ይመቻችሁ ጌቶቼ (አበራ ለማ)
ኩርዳዊ ነኝ ከኢራን - ኢማን አባስ እባላለሁ
በቋንቋዬ እንዳልቀኝ - እንዳልከትብም ሁኛለሁ፤
የኔ ጌቶች ያሻቸውን - እሆን ዘንዳ ቢያስጨንቁኝ
ግዳይ ጣልኩኝ እራሴን - ጭካኔያቸው ቢብሰኝ፤
ያውላችሁ ያሻችሁት - እንዳልሆን እሆን ፍርዳችሁ
አንደበቴን ተቆልፌ - ዓይኖቼን ተለጉሜ
ይመቻችሁ እላለሁ - ጆሮቼን አስከርችሜ፤
ብዕሬን ወርውሬ - ቀለሙን ደፍቼ
ፍረዱኝ እላለሁ - እናንት ወገኖቼ!
አበራ ለማ
(ለምሥራቅ ኩርድ ባለቅኔው ለኢማን አባስ አመጽ መታሰቢያ)