አድዋ (ወለላዬ)
ወለላዬ ከስዊድን
አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምሥራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ... ታሪክሽ ታወቀ
የድል ብሥራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ... አንጸባረቀ
የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ሻማ
መሆንሽ ተወራ አገር ለአገር ተሰማ
የአበው ተጋድሎ የጀግንነት ደም
ታሪኩ ተወሳ በከንቱ ፈሶ አልቀረም
የአባ ዳኘው መድፍ አሁንም አገሳ መልሶ
የጣይቱ ስም ተጠራ ተወደሰ አባ ነፍሶ
እንደገና አስተጋባ የአድዋ ድል
ገኖ ታየ ተደነቀ አባ መቻል
ሀብተ ጊዮርጊስ አባ መላ
ሥራው በድጋሚ ጎላ።
አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምሥራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ... ታሪክሽ ታወቀ
የድል ብሥራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ... አንጸባረቀ
ራስ አሉላ አባ ነጋ
በከፈለው የደም ዋጋ
ስሙ ዛሬ ሲነሳ
የባልቻ የገበየሁ አብሮ ሲወሳ
እነ አባተ ቧያለው
እነ ቃኘው እነ ውቃው
ከተኙበት ቀና ብለው
መቃብሩን ፈነቃቅለው
የአድዋን ድል አበሰሩ
ጀግንነትን አስተማሩ
አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምሥራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ... ታሪክሽ ታወቀ
የድል ብሥራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ... አንጸባረቀ
የአበው ተጋድሎ ያፈሰሱት ደም
ተወሳ ተነገረ ከንቱ አልቀረም
የምኒልክ መድፍ አሁንም አገሳ መልሶ
የጣይቱ ስም ተጠራ ተወደሰ አባ ነፍሶ
ትውልዱም የአባቶቹን ድል በማደስ
የጀግንነት ሥራቸውን እያነሳ በማወደስ
ለመጪውም ጊዜ እንዲሻገር
ኢትዮጵያ በታሪኳ እንድትከበር
የድርሻውን በተግባር አስመሰከረ
ይሄው የድል ቀኑን በአንድነት አከበረ
አድዋ! በድልሽ የተገኘ ምሥራች
ጊዜው ረዘመ ብሎ ሳይሰለች
ዕድሜው በዕድሜ ላይ እየጨመረ
ጀግኖችን እንደገና እያነሳ እየደመረ
ዛሬም በልጅ ልጅ ልጅ ... ታሪክሽ ታወቀ
የድል ብሥራትሽ በዓለም ዓለም ዓለም ... አንጸባረቀ
የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ሻማ
መሆንሽ ተወራ አገር ለአገር ተሰማ