ሰማሁ! እናቴ ሰማሁ! (ወለላዬ ከስዊድን)
አጉልተው ለመመልከት እዚህ ይጫኑ!

(ወለላዬ ከስዊድን)

ጠይም ፊትሽ መጥቆሩን፣

ትንፋሽሽ፣ ጥሎሽ መሸሹን፣

የፊትሽ ወዝ ማጠፈፉን

አካል ቁመናሽ መርገፉን

ሰማሁ እናቴ ሰማሁ፣

አይቻል የለ ችያለሁ።

በዝምታ ተውበሽ

በሰው ሸክም ተሞሽረሽ

በኡኡታ ...

በዋይታ ...

መሸኘትሽን ሰማሁት

አይቻል የለ ቻል አ'ረኩት

የሆንሽውን ሳልጠይቅሽ ሳትነግሪኝ

ጎንሽ ሆኜ ሳላዋይሽ ሳታዋይኝ

ሞተሽ ቀብርሽ ሳልቆምልሽ ከቀረሁኝ

እናቴ ሆይ! ፍረጂልኝ ፍረጂብኝ

ምን ላድረገው? ምን ታረጊኝ?

 

ስደት ዶጋ አመድ ያድርግህ!

እንደ እናቴ ትንፋሽ ይንሳህ!

ምንስ ብትነፍግ ብታሳጣ

ካገር ውጪ ብታወጣ

የናቴን! የናቴን እንኳን

የመጨረሻ ሽኝቷን

እንዴት! ከዓይኔ ታርቅ

እንዴት! ከእግሬ ትነጥቅ

አዎን! ግድየለም!

ሞት መቼም ለኛ አዲስ አይደለም

ግን! እናትን ያህል ነገር

እንዴት ታሳጣኝ ቀብር?

 

ምነው እናቴ አንችስ!

ናፍቆትሽን እስክወጣ

ከሄድኩበት እስክመጣ

ዓይንሽ ከዓይኔ እስኪተያይ

ሞትሽን እንደ ተዋነይ*

ገትረሽው በራፍሽ ላይ

ምነው ነበር በጠበቅሽኝ!

እስከማይሽ በቆየሽኝ

 

አንቺስ! ምነው አገሬ

ውለታትሽን ደፍሬ

እርግፍ አድርጌሽ ስወጣ

እናቴን ጭምር እንደማጣ

እያወቅሽው እያየሽኝ

በዝምታ ሸኝተሽኝ

ለትዝብትሽ ምነው ጣልሽኝ

 

የአገሬ ጥቁር ምድር

ፍረጅልኝ! ይሄን ነገር

ልብ በይው፣ እስቲ ፀሐይ

ከናቴ ጋር ሳንተያይ

ተገናኝተን ሳንወያይ

ሞት ሊነጥል ይችላል ወይ?

 

አንተ! ጨካኝ ሞት ራስህ

አፈር ግባ! ድብን ያርግህ!

አንድ እናቴን ሰርቀህ ስትሄድ

ያንጠልጥልህ ሞት ከመንገድ

ብቻ ... ብቻ ሞትስ ምን ያድርገኝ

ስንት ዘመን ይጠብቀኝ

ምን ታደርጊ አንቺ ራስሽ

ልታገኚኝ በጸሎትሽ

ብዙ ለፋሽ ብዙ አነባሽ

መጨረሻ ደክሞሽ አረፍሽ

 

ይልቅስ እናት ዓለም

ባይጠቅምሽም

ባይጠቅመኝም

ያየሁትን ልንገርሽ ሕልም

በአገራችን፣ በግቢያችን ገብቶ ነፋስ

ሕዝብ አገሩን ሲያተራምስ

ጉልበት አጥተሽ

አቅም አንሶሽ ...

ነፋስ መኻል ስትዳክሪ

ድምፅ አውጥተሽ ስትጣሪ

እየሰማሁ እያየሁኝ

ዝም ብዬሽ ትቼሽ ሄድኩኝ

ይሄን አየሁ ይሄውልሽ

ቀደም ብዬ ከመሞትሽ

ሕልም ... እልም ...

ብዬ ብልም

ያንቺ ነገር ሕልም አልሆነም

 

ይሄው! ጠይም ፊትሽ መጥቆሩን

ትንፋሽሽ ጥሎሽ መሸሹን

የፊትሽ ወዝ ማጠፈፉን

አካል ቁመናሽ መርገፉን

ሰማሁ እናቴ ሰማሁ

አይቻል የለ ችያለሁ።


መታሰቢያነቱ፡- ለእናቴና በስደት ዓለም ሆነው እናት፣ አባት ወይም የሚወዱት ዘመድ በሞት ለተለያቸው ጭምር ይሁን!

*ተዋነይ፦ የሰው ስም ነው። ተዋነይ ሞትን ለሰባት ዓመት በራፉ ላይ ያቆመ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋና ባለቅኔ ነበር።

ሰማሁ! እናቴ ሰማሁ! (ወለላዬ ከስዊድን)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ