሃገሩ ... ለአንዲት እናቱ!?
ለሌላውም ለጋሽ ... ሩህ ሩህ አንጀቱ፣
ለነፃነቱ ሟች ... ይሄ ክንደ ብረቱ፣
ሀገር ያቆየልን ... በደሙ ባጥንቱ፣
አዬ ምነው ጎበዝ! ... ኧረ ባርባራቱ፣
ለቀባሪው ማርዳት!? ... ልክ እንደ ተረቱ!፣

ተወን ባክህ ዓባይ ... እስቲ በፈጠረህ፣
መሸሹ ቀርቶብህ ... አንተም ተሰብስበህ፣
በሰው በረሃ ላይ ... መባከን ቀርቶብህ፣
ሲሳይ ለወገንህ ... መድን ለልጆችህ፣
እንደቃሉ ግዮን ... ያምላክ ፀበል ሆነህ፣
ለሚገዘትብህ ... እንደዚ በስምህ፣
እውነቱን አጥርተህ ... ውሸቱን አጋልጠህ፣
ዲያቢሎሱን ሁሉ ... ፈውሰው አጥምቀህ፣
ህሊና ሥራለት ... ኢትዮጵያዊ አርገህ።

ሚስኪኑንም ... እርዳው፣
እንደዛ በዙሪያህ ... ለተኮለኮለው፣
አንተ አባቱ እያለህ ... ጠኔ ለጠለፈው፣
ከፍሰትህ ጨልፈህ ... አንጀቱን አርጥበው፤
እባክህን ዓባይ ... እባክህን ስማን፣
ከፀበልህ እርጨን ... በጢስህ እጥነን፣
ሁሉን በሚያረገው ... በኤደን ፈጣሪህ፣
አቅፎ ባሳደገህ ... በጣናው አባትህ፣
ባክህ ተለመነን ... ባክህ እሺ በለን፣
በጢስህ እጥነን ... በዳመናህ ጋርደን፣
ከጎረቤት ቡዳ ... ከነገር ጠብቀን፣
ለም አፈሯን ትተህ ... ጠላቷን አጥፋልን፣
ቆሌህን አስቆጣው ... አለኋችሁ በለን፣
ከውስጥም ከውጭም ... ቆልፎ ከያዘን፣
ዲያቢሎስ መጋኛ ... እባክህ ገላግለን፣
... ፈውስ ፀበል ሁነን፣
ኤሎሄ ኤሎሄ ... ዓባይ ፍቅር ስጠን፤
ኤሎሄ ኤሎሄ ... ዓባይ ሠላም ሁነን።


"ግንባታ እሚጀምረው ከታች ከመሠረት ነው! እናም ምንም ክፍያ የሌለውን በተፈጥሮ የተሰጠ የሰው ልጆች ነፃነትን፣ ሰብዓዊ መብትን እና የዜግነት ክብርን መሠረት ያላደረገ የይስሙላ ግንባታ የእንቧይ ካብ ነው።"
አንዱዓለም በቀለ ከስዊዘርላንድ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ