አዳምጥ!

ከብራንጎ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

 

አንተ ተናጋሪ፣ አንተ ቀባጣሪ፣

አንተ ፍርድ ሰጪ፣ አንተ ወንጀል ሠሪ፣

 

አንተ አስተማሪ፣ አንተ ጆሮ ቆንጣጭ፣

አንተ አስተዳዳሪ፣ ፈላጭና ቆራጭ።

 

ጨጓራው ተቃጥሎ፣ አዕምሮው ደንዝዞ፣

ሰው ሲሞት ተርቦ፣ ተጠምቶ፣ ታርዞ፣

ማዳመጥ ተሳነህ፣ ሥራህ ተደራርቦ፤

ማየትም ተሳነህ፣ ዓይንህ ተሸብቦ።

 

“ጎንበስ፣ ዝቅ ብለህ፣ ወርደህ ከዚያ ማማ፣

አዳምጥ! አዳምጥ!” ስትባል አትሰማ።

 

አዳምጥ! አዳምጥ! የህዝብህን ሮሮ፤

ኋላ ጉድ እንዳትሆን፣ ህዝቡ ተመሳጥሮ!

 

አንተ ሁነህ አራሽ፣ አንተ እህል ዘሪ፣

አንተ ሁነህ ሸማች፣ አንተ ምግብ ሠሪ፣

አንተ ሁነህ ምሁር፣ አንተ ብቻ አሳቢ፣

አንተ ፈጥኖ ደራሽ፣ ምንዱባን ቀላቢ።

 

ግን ረሃብ አልጠፋ፣ አለ እንደ ትናንቱ፣

ግን ችግር አልጠፋ፣ አለ እንደ ትናንቱ፣

ሙስናም አልጠፋ፣ አለ እንደ ትናንቱ፣

ባለሀብቶች ጥቂት፣ ድሆች በረከቱ።

 

አዳምጥ! አዳምጥ! የህዝብህን ሮሮ፣

ኋላ ጉድ እንዳትሆን፣ ህዝቡ ተመሳጥሮ!

ምላስህን አሳርፈህ፣ እስኪ ጆሮህን ስጥ፣

አዳምጥ! አዳምጥ! አዳምጥ! አዳምጥ!

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ