የገብረመድህን ወግ - ክፍል ሁለት
የገብረመድህን እንባ፤ ከቀይሽብር እስከ ሀውዜን፡ ከሀውዜን እስከ አሁን
አለቃ ተክሌ - ከቫንኩቨር ካናዳትንሽ እንደ መግቢያ፡ ትንሽ እንደድልድይ
ከወያኔ ከድቶ ወደናት አገሩ የተቀላቀለውንና የሕወሀትን መሰሪ ተልእኮ ሲያጋልጥ የኖረውን የገብሬን ወግ ጀምሬላችሁ ነበር። ዛሬም የገብሬን እንባ እቀጥላለሁ። ከዚያ በፊት ግን በዚህ በገብሬ ወግ ምክንያት በተሰጡ አስተያየቶች ትዝ ስላሉኝ አንዳንድ ሰዎች ትንሽ ማስታወሻ ላስቀምጥ።
አንዳንድ ሰው የኢትዮጵያውያን ሁሉ እድሜ እኩል ይመስለዋል። እሱ እድሜው 40 ከሆነ ኢትዮጵዊያን ሁሉ የአርባ ዓመት ሰዎች ስብስብ ይመስሉታል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ለነሱ አዲስ ያልሆነ ነገር ለኢትዮጵያዊያንም ሁሉ አሮጌ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ማሰብ ሀጢያት ባልነበርና ባልከፋ። ይሄንን ሀሳባቸውን ይፎክሩበታል። ዓለምና ጋሽ ገብሬ እንዲሁም እኛ ወገኞች ለነሱ አዲስ የሆነ ወግ ስንፈጥር ማደር የለብንም። የዛሬ 20 ዓመ.ት ጋሽ ገብሬ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሲናገር ከሰማ ምን ይሄ እኮ ትናንት የሰማነውና ትናንት የምናውቀው ነው። ምን አዲስ ነገር አለው? በቃሀ አዲስ ካልሆነ ይሄ አዲስ የሆነላቸው ያንብቡት። ይስሙትም። ለነገሩ ከሰማይ በታች ምን አዲስ ነገርስ አለ አይደለም ያለው ጠቢቡ። ባለፈው ሰሞን የተስፋዬ ገብረአብ መጽሀፍ ሲወጣም ምን አዲስ ነገር ጻፈ ይሄ የምናውቀው ነው።” አዋቂ በዛ። ኢትዮጵያ ደግሞ እንዲህ እንዳሁኑ የሆነችው አዋቂ በዝቶ መሰለኝ። ለኛ ላልሰማነው ብንሰማም ደግመን መስማት ለምንፈልገው ግን ጋሽ ገብሬ በየዋህ አንደበቱ ግን ደግሞ በቁጭትና በእልህ ወጉን ቀጥሏል።
ህዝቡ ሲረግፍ፡ ባንኮች ሲዘረፉ፡ የወያኔ ኪስ ሲያብጥ
በርግጥ ዛሬ በዚያ አንዳንዶቻችን ላንስማማ እንችላለን። ትናንት ግን “ወያኔ የትግራይ ህዝብም ጠላት ነበር” ይለናል። ገብሬ፡ ገብረመድህን። ምሳሌ፤ የ1977ን ረሀብ ጠቀሰ። በዚያን ግዜ፤ እጅግ በጣም ብዙ ርዳታ መጣ። መድሀኒት፡ እህል፡ ገንዘብ፡ ዘይት፡ ምን ያልመጣ ነገር አለ? ወያኔ ግን የትግራይ ህዝብ በረሀብ እየተቆላ ርዳታውን ሸጦ 7 ዙር ካድሬ አሰለጠነበት። ስለማርክሲዝምና ሌኒንዝም። ገብሬም አንዱ ሰልጣኝ ነበር። ገብሬ እንዲህ አለ “ለእርዳታ ማግኛ ማሳያ ይሆን ዘንድ 1.5 ሚሊዮን አካባቢ የትግራይ ህዝብ ተጓጉዞ በሱዳን በሶስት ካምፖች እንዲቀመጥ ተደርጎ፡ ሕዝቡ እንደቅጠል እየረገፈ፡ የርዳታው ገንዘብ ግን ለወያኔ መቋቋሚያ ሆነ። ጉና የተቋቋመው በዚያ ገንዘብ በ1978 ነው አለ። እርዳታው እየተቸበቸበ ወደ ኪስ ይገባ ነበር። ለበሬ መግዢያና ለገበሬው ማቋቋሚያ የተሰጠ ገንዘብ ለሐወሀት ማቋቋሚያ ሆነ። ልብ በሉ የዚያን ግዜ የሱ የገብሬ ሀላፊነት የገንዘብ ቤትነት ነበር ይሄንን ነገር አሳምሮ ሳያውቅ አይቀርም።
ስለኤፈርት (EFFORT) መቋቋም ተጠየቀ። ግልጽ ነው። ኤፈርት የተቋቋመው ከኢትዮጵያ በተዘረፈ ሀብት ነው። ደርግ ሲዳከምና ሲወድቅ፡ የመንግስተ ባንክና ተቋሞች ተዘርፈዋል። እንደ ንግድ ባንክ ብሄራዊ ባንክ ያሉ ትልልቅ ባንኮች ተዘርፈዋል። ወያኔ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ከብሄራዊ ዘርፏል። ይሄ ካሽ ክሮፕ ሸጠን ከመርከብ ስራ ምናምን ያገኘነው ነው የሚሉት ታሪክ ቅጥፈት ነው። እነ አቦይ ስብሀት የሚቸረችሩት ቅጥፈት ነው። ቀድሞ ነገር ሁመራ በደርግ በኢዲዩ እጅ ነበርና ሕወሀት ሁመራ ገብቶ ካሽ ክሮፕ ሊያመርት የሚችልበት እድል አልነበረውም። በተለያየ ቦታ ሀብት ንብረት ነበረን የሚለው ምክንያት ሀሰት ነው። በሌላው አናጻር፡ እንደምታውቁት ሁሉም አገራት የራሳቸው የወርቅ ክምችት አላቸው። ያኔ ወያኔ ሲገባ የነበረ ወደ ስምንት መቶ ኪ.ግ. የሚጠጋ የወቅር ክምችት ተሸጦ ወያኔ ኪስ ገብቷል። ስብሀት ነጋ መርከብ ነበረን ምናምን የሚለው እልም ያለ ቅጥፈት ነው። “ወያኔ ጭነት አጋሰሰም አልነበረው እንኩዋን መርከብ። እኛ አኔ ተመጽዋች ነበርን። ያንን ሁሉ በረሀ የምንጓዘው በባዶ እግራችን ነበር። እስከ 1974 ድረስ ሻይ አናውቅም ነበር። ሰለዚህ ኤፈርት የዘረፋ ውጤት ነው።”
ኢህአዴግ የሚባል ነገር የለም፡ ሕወሀት የሚባል የቅጥረኞች ስብስብ እንጂ
ከዚያ ስም ጠቀሰ። እነማን እንደሆኑ የዚህ ሁሉ ስራ መሪዎች። መሰሪዎች። መለስ ዜናዊ፡ ስብሀት ነጋ፡ ብርሀነ ገብረክርስቶስ፡ አዲስ ዓለም ባሌማ፡ ስዩም መስፍን፡ አባይ ፀሀዬ፡ ትናንትም ከኢትዮጵያ ህዝብ ዘርፈዋል፡ አሁንም ከኢትዮ ህዝብ ይዘርፋሉ። ይሁን እንጂ ኤፈርት የኢትዮጵያ ነው። እህ ምን ማለትህ ነው? ኤፈርት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተዘረፈ ገንዘብ የተገነባ ስለሆነ ምንግዜም የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ነው። ያ ብቻም አይደለም፡ ዛሬ ብዙህ ሺህ ኢትዮጵአዊያን ወደ መቶ ሀያ በሚጠጉት የኤፈርት ድርጅቶች ከስራ ውጪ እንዲሆኑ ተግፍተው ወጥተዋል። ስለዚህ ወያኔ የተደመሰሰ እለት የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል። ስለአዜብ ጎላ ተጠየቀ። “እሷም ባሏም ሰርቀው ነው። ሁለቱም ሌቦች ናቸው።” ገበሬ ሲናገር በእልህና በምሬት ነው። ዋናው ሌባ ግን ወያኔ እንዳለ ነው አለ። ይሄ ኢህአዴግ ወያኔ መንግስት ምናምን የሚል ክርክር ተነስቶ ነበር አንድ ሰሞን። ኖ ኖ፡ “ኢህአዴግ የሚባል ነገር የለም።
ያለው ሕወሀት/ወያኔ ብቻ ነው።” ይሄንን ቃል በቃል ነው የምነግራችሁ ገብሬ እንዲህ ነው ያለው። “ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉ የትግራይ ሰዎች ናቸው። ሌሎች አብረው ይኖራሉ፤፡ ግን እነዚያ ከወያኔ ጋር የሚተባበሩ ካድሬዎች ትርፍራፊዎች ናቸው።” ገብሬ ከዚያ በኋላ ስለወያኔና ወንጀሉ አንበለበለው። “ወያኔ የወንጀለኞች ድርጅት ነው” ዌአኔ የዘራፊዎች ድርጅት ነው። በገንዘብ የደለቡ ናቸው። ገዳይ ናቸው። ቅጥረኛ አሸባሪ ድርጅት ነው። በነገራችን ላይ ይሄንን የትግራይን ህዝብና ወያኔን ግንኙነት በደንብ አድርጎ ጠንቅቆ የተረዳና የገባው ሰው ገብሬን አየሁ። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያን እየገዙ ያሉ ግን የትግራይ ሰዎች ናቸው ማለት በምንም መልኩ የትግራይን ህዝብ መወንጀል አይደለም ነው የሚለው። በዚህ ላይ ሌላ ግዜ አትታለሁ። ወደ ቀይ ሽብር እንሂድ።
ቀይ ሽብር፡ ሀውዜን፡ አብዮት ልጇን በላች አይደለም፡ ሕወሀት ትግራይን አስበላ እንጂ
ስለቀይ ሽብር ነጭ ሽብርም ተጠየቀ። በዚያም ግዜ ወያኔ የሰራውን ደባ እንዲህ ሲል ገለጸ። “ደርግ በቀይ ሽብር ምክንያት በትግራይ ውስጥ ብዙ ሰው አልገደለም።” እንደ ገብረመድህን አገላለጽ፡ ይልቅስ አጋጣሚውን በመጠቀም፡ ወያኔ በተለይ “አማራ ጠላት ነው” የሚለውን ዓላማ ይቃወሙ የነበሩትን ምርጥ ምርጥ የትግራይ ልጆች አስመትቶበታል፡ ተክሉ ሀዋዝ የተባለ ሰው እንደ ነገረው ከሆነ። ገብሬ በዚያን ግዜ አዲስ አበባ ወይንም ከትግራይ ውጪ በወያኔ ተንኮል የተገደሉትን የትግራይ ተወላጆች ምን የመሳሰሉ አገር ወዳድ መምህራን፡ ሀኪሞች፡ ኢንጂነሮች ስም ዝርዝር ጠቀሰ። እጄ እንደ ገብሬ ጭንቅላትና ምላስ ፈጣን አልነበረምና ስሞቹ አመለጡን። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው አማራ ጠላት ነው የሚለውን የህወሀት ፖሊሲ በሀይለኛው ይቃወሙ ስለነበር፡ ወያኔ በስማቸው እነሱን አባላት የሚያስመስል ደብዳቤ እየጻፈ ማህተም እየረገጠ አዲስ አበባ ለደርግ ደህንነቶች እንዲደርስ ሲያደርግ፡ ደርግ ደግሞ በኋላ በሀውዜን ግዜም እንደምናየው “አዙሮ ማስብ ስለማይችል” (እዚህ ጋር በጣም ስቄያለሁ፡ በኋላም እስቃለሁ፤ ባነጋገሩ ማለቴ ነው።) መረጃውን አገኘሁ ብሎ እነዚህን ወጣቶ መታቸው። ረሸናቸው። ሕወሀት መረጃ እየሰጠ ነው ያስፈጃቸው እንጂ፡ ደርግ ብዙም በቀይ ሽብር በትግራይ ሰው አልፈጀም። ወደ ሀውዜን ሄደ። የሀውዜን ድብደባስ?
“ወይ፡ ሀውዜንም የወያኔ ድራማ ነው።” በዚያን ጊዜ ሕወሀት በምትሰራው ስራ ምክንያት እጅግ በጣም ተጠልታ ነበር። ሰው አጣች። ምልምል ጠፋ። እናስ? ተንኮል አሰቡ። የዚያን ግዜ የትግራይ አስተዳዳሪ ለገሰ አስፋው ነው። ከዚያ ወያኔ ሀውዜን አንድ ክ/ጦር እያስገባች እያስወጣች ወያኔ ሀውዜን ስብሰባ ልታደርግ ነው የሚል ወሬ ለደርግ ደህንነት እንዲደርሰው አደረገች። ሀይሉ ሳንቲም (ሳነቲም ቅጽል ስሙ ነው) የሚባል የወያኔ የጦር ደህንነት፡ የወያኔ ጦር ሀውዜን ሊሰበሰብ ነው የሚለውን መረጃ ለለገሰ አደረሰ። እውነት እንዲመስልም፡ በገበያው ቀን የተወሰኑ ታጋዮች ባካባቢው ውር ውር ሲሉ እንዲታዩ ተደረገ። የሀውዜን ገበያ መቼም እጅግ የታወቀ ነበርና ከብዙ ቦታ ብዙ ሰዎች ለንግድ ይመጣሉ።
በእለቱ ስድስተ የደርግ ሚጎች እየተመላለሱ በመስቀልያ ቅርጽ፡ ገበአውን ደበደቡት። ይሄ ሁሉ ሲደረግ ቪዲዮ ይነሳ ነበር። ነገሩ ለረጅም ግዜ የተቀነባበረ መሆኑ የሚታወቅባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው። ወደ አስራ ሁለት ፎቶ አንሺዎች ሱዳን ውስጥ ሄደው እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። ገብሬ የዚያን ግዜ ቪዲዮ ካሜራ አያውቅም ነበር። እነ ተክለወይን አስፍሀ፡ እነ ሱራፌል ምህረተአብ፤ እነ እያሱ በርሄ ካሜራ ቀራጭነት ሱዳን ውስጥ ተምረው መጡ። ያ ሁሉ ድብደባ ሲደረግ ተራራ ላይ ቆመው እያንዳንዱን ሚግ ከሁሉም አቅያጫ ቪዲዮ ያነሱ ነበር። ይቀርጹ ነበር። በነጋታው ይሁን ማታውኑ ያ ሁሉ ፊልም ሱዳን ውስጥ በቲቪ ታየ። ገበያ ላይ የሞተው ሰው እንሰሳ፡ ህዝብ፡ ሽማግሌ ሕጻናት በቲቪ በደንብ ተቀርጿል።
ይሄም አንደኛ ደርግን አለማቀፋዊ ውግዘት አስከተለበት። አሳጣውም (ተሳጣ፡ መሳጣት ከሚለው ቃል የመጣ ነው)። እዚህ ጋር ነው ደግሞ ያሳቀኝ “ደርግ አዙሮ የማሰብ ችሎታ የለውም እንጂ” መረጃውን መመርመር ነበረበት ሲል። ይሄንን ድጋሜ ሁሉ እያሰብኩት አውቶብስ ላይ ስስቅ ሰዎች እየለቀቅኩ መስሏቸው ገልመጥ አድርገውኛል። ለነገሩ እንደወረደ ከራሱ ከገብሬ አፍ ካልሰማችሁት ላያስፈግጋችሁም ይችላል። ደርግ፡ የመጣለትን መረጃ አገኘሁ ብሎ መደብደብ አልነበረበትም። ደርግም በዚያ በስፋት ተወገዘ። ሁለተኛ፡ ከዚያ ቀን በኋላ ሰው አጥቶ የነበረው ወያኔ በመቶ ሺሆች የሚቆጠር ፈቃደኛ ይተምለት ጀመር። የተለያየ እርዳታም አገኘ። በዚያን ግዜ “በምን አውቃችሁ ነው ካሜራ ይዛችሁ ተዘጋጅታችሁ የጠበቃችሁት ወይም ያነሳችሁት ብሎ የጠየቀም አልነበረም።” ያነዜ እነ ኢያሱ በርሄና ሱራፌል ምህረተአብ አውሮፕላኖቹ ሲመጡ፡ ሲወርዱ፡ ሲደበድቡ የሚያሳየውን ፊልም ተዘጋጅተው እንደ ቀረጹ አጫውተውኛል። ወያኔ ለትግራይ ህዝብ ቆሜያለሁ ይላል ግን በሀውዜንም በቀይ ሽብርም እንዳየነው የትግራይን ህዝብ የጎዳ ጠላት ነው ዋናው ነጥብ። ይሄ ታሪክ ከዚህ ቀደም አንድ የማላስታውሰው የትግራይ ሰው፡ ካለው ነገር ጋር ተመሳሰለብኝ። ያ ሰው፡ “ትልልቅ የሆሊውድ ፊልም ማንሻ ካሜራዎችን ጠምደው ነበር የሚቀርጹት” ብሏል ያ ሰው። ገብሬ ብቻውን አይደለም ማለቴ ነው።
ደመኛ መንገደኛ፡ ታሪካዊ መሀረብ፡ እንባ አዳሽ ወ/ሮ
በደርግ ውስጥ ስልጣን ላይ ስለነበሩና ለወያኔ ያገለግሉ ስለነበሩ ወይንም ወያኔ ደርግ ውስጥ ሰርጎ ስለመግባቱም ተጠየቀ። የሚያውቀውን ያህል ተናገረ። ፍስሀ ድስታ በሚስቱ በኩል ሊደረግፋቸው ይችል ይሆናል። ምክንያቱም ሚስቱ ኤርትራዊት ነበረች። በተጨማሪም እነግዳለሁ እያለች ውጭ አገር ከቦታ ቦታ ትዘዋወር ነበር። ስለዚህ በዚያ አጋጣሚ መረጃ ልታቀብል ትችላለች ብሏል። (ከዚህ ቀደም ባለው ዘገባ እንደገለጽኩት አንዲህ ያሉ ነገሮችን በማንሳት የትግል አጋረሮቻችን” ኤርትራዊአንን ማስቀይም ባልፈልግም። እንደ ታሪክ ግን ሆኖና ተደርጎ ከነበረ ማንሳቱ አይጎዳም። ደግሞም አለፈ ነገር ነው። ደግሞም እኔ አይደለሁም ያልኩት። ገብረመድህን ነው።) የግበሬ ደስ አለን ነገር የማያውቀውን አይናገርም። ከሰው የሰማውንም ከሰው ሰማሁ ብሎ ነው የሚናገረው። ራሱ የነበረበትን ራሱ እንደነበረበት አድርጎ። ስለ ደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ብዙ አላውቅም ነው ያለው። ከዚያ ውይይቱ ቀጠለ። አወያይዋ፡ ወ/ሮ ብዙ ወንድማገኘሁ አንዳንድ ቦታ ላይ ነገር የምትጎትተው ነገር አልተመቸኝም። መቼም ብትቀየምም ትቀየመን እንጂ ገብሬ ጥሩ ታሪክ ጀምሮ መሀል ላይ የማታቋርጠውም ነገር እንደዚያው። ወደ ቀደመው ነገር ልመልሳችሁ። ወደ ገብሬ።
የሆነስ ሆነና፡ ወያኔ በትግራይ ህዝብ የሚጠላ ድርጅት ነበር ነው የሚለው ገብሬ። በወያኔ ውስጥ የነበረና ያለ አባል ምን ይደረጋል? “እኔ ከካርቱም ሱዳን ወደ አዲስ አበባ ስገባ እሪ እያልኩ እያለቀስኩ ነበር። ከአውሮፕላኑ እንደወረድኩ፡ መሬት ወድቄ እሪ እያልኩ፡ የወያኔ አባል ሆኜ ኢትዮጵያን የወጋሁ ነኝ ይቅር በሉኝ ብዬ ገባሁ። እዚህ ጋር ገብሬ አንጀት ይበላል። “አንተ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር በለኝ ብዬ ነው የገባሁት። ወንጀለኛ ነኝ ብዬ ነው የገባሁት። ተደብቄ ተሸፋፍኜ አይደለም የገባሁት። አንተ የኢትዮጵያ ህዝብ አንተ መሬት ወጋሁህ አደማሁህ ብዬ ገባሁ።
አንዲት ትልቅ ሴት አይተውኝ አይዞህ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ባይ ነው ብለው እስካሁንም እጄ ላይ ያለች ነጭ መሀረብ አውጥተው ሰጡኝ። ይሄ እንግዲህ በ1982 መጨረሻ ላይ ነው። በቃ ከላይ ከአውሮፕላን ማረፊያው ማማው ወርጄ እታች መሬት ተፈጠፈጥኩና እየተንከባለልኩ ይቅርታ ጠየቅኩኝ። አንድ የሚቀበሉኝ ባለስልጣን ነበሩ፡ ዝም ብለው ያዩኝ ነበር። ባጠቃላይ ይቅርታ ተይቄ ነው የገባሁት። ወያኔን ወንጅዬ ራሴን ነጻ ማድረግ አልችልም። ወያኔ ሽብርተኛ ዘረኛ ድርጅት ነው። ግን አባሉም ያው ነው። ሀላፊነት እወስዳለሁ። እኔም አሽከር ሆኜ የወንጀሉ ተካፋይ ነበርኩ። እንድም ቀን ይሁን አንድ ሳምንት በአባልነት የቆየና የተባበረ ሁሉ ልክ እንደኔ ይቅርታ ካልጠየቀና ካልወጣ በስተቀር ተጠያቂ ነው።
እነ ገብሩ አስራትስ? እነስዬስ? ይቀጥላል፡ ገብሬ። እንደው ለንጽጽርና ለመረጃ ያገለግል እንደሁ እንጂ፡ እኔ እንደጸሀፊ ይሄንን እነ ስዬን እን ገብሩን ሀጢያታቸውን እንዲናዘዙ እናፋጣቸው የሚለው ስልት አቀንቃን አይደለሁም። እንደ ገብሬ ከውስጣቸው ካልመጣና ካልተናገሩት በስተቀር። የሆነ ሆነ የገብሬን የመጨረሻውን ክፍል ውይይት እንዳደረሰኝና www,ecadforum.com ሳይቀድመኝ ይዤላችሁ እቀርባለሁ። የገብሬ ጠቃሚ ወግ አይልቅም። ስላለፈው ብቻ አይደለም ከዚህ በኋላም “ዋናውን ወያኔን የመደምሰስ ስትራቴጂያችንን” እንዴት ከግብ ማድረስ እንደምንችልም ይናገራል። በሰላማዊስ መንገድ ስልጣን ለህዝብ ይሰጣሉ? ገብሬ ይመልስልናል። አሁን እየነጋም ነው። ስራም ጨርሼ ከቤት ገብቼ መተኛት አለብኝ። የምጠብቀው ህንጻም እየሞቀ ነው። መልካም ቀን።
ልጅ ተክሌ ነኝ፡ ከአገረ ካናዳ (በነገራችን ላይ “ልጅ” የሚለውን ለራሴ የሰጠሁትን ሹመት ወዳጄ መስፍን አማል አልወደደልኝም። ትውልዴም እድገቴም ደሜም ከነጌሌ ቦረናና ከአርሲ ነጌሌ መሆኑን ስለሚያውቅና ከሁለቱም ነጌሌዎች የነገስታት ደም ያለው ልጅ አይወለድም ብሎ ነው። በእውኑ ነጌሌ ከመስፍን አማን አገር ታንሳለችን? በፍጹም። ግን ይሁን። ስለዚህ ትንሽም ቢሆን ወደሚቀርበኝ አለቃነት ቀይሬያለሁ። ሌላ ተቃዋሚ እስኪመጣ፡ ያው ልጅ ተክሌ ነኝ። ከቫንኩቨር ካናዳ)። ልትተቹ ወይም ልትመቹ የምትሹ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ብትመይሉልኝ ማንም ይነግረኛል። ይደርሰኛል።