ከደርግ መፈክሮች / Revolutionary monument extols the virtues of communism. Courtesy Paul Henze. ጌቱ ኃይሉ

አቶ ዠ 57 ዓመታቸው ነው። መተዳደሪያ አላቸው። እንዴት ያለ ሙያ!! ባሥራ ሰባት ዓመታቸው የጀመሩት። አርባ ዓመት ሙሉ ያለማቋረጥ እየሠሩ ያሉት። ሰዉ ከሥራው በመንግሥት ለውጥ፣ በሰበብ ባስባቡ ሲባረር እሳቸው ሥራ አላጡም። ሥራቸው መፈክር አድምቆ መጻፍ።

መጀመሪያ በሁለት ቃላት ጀመሩ። ሊያውም በነጻ፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” ብለው አድምቀው ጻፉ። ከዚያ እየተከፈላቸው ደግሞ “ከቆራጡ መሪ ጋር ወደፊት!!” ብለው ቀጠሉ። ሰውየው ብቻቸውን ሲቀሩ። ወደ መጨረሻው ግድም ደግሞ “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት” ብለው ደጋግመው አድምቀው ጻፉ። እንደሌሎች “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ዝምባብዌ!” ብለው አላፌዙም።

አቶ ዠ ፕሮፌሽናል ናቸው። የከፈለ ያጽፋቸዋል። ጊዜው እየረዘመ ሲሄድ መፈክሮቹም መርዘም ጀመሩ። አንድ ገጽ የሚሆን መፈክር ጻፉ ሲባሉ እንኳን “እሺ፣ ሂሳቡ ይሄ ነው” ብለው ቀጠሉበት።

“ከልማታዊው መንግሥታችን ጋር በመተባበር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የየበኩላችንን ድርሻ በቅንነት እንወጣ" ብለው ይጻፉ ሲባሉ አሳምረው ጻፉ። "የቅንድባችንን ፀጉር በማሳደግም አስተዋይነታችንን እናጎልብት!!” ብለው አላፌዙም።

“የሚሰጠንን የአቅም ግንባታ እና የተሃድሶ ሥልጠና በማጠናቀቅ ለሀገራችን የኅዳሴ ጉዞ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን!!" ብለው ይጻፉ ሲባሉም፤ "እሺ!" እንጂ "በሥልጠናው ወቅት በሚሰጠን የውሎ አበል ግድቡ አቅራቢያ ያለች የገጠር መንደር ሄደን እያጨበጨብን እንጨምሳለን!!" ብለው አላፌዙም።

“ኢትዮጵያ፣ ካሊፎርኒያ እና አውስትራሊያ ተመሳሳይ ናቸው!!" ብለው መፈክር ለመጻፍ በራሳቸው አነሳሽነት ከጀሉ። "ምክንያቱስ?" ሲባሉ "ሦስቱም ሀገሮች ድርቅን ምንም ማድረግ አልቻሉምና!!” ብለው ማፌዝ ግን አልከጀሉም። ያ ፌዝ "copyrighted" ነውና!

“እኔ የምለው? እንዴት ነው ይኸ ነገር? ‘ሙያ በልብ ነው’ የሚባለው ያባቶቻችን ብሂል ገደል ገባ እንዴ? መፈክር ብቻ ሆነ እኮ ነገራችን። አርባ ዓመት ሙሉ መፈክር። አርባ ዓመት ሙሉ ፉከራ! አንድ ነገር ሳንሠራ! አይ የኛ ነገር!” ጓደኛቸው አቶ ጠ ጠየቃቸው።

“ዝም በል አንተ! መተዳደሪያዬን እንዳታሳጣኝ ...” መለሱ አቶ ዠ ቆጣ ብለው።

እባክዎን ሳያስፈቅዱ ላለመቅዳት መልካም ፈቃድዎ ይሁን!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ