አቶ መለስና ወ/ት ብርቱካን ሲነፃፀሩ (ግርማ ካሣ)
ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ሁለቱም በኢትዮጵያ እየተፋፈመ በመጣው የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላቸው። ሁለቱም አባል የሆኑበት ድርጅት ሊቀመንበር ናቸው። ሁለቱም በደጋፊዎቻቸው ይደነቃሉ። ሁለቱም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የነበሩ ጊዜ ጎበዝ ተማሪዎች ነበሩ። ሁለቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበሩ። ሁለቱም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በአዲስ አበባ ነው። ሁለቱም ወላጆች እንደመሆናቸው የልጅን ፍቅር ያውቃሉ። ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው።
የመጀመሪው አቶ መለስ ዜናዊ ይባላሉ። የአምሳ አራት አመት አዛውንት ናቸው። እናታቸው የአዲቋላ (ኤርትራ ተወላጅ) ሲሆኑ አባታቸው ደግሞ የአድዋ ትግራይ ሰው ነበሩ። ሌላኛዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት። አባቷ የወለጋ ሰው ሲሆኑ እናትዋ ደግሞ የሸዋ ሰው ናቸው።
በነዚህ ሁለት የፖለቲካ ሰዎች ውስጥ ትግራይ፣ ኤርትራ፣ ወለጋንና ሸዋን እናያለን። (ከቀድሞ የኢትዮጵያ አሥራ አራቱ ክፍለ ሀገራት አራቱ ማለት ነው)
አቶ መለስ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ለገሰ የሚል ነበር። “ዜናዊ” ማለት ዜና አብሳሪ ማለት ይመስለኛል። ወላጆቻቸው ለገሰ ዜናዊ ሲሏቸው “የሚያበስር ተሰጠን፣ ተወለደልን፣ ተለገሰልን” ብለው ሳይሆን አይቀርም ያንን ስም የሰጧቸው። መቼም ወላጆቻቸው ያኔ የተመኙት አቶ መለስ (ለገሰ) መልካም ብሥራት፣ መልካም ወሬ አብሳሪ እንዲሆኑላቸው ነበር የሚል ግምት አለኝ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ስሟ እንደሚገልጸው፣ ወላጆችዋ “ያማረች፣ የጣፈጠች፣ በሰው የተወደደች ትሁን” ብለው ይመስላል “ብርቱካን” ያሏት። “ሚደቅሳ”ም ተመሳሳይ ትርጉም አለው። “ሚደቅሳ” በኦሮምኛ ማሳመር፣ ማስዋብ ማለት ነው።
የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም ሆነ የአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦች ሁለቱም ልጆቻቸው ትልቅ ደረጃ ደርሰው፣ መልካም ነገር አድርገው፣ በመልካም ስም ታውቀው እንዲያልፉ ፍላጎት እንደነበራቸው ነው የምናየው።
የነዚህ ሰዎች መመሳሰል ግን እዚህ ላይ ያበቃል። አሁን ባለንበት ሁኔታ አቶ መለስ ዜናዊ ትልቅ ጭካኔ የተሞላበት ኢ-ሰብዓዊ ሥራ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጨምሮ በሠላማዊ ዜጎች ላይ እስኪሰሩ ድረስ፣ በጥላቻና በክፋት የተሞሉ፣ እልኸኛ ሰው እንደሆኑ እያሳዩን ያለበት ወቅት ነው።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ “ቅንጅት የሰው ጠላት የለውም። ወያኔ ጠላት አይደለም። ለሀገራችን መፍትሄ ፍቅር ነው። ያሰሩኝን ይቅር ብያለሁ” እስከማለት ድረስ በፍቅርና በደግነት የተሞላች፣ የበደሏትንና ወደ ሁለት አመት ገደማ በግፍ ያሰሯትን ሰዎች፣ አቶ መለስን ጨምሮ፣ይቅር ያለች ታላቅ የፍቅር ሴት ናት። አንድ በሉ።
አቶ መለስ ዜናዊ በሚቆጣጠሩት የደህንነት ጽ/ቤት፣ የፌደራል ፖሊስና የአጋዚ ጦር ይመካሉ። እነዚህን ሕሊና የለሽ ሰዎችን በመላክ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎችን በጠራራ ጸሃይ አስገድለዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ አሳስረዋል። ሠላማዊ መንደሮችን እንዲቃጠሉ አስደርገዋል።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታጠቀ ሰራዊት የላትም። በቤቷ መሳሪያ አልተገኘም። በእጆችዋ የወደቀውን አነሳች እንጂ የቆመውን ተኩሳ አልጣለችም። የምትተማመነው በሕዝብ ጉልበት እንጂ በጠመንጃ ጉልበት አይደለም። ሁለት በሉ።
አቶ መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ እርሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ትዝብት ውስጥ እስኪከቱ ድረስ የሚዋሹ ቀጣፊ ሰው ናቸው። ለምሳሌ የቅንጅት መሪዎች ከሁለት አመታት በፊት በተፈቱ ጊዜ፣ አቶ መለስ “ ከአሁን በኋላ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ መመለስ የለብንም። ሕግን እስካልጣሱ ድረስ (የተፈቱት እሥረኞች) ሙሉ የፖለቲካ መብታቸው ተጠብቆ መንቀሳቀስ ይችላሉ” ነበር ያሉት። ነገር ግን ቃላቸውን ለውጠው፣ ቀድሞ ከተፈቱት እሥረኞች መካከል ወ/ት ብርትካን ሚደቅሳን በግፍ እንድትታሰር አድርገዋል።
አቶ መለስ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታህሳስ 2001 እስከ ሐምሌ 2001 ድረስ በጨለማ ቤት ውስጥ በግፍና በጭካኔ እንድትቀመጥና ሕገ መንግሥትና ፍርድ ቤት የፈቀደላትን በዘመድ፣ በሃኪም፣ በመንፈሳዊ አባት፣ በጠበቃ .. የመጎብኘት መብቷ እንዲረገጥ አስደርገዋል። በማንም ነፈሰ ገዳይ ላይ እንኳን ያልደረሰ ጭካኔ እንዲደርስባት ፈቅደዋል። በአንድ በኩል ይህን ሁሉ እያደረጉ በሌላ በኩል ግን ወ/ት ብርቱካን ሰብዓዊ እንክብካቤ እየተደረገላት እንደሆነ በአደባባይ ይናገራሉ። ይህም በውሸት መለኪያ በዓለም ከቀዳሚዎች መካከል የሚሰለፉ ሰው መሆናቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያላደረገችውን “አድርጊያለሁ” እንድትል፣ እንድትዋሽ፣ ግፊትና ዛቻ ቢደረግባትም “እምቢ” ብላ ለእውነት የቆመች ናት። ለእውነትም በመቆሟ ትልቅ ዋጋ በአሁኑ ወቅት በመክፈል ላይ ትገኛለች። ሦስት በሉ።
አቶ መለስ ዜናዊ ከቀድሞ የ66ቱ አብዮት ዘመን ከነበረው፣ እርስ በርስ በደም ከተቃባው፣ እምነተ ቢስ ፍልስፍናን ለኢትዮጵያ ህዝብ ካስተዋወቀው፣ እግዚአብሔርን ከካደው፣ ሀገራችንን ወደ ጨለማ ከወሰደው ትውልድ ናቸው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በጥላቻና በቂም በቀል ካልተሞላው ከአዲሱ ትውልድ ናት። አራት በሉ!
የአቶ መለስ ዜናዊ ሴት ልጅ (ገንዘቡ ከየት እንደተገኘ እግዜር ይወቀው) በዓለም ዝነኛ የሆነው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየተማረች ናት። ለኑሮ፣ ለትምህርት ቤት ክፍያና ለተለያዩ ወጭዎች በአመት ሃያ አምስት ሺህ ፓውንድ ወይንም ሠላሳ ስምንት ሺህ ዶላር አካባቢ ( ከአራት መቶ ሺህ ብር በላይ ) አቶ መለስ ለልጃቸው ይከፍላሉ። የአቶ መለስ ዜናዊ ልጅ እንደ አባቷ ጎበዝ ተማሪ ከሆነችና በአራት አመት ውስጥ የባችለር ዲግሪ የምትይዝ ከሆነ፣ የአራቱን አመት ሂሳብ ብናሠላው፣ ከአንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ብር በላይ ገንዘብ ያወጣል።
የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ልጅ ሕጻን ሐሌ፣ እናቷ በጭካኔ ተወስዳባት፣ በሣምንት አንድ ቀን፣ ከፈረንሣይ ለጋሲዮን ቃሊቲ ድረስ፣ ከአሮጊት አያቷ ጋር በመሄድ፣ ለአሥራ አምስት ደቂቃ ብቻ ነው የምታያት። በቃሊቲ እስር ቤትም ያሉ ሰራተኞች፣ ከአራት ኪሎ በሚደርሳቸው ጥብቅ መመሪያ፣ በእናቷ እንኳን መታቀፍ እናቷንም መሳም ያልቻለች ምስኪን ልጅ ናት። አምስት በሉ!
አቶ መለስ ሕግን እንደ በትር በመጠቀም፣ እንዳሻቸው በመተርጎምና በመለጠጥ በሕግ ስም በዜጎች ላይ የግፍ ቀንበር የሚጭኑ ሰው ናቸው። በአፋቸው “ሕግ ሕግ” ይላሉ በተግባራቸው ግን ሕግ የሚያስፈራቸውና ከሕግ ጋር የተጣሉ፣ ሕግንም የሚረግጡ ግለሰብ ናቸው።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአመታት በፊት በሕግ ፊት ለቀረቡት አቶ ስየ የዋስትና መብት በሰጠችበት ጊዜ እንዳስመሰከረችው፣ ከአራት ኪሎ በአቶ ስየ ላይ ኢፍትሃዊ ውሳኔ እንድትወስን ተጽኖ ቢደረግባትም፣ ሕግ ከማንም በላይ መሆኑን ያሳየች የፍትህ ሴት ናት።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሕግ የበላይነት ያላትን ቁርጠኝነት በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባር ያሳየች ታላቅ ኢትዮጵያዊት ናት። ለዚህም ነው የአቶ መለስ የልጅነት ጓደኛ የሆኑት አቶ ስየ አብርሃ “ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ አይደለም። በጦርነት ከሚታይ ጀግንነት ያልተናነሳ ጀግንነት ያሳያች፣ ጀግና ሴት” ሲሉ ለብርቱካን ሚደቅሳ ያላቸውን ክብር የገለጹት። ስድስት በሉ!
ምንም ቢሆን ክፉ የሰራ ሰው በመንፈሱ ሠላም ስለማያገኝ፣ አቶ መለስ ዜናዊ የጭንቀትና የመንፈስ መረበሽና የፍርሃት እሥረኛ ሆነው እየተሰቃዩ ናቸው። እራሳቸውን ይፈራሉ። አብረዋቸው ያሉትን የፖሊት ቢሮ አባላት ይፈራሉ። ህዝቡን ይፈራሉ። (ምናልባት የማይፈሩት ጎርደን ብራውንና ሲልቪዮ ቤሎስኮኒን ብቻ ሳይሆን አይቀርም።) ሌሊት፣ በቤተ መንግሥት በላጠጠ መኝታ ላይ እየተኙም እንቅልፍ የላቸውም። እንደምንሰማውም ከፍተኛ የራስ ምታት ስላለባቸው ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር ብዙ ጊዜ ይሄዳሉ። አላወቁትም እንጂ የታሰሩትስ አቶ መለስ ዜናዊ እራሳቸው ናቸው - በክፋትና በጭካኔ መንፈሥ።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመንፈሷ ነፃ የሆነች ሴት ናት። በሥጋ በማይመች ቦታ ታስራለች። ግን በዚያ በማይመች ቦታ ሆና የጣፈጠ እንቅልፍ ትተኛለች። ውስጧ በፍርሃት የተሞላ አይደለም። በራሷ ትተማመናለች። ከማንም ጋር መኖር ትችላለች። በየትም ቦታ ብትሄድ ማንም አይነካትም። ሁልጊዜ እራሷን ቀና የምታደርጋት ናት። ሰባት በሉ!
አቶ መለስ ዜናዊ በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን እንደጨበጡ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጨርቅ ነው በማለት ሀገራችንን በዘር የከፋፈሉ ፀረ-ኢትዮጵያ የኋላ ቀር ፖለቲካን ያራመዱ ሰው ናቸው። ኦሮሞው ከአማራው ጋር እንዲጋጭ፣ አማራው ኦሮሞውን እንዲሸሽ፣ ትግሬው አማራውንና ኦሮሞውን እንዲፈራ፣ በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠር ከተለያየ ዘር የተወለደውና የተደባለቀው ኢትዮጵያዊ መብቱን እንዲረገጥ ያደረጉ፣ከፋፋይ መሪ ናቸው። እርሳቸው የዘረጉት ፖለቲካ፣ የዘር ድርጅቶች እንደ አሸን እንዲፈሉ ያደረገ ፖለቲካ ነው።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያ አንድነትንና ሉዓላዊነትን መሰረት ያደረገ ድርጅትን የምትመራ ሴት ናት። የኢትዮጵያዊነትን ትልቅነት በማጉላትና በማሳያት በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰልፈው የነበሩትን ያሰባሰበች፣ መድረክ የሚባለውን በአሁኑ የ2002 ምርጫ ጠንካራ አማራጭ ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብን ለመብቱና ለአንድነቱ እያደራጀ ያለው አካል፣ እንዲመሰረት መሰረቱን የጣለች ሴት ናት። በርሷ መሪነት የጎሳና የብሔር ድርጅቶች የኢትዮጵያ አንድነትን እያነገቡ በሕብረ ብሄራዊነትና በኢትዮጵያዊነት ሥር ተሰባስበው እየታገሉ ናቸው።
አቶ መለስ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ዘረኝነት የሚወስድ ፖለቲካ ሲያራምዱ፣ ወ/ት ብርቱካን ከዘረኝነት ወደ ኢትዮጵያዊነት የሚያመጣ፣ የአንድነት፣ የፍቅርን የወንድማማችነትን ፖለቲካ የምታራምድ ናት። ስምንት በሉ!
ሰው የቅርቡንና የላይ ላዩን ያያል። እግዚዚብሔር ግን የሩቁንና የልብን ይመለከታል። እምቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የመጥምቁ ዮሐንስ እናት ኤልሳቤትን ለመጎብኘትና ለማገልገል በሄደች ጊዜ የተናገረችው አንድ ትልቅ አባባል ነበር። “እግዚአብሔር ለትኁታን ፀጋን ይሰጣል። ትዕቢተኞች ግን ያዋርዳል” ነበር ያለችው።
ዛሬ አቶ መለስ ጠዋትና ማታ በኢትዮጵያ ቴለቭዥን ስማቸው ሲጠራ፣ ዛሬ አፍሪካን ወክያለሁ ብለው በዓለም አቀፉ መድረክ ከነኦባማና ጎርደን ብራውን ጋር ፎቶ ሲነሱ፣ ከኒኮላይ ሳርኩሲ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ ዛሬ አይጋ ፎረምና የመሳሰሉ “መለስ የኢትዮጵያ አንበሳ “ እያሉ ሲያወድሷቸው፣ የጸኑ፣ የበረቱ፣ የማይወድቁ ሊመስላቸው ይችላል።
ነገር ግን በትዕቢት ሰንሰለት ታስረዋልና መሰበራቸው አይቅርም። ንስኀ ካልገቡ ወደ እግዚአብሔር ካልተመለሱ፣ ክፉ ከመሥራት ካልተቆጠቡ፣ የቀናውን መንገድ ካልያዙ በርግጥ አሰባበራቸውና አወዳደቃቸው እጅግ ታላቅ ነው የሚሆነው።
ብዙዎች አቶ መለስን እንደ ጠላት ነው የሚያዩት። ብዙዎች የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ ላይ ቀንድ እያደረጉ እንደ ጭራቅ ይመስሏቸዋል። (ይሄ ሁሉ ከሚሰሩት ግፍ የተነሳ ነው። ስራቸው ነው እንዲጠሉ ያደረጋቸው)
ነገር ግን አቶ መለስ አሁንም የሚታገስና የሚችል አንድ ወዳጅ አላቸው። እርሱም የሐጢያተኞች ወዳጅ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ነው። ወደዚህ ወደ ቸሩ መድሃኔዓለም ከመጡ፣ ልባቸውን በፊት ካዋረዱ፣ ከታዘዙት ይባረካቸዋል። እርሱም ሐጢያታቸውን ይቅር ይላል። በፍርሃትና በጭንቀት የተሞላውን ሕይወታቸውን ይለውጠዋል። ከራሳቸው አልፈው ለሀገር እርግማን ሳይሆን በረከት ያደርጋቸዋል። ከዚህ በፊት ያበላሹትን የሚክስ ሥራ የሚሰሩ ይሆናሉ።
“እሺ ብትሉ፣ ብትታዘዙ የምድረን በረከት ትበላላቹህ፤ እምቢ ብትሉ ግን፣ ብታምጹ ሰይፍ ይበላቹህል” ተብሎ በትንቢተ ኢሳይስ ምእራፍ አንድ ላይ እንደተጻፈው፣ እምቢ ካሉ፣ ልባቸውን ካደነደኑ፣ ለድሆችና ለተጎዱት የምትፈርደዋ የታላቁ እግዚአብሔር እጅ በተዘረጋች ጊዜ፣ ያኔ አያዝልቅ ነው!!! እግዚአብሔር ከዚህ ይሰውረን! አቶ መለስንም ከመንፈሣዊ እስራት ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ ደግሞ ከሥጋ እስራት ይፍታቸው! ሀገራችን ኢትዮጵያንም ይጎብኛት!
ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
የካቲት 4 ቀን 2002 ዓ.ም.



