እየተጓዙ ንባብ (ቦጋለ ዳኜ)
ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርኒያ
ረጅም ጎዳና፤
ስንሔድ ባውቶቡስ በመኪና፤
ረጅም በረራ፤
ስንሔድ ባውሮፐላን በጠያራ፤
በምቹ ወንበር በሚሳብ በሚለጠጥ፤
በመንፈላሰስ በመቀመጥ፤
በሚዘረጋ በሚታጠፍ፤
መከዳ ላይ በመደገፍ፤
ይነበባል መጽሐፍ፤
"ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ"፤
የሥልጣኔ ትርፍ።
ወደኛው ታሪክ ስንገባ፤
የሕንደኬው ጃንደረባ፤
ሲጓዝ በሠረገላ፤
ተጠልሎ ባጎበር በጃንጥላ፤
በማለፊያ ወንበር በደልዳላ፤
ዘና ብሎ ተቀምጦ በስተኋላ፤
ሳያገኘው እንቅፋት አሜኬላ፤
ቊሩ፤ ሐሩሩ፤ ውሽንፍሩ ሁላ፤
ያነብብ ነበር እንዳሁኑ፤
እሱም በዘመኑ፤
ሁለት ጉዳይ፤
መተኮስ አንድ ላይ
ሥልጡን እንጂ! ዘመናይ!
ይኼ ሁሉ ቀርቶ፤
የኛ ሰው በንትርክ ተኝቶ
በዚያ ሳቢያ ሥልጣኔ ከኛ ሸሽቶ፤
ሌላ ዘንድ ዳብሮ ሰፍቶ፤
ቆይቶ፤ ቆይቶ፤ ቆይቶ፤ ቆይቶ!
አውሮጳን፤ እስያን፤ አሜሪካን ቃኝቶ፤
ሰው አገኘሁ ብሎ አዲስ ቅኝ ሽቶ፤
ተስተናግዷል ተመልሶ ባዶ ቤት አግኝቶ፤
የጥንት ቤቱ፤ መሆኑን ረስቶ።
ቦጋለ ዳኜ ከካሊፎርኒያ



