ቀና በል ተነሳ! (ስምራን)
ቀና በል ተነሳ!
ስምራን ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ቀና ብል እንዳለ
ምንም ለውጥ የለ
ብሷል ማቃጠሉ
የሚሰማው ሁሉ
አትበሉኝ እባካችሁ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
የሚያቃጥል ብቻ
የሚያናድድ ብቻ
የሚያበሳጭ ብቻ
የሚያሳዝን ብቻ
መሬት ተወሰደ
እህል ተወደደ
ኑሮ አስመረረ
ሀገር ተደፈረ
ሕመሙ ነደረ
ስቃይ ተከመረ
ረሃብ አገረሸ
ድህነት ሰው አሸ
የችግር መንጋጋ
አግጦ እየወጋ
ጎርፍ ሀገርን ፈጀ
ረሃብ ጊዜ አወጀ
የተማረው ሸሸ
የሚማረው ሸሸ
ፓርቲ ተገመሰ
ብሔር ተካሰሰ
አትበሉኝ እባካችሁ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
በደቡብ ተፋልጦ
በምስራቅ ተጋልጦ
በምዕራብ ተቆርጦ
በሰሜን ተፋጦ
በደረቅ ወደብ ገጦ
አትበሉኝ እባካችሁ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
ሀገር ተሸንፏል
ፓርቲ አሸንፏል
ድርጅቱ በዝቶ
ትርፉ ተንኮታኩቶ
ጉቦ ተንሰራፍቶ
ግሽበት ሞልቶ ፈልቶ
ከሳሽና ክሱ ወዳጅ አሰጥቶ
አትበሉኝ እባካችሁ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
ይታየኛል ብዬ
አልዘፍንም እምዬ
ቁርስህ ተዘጋጅቷል
ፍትፍት ተፈትፍቷል
ጨጨብሳ ቀርቧል
ወተትህ ተፈልቷል
ካላልሽኝ በስተቀር
ተይኝ ካለሁበት
ተራበም አትበይ
ይብቃ ያንች ስቃይ
አትበይኝ እናቴ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
ባህር ተሻጋሪው
የማይዘሩት ፍሬው
ያን የ’ርዳታ ስንዴ
ልምድ አያርገው ሆዴ
አባትህ የዘራው
ያ ያማረ አዝመራው
ብላ ማኛና ሠርገኛ
ካላልከኝ በስተቀር
ባለሁበት ልቅር
አትበለኝ አባየ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
መብትና ግዴታ
ሳይሆኑ ውለታ
ስጠየቅ ዝግጁ
ስጠይቅ ዝግጁ
እስኪሆኑ ድረስ
ሳይጨነቅ መንፈሥ
የሉም ካላችሁኝ
ሀገር ላይ አይገኝ
አትበሉኝ እባካችሁ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
ችግር በየፈርጁ
በሚያሰቃይ እጁ
ሳይለይ አዋቂን ከልጁ
ሔዋኗን ለስደት
ለመከራ ቅስፈት
መውደቂያውን ሳያውቅ
የህልም ሀገር ስሎ
የጠፋውን አዳም ኮብሎ! ኮብሎ!
ቤት የሚቆጥራቸው
ደመ-ከልብ ደማቸው
ሳይታወቅ አጥፊያቸው
ውሃና በረሃ ከንቱ ያስቀራቸው
ያገር ልጁ ሁላ ኑሮ ያሳደዳቸው
ይሄ! ይሄ! ቀርቷል
ሀገር ተረጋግቷል
የሠላም ነጋሪት
ሲጎሸም ያልሰማ
የተኛም ሳይሰማ
አይበለኝ እባካችሁ
ነጋ! - ወጣች ፀሐይ
ቀና በል ተነሳ
ይህንን እንድታይ
ስምራን ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )



