ምድረ ቺካጎ (ግርማ ካሣ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ነሐሴ 27 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ አበባ ጊዮርጊስ አካባቢ ነው። ሰዎች በአንድ ቦታ ተከማችተዋል። ግርግር ነገር ይታያል። በመንገድ የሚያልፉ አንድ አባት በመኪና ውስጥ አብረዋቸው ያሉትን «ምንድን ነው የተፈጠረው?» ይሉና ይጠይቃሉ። ሹፌራቸው መኪናውን ቀስ አድርጎ እንዲያቆም ያዛሉ። ከሹፌሩ ሌላ አብሯቸው መኪናው ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት ከመኪናው ወርዶ፣ ነገሩ ምን እንደሆነ አጣርቶ እንዲመጣ ይልካሉ። ወጣቱ፣ ፈጥኖ ብዙ ሰዎች ወደ ተሰበሰቡበት ያመራል። እየሆነ የየነበረውን ተመልክቶ ይመለሳል።

 

አንዲት ድሃ ነፈሰ ጡር ኢትዮጵያዊት ውሃ ፈሷት፣ ምጧ በድንገት መጥቶ ትሰቃይ ነበር። ይሄዱበት የነበረውን መኪና አስቁመው፣ የተፈጠረውን ነገር ለማወቅ ወጣቱን የላኩት አባት ደግሞ፣ የልእልት ሳራ ግዛው ባለቤት፣ የአጼ ኃይለስላሴ ልጅ፣ ተወዳጁ ልኡል መኮንን ነበሩ።

 

ልእሉ መኮንን የተፈጠረውን ጠንቅቀው ከተረዱ በኋላ መንገዳችውን ወደ ቤተ መንግስት አልቀጠሉም። ከኋላቸው አጅቦ በሚከተለው ሌላ መኪና፣ በአስቸኳይ ኢትዮጵያዊቷ ተጭና ወደ ሆስፒታል እንድትሄድ ያዛሉ። እርሳቸው በመኪናቸው ይችን መንገድ ላይ የወደቀች ሴት ተከትለው ሆስፒታል ድረስ ይጓዛሉ።

 

ይህ ሲሆን ገና አልተወለድኩም። ስለ ልኡል መኮንን ብዙም አላውቅም። ነገር ግን ድሃ የሚወዱ፣ በህዝብ በጣም ተወዳጅ እንደነበሩ ብዙ ጊዜ ሰምቼያለሁ። የዚችን የነፍሰ ጡሯን ሴት ታሪክ ግን በቅርቡ ነበር የሰማሁት። ልቤ በጣም ተነካ። ከአንድ መሪ ማየት የምፈለገውን ከልኡል መኮንን አየሁ።

 

ልኡል መኮንን የጊዮርጊሱን ግርግር ባዩ ጊዜ «እኔ የምኖረው አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ነው፤ ከኔ ጋር የሚገናኝ ነገር የለም። ጊዜዬን በዚህ ድሃ ሴት ዙሪያ ከማጠፋ በቶሎ ወደ ቢትወደድ እንትና፤ ራስ እገሌ ... ጋር መሄዱ ይሻለኛል» ብለው መንገዳቸው መቀጠል ይችሉ ነበር። ነገር ግን መሪ ማለት፣ የሚመራውን ህዝብ ችግር የሚያይ፣ የሚያውቅ፣ መፍትሄም የሚፈልግ መሆኑን የተረዱ ሰው ነበሩ።

 

ልኡል መኮንን በሴቲቱ ላይ የደረሰውን ችግር በተረዱ ጊዜ ታክሲ እንዲወስዳት ሳንቲም መወርወር ይችሉ ነበር። ነገር ግን መሪ ማለት ለሚመራው ሕዝብ የሚያሰብ፣ የሚመራው ሕዝብን ችግር የራሱ ችግር አድርጎ የሚቆጥር እንደሆነ አውቀው ነበር። በመሆኑም የዚችን ሴት ችግር የራሳቸው ችግር አድርገው ወሰዱት። መኳንንት በሚሳፈሩበት መኪና፣ ይች ምስኪን ድህ ሴት እስከነ ደሟ እንድተቀመጥ አስደረጉ። የራሳቸው ሚስት፣ እህቶች፣ የቅርብ ዘመድ እንደሚንከባከቡት ለዚህ ድህ ሴት እንክብካቤ አደረጉላት። በሰላም ሆስፒታል አደረሷት። ሴቲቱም በሰላም ተገላገለች።

 

ከ19 አመታት በፊት ነበር። አስመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበርኩኝ ጊዜ መድሃኔ አለም የሚባል የኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን አምላክን ላመሰግን እሄዳለሁ። አንድ አባት በዚያ ተቀምጠዋል። እዚያው አስመራ በለመድኩት የተንተባተበ ትግሪኛ ከርሳቸው ጋር ጨዋታ ጀመርኩ። በአስመራ ከተማ ስለሚፈነዳውና ሻእቢያ ከሩቅ ስለሚተኩሰው ሚሳዬል (ያኔ ግራፒ ነበር የምንለው) አነሳን። ትዝ ይለኛል በሚፈነዳው ሚሳዬል ምክንያት ከቴራ ቦሎና አይሮፕላን ማረፊያው አካባቢ (ደቡብ አስመራ) ህዝቡ ቅዬውን እየለቀቀ ወደ መሃልና ሰሜን አስመራ ይፈልስ ነበር። «እንደው እግዚአብሄር ሰላምን ያምጣልን። መፍትሄው እርሱ ብቻ ነው” አልኳቸው እኝህን አባት። እርሳቸውም «ልክ ነሀ፣ ሰላም ነው መፍትሄው። ከጅምሩ ቀውሱና ጦርነቱ በሰላም በንግግር ቢፈታ ኖሮ ብዙ ሺህ ወጣት ባልሞተ ነበር» ሲሉ ስለ አንድ ሰው አጫወቱኝ፤ ጄነራል አማን አንዶም!

 

በአብዮቱ ወቅት ነው። ጀግናውና ዝነኛው የጦር መኮንን ጄነራል አማን አንዶም የደርግ ሊቀመንበር ሆነው ተሾመዋል። በኤርትራ ሻእቢያና ጀበሃ እየበረቱ የመጡበት ጊዜ ነበር። በተለይም በኤርትራ የነበረው ፌደረሽን በአጼ ኃይለስላሴ ከፈረሰ ጀምሮ፣ የመገንጠል ጥያቄ ሥር እየሰደደ የመጣበት ወቅት ነበር።

 

ጄኔራል አማን አንዶም ነፍጥ አንስተው የሸፈቱትን አነጋግረው እያሳመኑ በኤርትራ የተፈጠረውን ቀውስ በንግግር በማሳመን ለመፍታት ትልቅ ጥረት ጀምረው ነበር። ኤርትራ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ አካል እንደሆነች፣ የኢትዮጵያ ስልጣኔ የጀመረው ከትግራይና ከኤርትራ እንደሆነ፣ በሰንአፈ ኤርትራ እንደተወለዱት የአክሱሙ ንጉስ ኤዛና ብዙ ታላላቅ የኢትዮጵያ ነገስታት ከኤርትራ ጋር ትስስር እንዳላቸው፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ከጣሊያኖችና ከግብጾች ጋር በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን (ኤርትራውያንንም ጨምሮ) ደማችው በኤርትራ ምድር እንደፈሰሰ፣ ከኤርትራ ውጭ በመቶ ሺሆች የኤርትራ ተወላጆች ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ በኤርትራ ውስጥ እንደሚኖሩ፣ ህዝቡ እንደተደባለቀና እንደተዛመደ እያሰረዱ ሻእቢያና ጀብሃ የመገንጠል ጥያቄያቸውን ትተው ወደ ሰላም እንዲመጡ እያሳመኑ ነበር።

 

አዲስ አበባ የተቀመጡት፣ አርቆ ማስተዋል የተሳናቸው፣ በግርግር ስልጣን የጨበጡትና ትንሽ እውቀት ይዘው የሚንጠራሩ መቶ አለቆች፣ የሰላሙን ጥረት ቀጩት። የትላንቱ ጀግንነት ተረስቶ፣ የትላንቱ ጥሩ ሥራ አመድ ለብሶ፣ በትግሪኛ ህዝቡን ማናገራቸው እንደ ሐጢያትና ወንጀል ተቆጥሮ ጄኔራል አማን አንዶም «የወንበዴ ረዳት» ተደርገው ተወሰዱ። አዲስ አበባ አይሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው ቤታቸው በግፍና በጭካኔ ተገደሉ።

 

ጦርነት ከተፈለገ በኢትዮጵያ ታሪክ ነበሩ ከሚባሉ ታላቅ የጦር መሪ አንዱ ጄኔራል አማን አንዶም ነበሩ። ጦር መርቶ፣ በጦርነት ድል ማድረግ የለመዱና የሚችሉ የወታደራዊ አመራር ብቃት የተላበሱ ነበሩ። ነገር ግን፣ በተለይም የራስን ወገን በጠመንጃና በመድፍ ከማስፈራራት እንዲሁም በጉልበትና በጡንቻ ሕዝብን ከማስገበር ይልቅ፣ ትሁት ሆኖ በንግግርና በማሳመን የሚገኝ ውጤት ዘለቄታ ያለው መሆኑን የተረዱ ሰው ነበሩ። «ጠመንጃ ያነሳውን ብትገድለው ነገ ልጁ ደግሞ ይነሳባሃል። ጠመንጃ ያነሳውን ግን አሳምነህ ወዳጅ ብታደርግው ነገ ልጁ የልጅ ልጁ ወደጆችህ ይሆናሉ» በሚል እምነት ነበር ያኔ በሰላሙ ሃሳብ የተንቀሳቀሱት።

 

የልኡል መኮንን እና የጄነራል አማን አንዶምን ምሳሌ ያለ ምክንያት አላመጣሁም። አገራችን ኢትዮጵያ ለአመታት ያጣችውና የጎደላት ነገር ቢኖር እንደዚህ አይነት መሪዎችን ነው።

 

በአሁኑ ጊዜ የትኛው የአገራችን መሪ ይሆን ለተጠቃው፣ ለተጎዳው፣ በግፍ ቀንበር ለሚሰቃየው ወገናችን የሚቆረቆረው ? የትኛው መሪ ይሆን ፍትህ ለተነፈጉት፣ ወንጀል ሳይሰሩ በየእሥር ቤቱ ለሚማቅቁት ወገኖች የሚያስበው? የትኛው መሪ ይሆን ከሼራተን፣ ከቤተ መንግስት፣ በቦሌ መንገድ ካሉ ዳንኪራ ቦታዎች፣ በየቦታው ከተሰሩ የታጠሩ የሃብታም ሰፈሮች ወጥቶ ሴቲቱን ለመርዳት መኪናውን የሚያቆመው?

 

እንደውም እንዳየነው ከሆኑ፣ የኑሮ ውድነት በአንድ በኩል እያሰቃየው፣ በሌላ በኩል ለሕዝባችን በሽታ የሆኑበት አገርን እንመራለን ብለው ስልጣን ላይ የተቀመጡት መሪዎቹ እራሳቸው አይደሉምን? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ጽ/ቤት የተዘረጋው የስልጣን መረብ፣ ህዝቡ በፍርሃትና በሰቀቀን አንገቱን ደፍቶ «እሺህ ጌታዬ» ብሎ በአገሩ እንደ ባርያና ሁለተኛ ዜጋ እንዲኖር አልተደረገምን? የሙስናና የሌብነትን ሌላው መረብ ከላይ ወደ ታች በመዘርጋት ህዝቡን እያስጨነቁት ያሉት አገርን እንመራለን የሚሉቱ አይደሉምን? ከአሁን ለአሁን ለስልጣናችን ያሰጋናል በማለት ለሰላም፣ ለፍትህ የቆሙትን የሚያስሩና የሚያስቃዩ የሚገድሉም እነዚሁ አገርን እንመራለን የሚሉት አይደሉምን?

 

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የት ነው ያሉት ? አንድ ሰው ተኩሰው ገድለዋል ? አምስት ሳንቲም ከሰው ኪስ ሰርቀዋል? በሕክምና ሞያቸው ቀዶ ጥገና ሲያደርጉ መቀስ ሆድ ውስጥ ረስተዋል ? የአሁኑ የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስተር በፓርላማ ሲናገሩ እንደሰማነው፣ «ሌቦች፣ ወራዳች …» ብለው ተሳድበዋል? እስቲ የሚደፍር ካለ ይንገረን … እሥር ቤት እያሉ በበረታባቸው ሕመም ምክንያት እስኪሞቱ ድረስ ለዚያ ሁሉ አመታት በእሥር እንዲሰቃዩ መደረጋቸው ምን ወንጀል ቢፈጽሙ ነው?

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የት ነው ያለችው? ቱሃንና አይጥ በሚሯሯጡበት ቃሊት እሥር ቤት አይደለምን? ምንድን ነው ወንጀሏ? ዳኛ የነበረች ጊዜ ጉቦ በላች? በውጭ አገር ጉብኝት ባደረገች ጊዜ ጦርነት አወጀች ? የአገር ባለስልጣናትን ሰደበች? ገንዘብ ሰረቀች? ሕገ መንግስቱን አልቀበልም አለች? «ይቅርታ ጠይቃ፣ ይቅርታ አልጠየኩም ብላለች፤ አጭበርበራለች» ይላሉ አቶ መለስ። በርግጥስ ብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ አልጠየኩም ብላለች? እንደውም ቃሌ በተሰኘው ጽሁፏ በአገር ሽምግልና ወግ መሰረት «ሕዝብንና መንግስትን ይቅርታ መጠየቄን አልክድም» አይደለምን ያለችው?

 

ታዲያ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በአገራችን ባሉ መሪዎች ዘንድ የምናየው የልኡል መኮንን አይነት ሃዘኔታን፣ ፍቅርን፣ ርህራሄን፣ ሰላምን፣ በጎነትን ሳይሆን ጭካኔን፣ ክፋትትን፣ አረመኔነትን አይደለምን?

 

ከላይ እንደጠቀስኩት ጄነራል አማን አንዶም ጠመንጃ ካነሱ ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ደፈረው ነበር። ጠመንጃ ያነሳው ጠመንጃውን ካስቀመጠማ ምን ንግግር ይባላል። «እምቢ አሻፈረኝ ብሎ የሸፈተንስ ጠመንጃህን አስቀምጥና እንነጋገር” ቢባል ከወዲሁ በጠመንጃ ካልተሸነፈ በቀር እሺ ሊል አይችልም።

 

አቶ መለስ በቅርቡ ለሰላም እንደቆሙ ገልጸውልናል። ከግንቦት ሰባትና ከኦነግ ጋር ለመነጋገር ፍቃደኝነታቸው አሳውቀዋል። «በሕግ መንግስቱ አምነው፤ ሕገ መንግስቱን ለመከተል ፍቃደኛ እስከሆኑና በሰላም ለመታገል(ጠመንጃቸውን ለማስቀመጥ) እስከወሰኑ ድረስ» እነ ኦነግ አገር ውስጥ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ነው የጠቁሙት።

 

መቼም የሰላም ሃሳብን የሚጠላ የለም። ከማንም የምጣ፣ ማንኛውም የሰላምና የእርቅ ሃሳብ የሚደገፍ ነው።፡ነገር ግን ይህ የአቶ መለስ የሰላም ሃሳብ፣ ገና ከአቶ መለስ አንደበት እንደወጣ ያኔውኑ፣ እራሳቸው አቶ መለስ በተግባራቸው ሽረውታል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታለች ወይ ተብለው ሲጠየቁ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ የሕግ ጉዳይ እንደሆነ ነበር የገለጹት።

 

እንዴት ተደረጎ ነው ታዲያ በሰላም የሚታገሉትን እያሰሩ፣ በውጭ ያለውንና ነፍጥ ያነሳውን ተቃዋሚ፣ አቶ መለስ ዜናዊን አምኖ ነፍጡን የሚያስቀምጠው? እንዴት ተደረጎ ነው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ቃሊቲ እየማቀቀች፣ በሰላም ይታገሉ የነበሩት እንደ አቶ በቀለ ጂራታ ከአገር እንዲሰደዱ እየተደረገ፣ የኦነጉ አቶ ዳዎድ ኢብሳ ወይንም የግንቦት ሰባቱ ዶር ብርሃኑ ነጋ፣ የአቶ መለስን የሰላም ጥሪ አክብረው በሰላም ለመታገል አገር ቤት የሚገቡት?

 

እንግዲህ አቶ መለስና ጓዶቻቸው በርግጥ ለሕዝብ እናስባለን፣ ለድሃ እንቆረቆራለን የሚሉ ከሆነ፣ በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን በርግጥ ፍላጎት ካላቸው፣ በሥራቸው ያሳዩን። ፈረንጆቹ «ዌር ኢዝ ዘሚት» እንደሚሉት ወሬውና ጩኸቱ፣ ጋዜጣዊው መግለጫ ይብቃና በፖሊሲና በተግባር የተጨበጠ ነገር ያሳዩን።

 

የፊታችን አዲስ ዓመት መልካም አጋጣሚዎች ከፍቶላቸዋል። ካሉበት አጥር ወጣ ብለው የጊዮርጊስን ግርግር መመልከት ይኖርባቸዋል። በሰላዮቻቸው ፊት ሳይሆን በጓዳ በሕዝብ ዘንድ የሚነገረውን ማዳመጥ መቻል አለባቸው። የሕዝብን ልብ ትረታ የያዘችውን ዳግማዊት ጣይቱ ብጡል ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በአስቸኳይ መፍታት ይኖርባቸዋል። የልኡል መኮንን አይነት ርህራሄና የድሃ ፍቅር ልባቸውን ሊሞላ ይገባል። ጄነራል አማን አንዶም ጦራቸውን ወደ ሰገባው ከተው በንግግርና በውይይት በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት እንደሞከሩት ሁሉ፣ እነርሱም በሕዝቡ ላይ የጫኑትን የፍርሃትና የጭቆና፣ የጡንቻ የጉልበት አገዛዝ አቁመው፣ እራሳቸውን በሕዝብና በታላቁ እግዚአብሄር ፊት አዋርደው፣ የሰላም የወንድማማችነት፣ የመከባበር ባህል እንዲሰፍ ጉልህ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባችዋል።

 

ላለፉት አመታት የተመኘነውና ተስፋ ያደረግነው አልሆነልንም። በደስታ አመቱን ጀምረን በሃዘን ነው ያጠናቀቅነው። የ2002 ዓመትን ከጥቂት ቀናት በኋላ እንሰናበተዋለን። እንደ 2002 እና ያለፉት አመታትስ 2003 ዓ ምን አያደርግብን! በዚህ አዲስ ዓመት እግዚአብሄር ቸሩን ያሰማን!

መልካም አዲስ ዓመት!


ምድረ ቺካጎ

(ግርማ ካሣ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ