ታሽጓል

ታሽጓል

በማሸግ የሚካሔደው የሕግ ማስከበር ሥራ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ …

ኢትዮጵያ ዛሬ - ዓለም የበረታ ጭንቅ ውስጥ ገብታለች። ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለይ በአንድ ቫይረስ በየዕለቱ የሞት መርዶ እየተነገረባ ነው። በሀብት መጠናቸው የፈረጠሙ፣ በዴሞክራሲ እርምጃቸው የሚቆለጳጰሱ የዓለማችን ልዕለ ኃያላን አገሮች ሁሉ በዚህ ወረርሽኝ እያለቀሱ ነው።

በሀብት መጠናቸው ድንበር ጥሶ የገባውን ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ባለመቻላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጭምር በማውጣት ዜጎቻቸውን ተጠንቀቁ ከማለት ውጭ፤ ይሔ ነው የሚል መፍትሔ እያበጁ ነው ማለት አይቻልም። ዛሬ በዚህ ወረርሽኝ አስር ሺህ ሊደርስ በጣት የሚቆጠር የቀረውን የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፤ (ይህንን ርዕሰ አንቀጽ ከማውጣታችን ደቂቃዎች በፊት የሟቾች ቁጥር 9989፤ በቫይረሱ የተያዙት ደግሞ 241 ሺህ 908 ነበር)። ይህ የኾነው በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው። ኮሮና ቫይረስ በታላላቆቹ አገራት የሚሰዋውን ሰውቶ፤ የአገራቱን ኢኮኖሚ አዳክሞ፤ ዘግየት ብሎ አፍሪካ ገብቷል።

ኢትዮጵያንም መጎብኘቱ ከተሰማ ሳምንት ኾነ። በተዳከመ ኢኮኖሚ አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያ እንዴት መቋቋም እንደምትችለው ለመገመት አይከብድም።

የቫይረሱ ሥርጭት ብቻ ሳይኾን፤ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ሳይታለም የተፈታ ነው። በድንብር በቅሎ ላይ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ፤ የአገሪቱ ገበያ በዋጋ እድገት ትኩሳቱ የጨመረው በኢትዮጵያ ቫይረሱ ተገኘ የሚለው ዜና እንደተሰማ ነው።

ብዙዎች እንደሚስማሙት በአግባቡ የመነገድ ባህል በሌለበትና አጋጣሚዎችን በመጠበቅ የመበልጸግ ፍላጎት ያላቸው ነጋዴዎች በገበያ ውስጥ እዚህም እዚያ ባሉበት አገር፤ ያልተገባ ጭማሪ አዲስ ባይኾንም፤ በዚህ ፈታኝ ወቅትም ያለርህራሔ መተግበሩ ግን እጅግ ያሳዝናል።

መንግሥት ይህንን ድርጊት መቆጣጠር ብቻ ሳይኾን፤ በገበያ ውስጥ የሚታየውን ክፍተት የመሙላት የራሱ ኃላፊነት አለበት። ለዚህም ነው ገበያው ላይ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠርና እርምጃ ለመውሰድ ልዩ ግብረኃይል አቋቁሞ የዘመተው።

ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እንደሰማነውም፤ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ያለአግባብ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የነበሩ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ድርጅቶቻቸውን እስከማሸግ የደረሱ እርምጃዎች እየተወሰደ ነው። እስካሁን ከሁለት ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት በዚሁ በዋጋ ጭማሪና ተያያዥ ጉዳዮች ታሽገዋል።

አዎ! በዚህ ወቅት ዋጋ በመጨመር ሌላ ራስ ምታት የሚፈጥሩ ስግብግቦችን መቅጣት ተገቢ ነው። ኾኖም መደብሮቹን ካሸጉ በኋላ ምን ይኾናል? የሚለው ጉዳይ ያሳስባል።

ምክንያቱም እነዚህ በሺህዎች የሚቆጠሩ መደብሮችና መጋዘኖች በውስጣቸው የያዙት ንብረት እንዲህ ቀላል አይደለም።

ሕብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን ምርቶች በተጋነነ ዋጋ በመሸጣቸው እንዲታሸጉ ሲደረግ፤ እነዚህ ምርቶች ላይም ተቆለፈ ማለት ነውና፤ በገበያው ውስጥ የምርት እጥረት ሊፈጥር ይችላል። ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶችም ይኖራሉ። ይህ ትክክል ከኾነ፤ ከእሸጋው ጎን ለጎን በየመደብሮቹና መጋዘኖቹ ያሉ ምርቶች እጣ ፈንታም መታሰብ ያለበት መኾኑን ያመልክታል።

ሕጋዊነትን እናስከብራለን ተብሎ፤ ሌላ እጥረትና ኢኮኖሚያዊ ክስረትን እንዳያመጣ፤ ነጋዴዎቹ የሚቀጡትን ተቀጥተው፤ እቃዎችና ምርቶቹ ግን ለሕብረተሰቡ መቅረብ አለባቸው። በማሸግ የሚካሔደው የሕግ ማስከበር ሥራ የበለጠ ውጤታማ የሚኾነው፤ ምናልባትም ሌላውን ሊያስተምር የሚችለው ንብረቶቹን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሲደረግ ነው። በተለይ በዚህ ወቅት እንዲህ ያለው አሠራር ተገቢ መኾኑን ልንጠቁም እንወዳለን። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ