አትክልት አሰፋ (ቫንኩቨር - ካናዳ)

አራት ኪሎ አካባቢ ትንሽ ቡና ቤት ያላቸውና ቁም ነገርን ጣል በማድረግ ዝናቸው የናኘ እናት በጠባብ የመጠጥ ቤታቸው ውስጥ ሁለት ጠጭዎች ተደባድበው ወደ ጣቢያ ለምስክርነት ተጠርተው ያያቸው የመቶ አለቃ በዝና ያውቃቸው ኖሮ፤ የሚናገሩት የማያጡትን እናት እያየ ‘እማማ ምነው? ምነው?፤ እንዴት ቤትዎ ውስጥ ጠብ ሊነሳ ቻለ?’ ቢላቸው “አረ ዝም ብለው ነው ልጄ ቤቴን ታውቃት የለ እንኳን ለጠብ ለፍቅርም አትመች” አሉት ይላሉ። ዛሬ በየአረብ ሀገራቱ እየተፈጠረ ያለው የህዝብ የነጻነት ጥያቄ ነገ ከጥቁሮቹ ቤት አይገባም ብሎ እጅን ማጣጠፍ የሚቻልበት ሰዓት ላይ አይደለንም። የአለም የፖለቲካ አዙሪት ያለ ህዝባዊ ይሁንታ በኃይል ብቻ ይዘለቃል የሚባልበት ዘመን አክትሞለታል ማለት ይቻላል። አሁን አሁን መንግስትን ለመገልበጥ የሟች ቁጥር እንደጥንቱ፤ እንደዚያ ዘመን በመቶ ሺህዎች መቁጠር የለም። እድሜ ለቴክኖሎጂ። ህዝብ በቃ ካለ ነገ ስራ አልገባም ብሎ ለማመጽ ደቂቃ የማይወስድበት የስልጣኔ ዘመን እየመጣ ይመስላል።

 

ይህ የአረቦች ነውጥ የአለምን ቀልብ ከማዋለሉም በላይ ገዥዎች ኑሮን እንዳዲስ ለመመስረትና በሰላም ለመሰናበት እንኳ ጊዜ ያጡበት ሁኔታ ነው የምናየው፤ እንደሊቢያው ጋዳፊ ማንቁርቱን ሲያዝና ጣር ሲተናነቀው ‘እንደንግስቲቷ ሆኘ በክብር ልቀመጥ’ ብሎ በነፍስ ውጭ በነፍስ ግቢ ሰአት መቀባጠር ምን ያህል አምባገነንነት አዋራጅ ብቻ ሳይሆን የፈሪዎች መገለጫ መሆኑን አሳይቶናል።

 

አንድ ፖለቲካ አይነካካኝም የሚል የቅርብ ወዳጄ ጋር ስለአረቡ ‘ነውጥ’ ስናወራ ‘አምባገነኖች እኮ አንድ ናቸው’ አለኝ አስቡት እስኪ መለስ ከሙባረክ፣ ጋዳፊ ከሳልህ፣ ሙጋቤ ከአልበሽር፣ ሙሶቬኒ ከኢሳያስ… በምን ይለያሉ?

 

ሁሉም ውስጥ አንድነት አለ፣ መመሳሰል አለ፣ የጋራ ማንነታቸውን ታያላችሁ፤ ሁሉም ከ20 ዓመት በላይ ህዝብን አሰቃዩ፣ ሁሉም አገዛዛቸው በሙስና የተዘፈቀ፣ ሁሉም በረሀብ ህዝባቸውን የቀጡ፣ ጠቅላላቸውም ሃብት ያካበቱ፣ ዘር ወይንም ዘመዳቸውን በሀብት ያጥለቀለቁ፤ ማናቸውንም ስናይ የሰው ደም በእጃቸው የሚንጠፈጠፍ፣ ህዝብን የሚንቁ፣ ጸያፍና ደፋር ንግግር ካፋቸው የማይለይ…፤ የመኖሪያ ስልታቸው ህዝብን መከፋፈል፣ ማጣላት፣ ማጋጨት፣ መግደል፣ ማሰር፣ ማሰደድ አንድነታቸው ነው።

 

መለስ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲ ብቁ አለመሆኑንና በሂደት ላይ ያለ መሆኑን በነገረን በ6 አመቱ ሙባረክም ግብጽ ለዲሞክራሲ ዝግጁ አለመሆኗን ቀባጠረ፤ ጋዳፊ አልቃይዳ አደንዛዥ እጽ የሰጣቸው ህጻናቶች ናቸው ሰልፍ የወጡብኝ ያለን መለስ አደገኛ ቦዘኔ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የበረንዳ አዳሪ ህጻናትን ሰብስበው… ምናምን.. ከሚለው በምን ይለያል?።  

 

ሞታቸውም ስደታቸውም ውርደታቸውም ይመሳሰላል፣ መንግስቱን እንይ፣ ቤን አሊም አለ፣ ሙባረክ ተከትሏል፤ የጋዳፊን ያሳየን ፣ የመለስን ያፋጥነው፣ የሙሴቬኒን መስማታችን አይቀርም፣ የሁሉም ጣር አንድ ነው በተለያየ መልኩ የሚገለጽ።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የቱኒዚያው፣ የግብጹና የሊቢያው አይነት ህዝባዊ የነጻነት ጥያቄ ሊቀሰቀስ እንደሚችል የሲአይኤ ቱባ ቱባ ባለስልጣናት የያዙትን ዶሴ ይዘው ተቃዋሚዎችን ለማነጋገር በመናገሻችን መሯሯጣቸው ብቻ ሳይሆን የመለስ ሰዎች እንደ እስክንድር ነጋ ያሉትን ጸሀፊያን ባደባባይ ‘አንተን ማሰር ሰልችቶናል’ የሚያስብል ጭካኔ ላይ መሆናቸው በቂ መረጃ ነው። ወረድ ካልንም አልጄዚራ የተባለውን የቴሌቭዥን ጣቢያ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች እንዳያሳዩ በህወሀት/ኢህአዴግ የደህንነት ሹሞች ምክር መጀመሩም ሌላው አሳሳቢ ውጥን መኖሩን የሚያመላክት ይመስላል።

 

እኔ የምለው እኒህ የወያኔ ሰዎች አንድ ግለሰብ ለ20 አመታት ሲገዛ፤ አንዳንዶቹም ሰላሳ ሲደመር አመታት ሲገዙ፣ ሲያሽከረክሩ አይሰለቻቸውም፤ ምርር አይላቸውም። ድሮ ድሮ ነገስታት ረዥም ጊዜ ቢገዙ ትግስቱ አለ፣ የቦታ ርቀቱም ይስተዋላል፣ ብልህነቱም አልጠፋ፣ የንቃት ጉዳይም አለ፣ እውነት እንነጋገር ከተባለ ቅንነትንም የተሸከሙ ናቸው። ከማሰራቸው በፊት ሽምግልና ይቀመጣሉ፣ ያስመክራሉ፣ ይመክራሉ እንጂ ያይንህ ከለር…. የሚሉ አልነበሩም።  

 

መቸ? እና እንዴት? ሚለው ጉዳይ ባይታወቅም ይህ ህዝባዊ አመጽ መነሳቱ አይቀርምና መደረግ ስለሚገቧቸው ጉዳዮች መወያየቱ መልካም ነው። አንዱ ወዳጄ ምክር ጀምሮ አስረኛውን ትቶታል እኔ አስርን አንድ ልበልና ልቀጥል።

 

አንድም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩት ዜጎች ድርሻ ምንድነው፣ በሀገርና በውጭ የሞኖሩ የፖለቱካ ድርጅቶች ሚና ምን ይምሰል፣ የሚድያ ተዋጽኦና የሚያደርጉት ሙያዊ ጥረት ስኬታማ እንዲሆኑ ስለማድረግ፣ ይህ የህዝብ ጥያቄ የትኛው ክልል መጀመሩ ውጤታማ ይሆናል።… ብዙ ሊጠቀሱ የሚገባቸው እውነቶች አሉ።

 

የቀጠልን እንደሁ ከአሁን በፊት ካየናቸው ችግሮች በመነሳት ይህንን ህዝባዊ  ያቄ ለማክሸፍ ወያኔ/ኢህአዴግ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ታክቲኮች በሚገባ ተበጥረው መታየትና መረዳት ብልህነትን ያሳያል። መለሰ ዜናዊና አጋሮቹ ስልጣናቸውን አሳልፈው ላለመስጠት የማያደርጉት ነገር የለም። በጭካኔያቸው የታወቁ ናቸው። በሱዳን በረሀ ጠዋት ሶስት አራት ልጆቿ በርሀብ ሞተውባት የቀበረች የትግራይ እናት ማታ ‘ጓይላ’ ጭፈራ ውጭ ብለው የሚያስደንሱ ናቸው። እነኝህ ሰዎች ሴትን አስደፍረው ከወለደች በኋላ ልጇን እንዳታይና ልጁን ጨካኝ አድርገው ለማሳደግ ትግስት ያላቸው ጉዶች ናቸው፣ እኒህ ፍጥረቶች ለስልጣናቸው መፈጠር ዋልታ የነበሩ ጓዶቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከማጥፋት ወደኋላ ያላሉ አረመኔዎች ናቸው። ከአምስት አመት በፊት እንኳን ሀሽሽ አስጭሰው በጎረመረሶች ያስደፈሯትና ከፖለቲካ ድራሿን ያጠፏት ሴት ስንቶቻችንን ሲያንገበግበን ቆይቷል፣ አንድ የቅርብ ወዳጄ ዘመድ የሆነ የባንክ ባለስልጣን ቤቱ ሄደው አይኑ እያየ ሰው ገድለውበት አእምሮውን እንዲስት ያደረጉ ወረበሎች ናቸው። ይህ የሚያስረዳው ታዲያ ጓዴ እንደሚለው ፊታችን የሚገደሉ ሰዎችን ያዘጋጁ ፍጥረቶች ናቸው።  ለዚህም ነው እነመለስ ስልጣናቸውን ለማቆየት ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ቀዳዳ መድፈን ግድ የሚለው።             

  

 

ሶስተኛ ከዘለቅን ህወሀት /ኢህአዴግ የጎሳ መከፋፈልን እንደዋና መሳሪያ ስለሚጠቀምበትና በተለይም አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ ጉራጌ፣ አኝዋክ፣ ስልጤ የሚለውን አፍ መፍቻውን መጠቀሙ የማይቀር መሆኑን በመመልከት ሁሉም ዜጎች በእኩልነትና ከብሄራቸው በፊት ኢትዮጵያዊነት በተለይ የትግራይ ሰዎች በቂ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያለምንም አማራጭ ተግቶ መስራት አስፈላጊነት መታየት አለበት።

 

ለዚህም እንደ ትንሽ ምሳሌ 97ቱን ምርጫ መጨንገፍና ለወያኔ ስኬት ዋናና ጠንካራ ድጋፉ የ97ቱን ምርጫ ያለምንም ማመንታት ቅንጅትን የመረጡና የለውጥን አማራጭነት የተረዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የትግራይ ተወላጆች ወያኔ ባራመደውና ተራ መሆኑ ግልጽ በሆነው የአቶ በድሩን ወያኔዎችንወደመጡበት እንመልሳቸዋለን’’ ንግግር እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ምን ያህሉን የአዲስ አበባ ነዋሪ የትግራይ ተወላጅ ስጋት ውስጥ እንዲገባ እንዳደረገና እውነት ነው ብለው እንዲያምኑ፣ በዘር ጥላቻ ተተርጉሞ እንዲሰራጭ በወያኔ የፕሮፓጋንዳ ባለሙያዎች ሆነ ተብሎ መሰራጨቱ የሚዘነጋ አይመስለኝም።

 

ያዲስ አበባውን ብቻ ሳይሆን እዚህ ውጭ ሀገር የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን ሳይቀር ራሳቸውን እንደመከላከል እንዲያዩት ቅስቀሳው ኃያል ነበር። የትግራይ አካባቢ ተወላጅ ምሁራንና የፖለቲካ  ሰዎችም  እነ / አረጋዊ በርኸ ሳይቀሩ ባደባባይ ይህንን በመለስ የፕሮፓጋንዳ ባለሙያዎች የተጠረበ ንግግር ቦታ ሰጥተው ሲያብጠለጥሉት ተስተውለዋል። እንዲህ አይነት ፕሮፓጋንዳ እንደነ አቶ አረጋዊ ያለ ሰው ጆሮ ውስጥ ገብቶ ቦታ ማግኘቱ እጅግ ያሳዝናል።

 

ቀልድም ሆነ ቁምነገር በሁሉም ዘር ላይ በህንዱም፣ በቻይናውም፣ በነጩም፣ በጥቁሩም በግለሰቦች አሁንም ድረስ ይነገራል? በጉራጌው፣ በኦሮሞው፣ ባማራው፣ በሀደሬው በከንባታው በሁሉም… አሁን አሁን ስለትግሬ መናገር ለምን የትግሬ ጠላት፣ ትግሬ አይወድም የሚሉ የበታችነት መገለጫ ስያሜ እንደሚያመጡ አይገባኝም።

 

ጉራጌው በራሱ ሲቀለድና ሲቧለት አብሮ እየሳቀ፣ አማራውም ኦሮሞውም እንዲሁ ካደረገ ትግሬው ለምንድነው የሚቆጣው? አንዱ የተበሳጨ ፖለቲከኛ እንደው እንበልና አዲስ አበባ ውስጥ ባለስልጣን በሆኑ የትግራይ ልጆች የሚሰራው ቡጥቦጣ አበሳጭቶት ‘ትግሬ ይውጣ’ ቢልስ እንደእውነት ተቆትሮ ድፍን ትግሬ በቁጣ መንገብገቡን ምን አመጣው፤ በዋናውና በችግር ጊዜማ አድዋ ሄዶ የሞተው የመሀል ሀገሩ ሰው አይደለም እንዴ? ችግር ሲመጣማ ከሻእቢያ ጋር ሲሞዳሞዱ የነበሩት የትግራይ ነጻውጭዎች አዲሳባ ዳንኪራ እየመቱ ሲያቃጥሉት የኖረው የመሀል ሀገር ሰው አይደለም እንዴ ሀይደር ተመታ ሲሉት ጥቃቱን ትቶ፤ ቂም ሳይቋጥር… ሆ ብሎ የተነሳው? በነገራችን ላይ ትግራይ ‘በሻቢያ አውሮፕላን’ ስትመታ እግሩ የተመታ ህጻን ልጅ አቅፎ ለእርዳታ ይሯሯጥ የነበረ ወጣት ከህሊና አይጠፋም፤ እስካሁን የሚያቆስለኝ ግን ያ የተጎዱ ህጻናትን ይረዳ የነበረ ጀግና ወጣት በሁለተኛው የአውሮፕላን ጥቃት መገደሉን መስማቴ ነው። ያንን ያየ የመሀል ሀገር ወጣት ለነገ አላሰበም፤ ባድመ ሄዶ ተማገደ፤ ዛላምበሳ ላይ ደሙን አፈሰሰ፣ አስከሬኑን የተከዜ ወንዝ ወሰደው። ጥቃቱን እንደጥቃት አይቶ ራሱን ለሞት ሰጠ። ምነው ዛሬ ትግራይ ዝም አለ? ምነው መሀል አዲስ አባ ጥይት በልጆች ግምባር ሲከተት አስቻለው፣ ምነው በኦጋዴን፣ በሶማሌ፣ የሚፈሰው ደም አልታይ አለው፣ ምነው ህዝብ ሲበደል፣ ሲታሰር ሲሰደድ ጸጥታ ሆነ ምላሹ። የትግራይ ሰዎችን አስተዋጽኦና መስተጋብር፣ አስፈላጊነት በራሱ በትግራይ  ምሁራንና ፖለቲከኞች  ከትግራይነት በላይ ኢትዮጵያዊነት በውስጣቸው እንዲሰርጽ ተግቶ መስራት በዋናነት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም። የመለስ ወሬኞች ምንም ይበሉ ምን በፕሮፓጋንዳቸው ላለመሸነፍ ቆርጦ መነሳት ግድ ይላል።

 

 

 

ወደ አራት ስንዘልቅ ደግሞ ወደራሳችን ተመልክተንገና ባርቆ ዘምቦ…’ እንዳለው ያገሬ ሰው ሽሚያ ላይ የሚሯሯጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሽቅድምድም ነጻ ሆነው ለዚያ ህዝብ ነጻነት በጥንቃቄ እንዲያስቡና ገና ለገና ከድል በኋላ ማን? የሚለው የችኮላና  ጽሞና  የጎደለው አካሄድ  እንዲነቀስ ብርቱ  ክትትልና ምክክር ማድረግ በዋናነት ሊታይ ይገባል። አምስት ብየ ልቀጥል…።

 

ሁላችሁንም ያንጨረጭር ይሆናል እንጂ በእርግጥ  እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ የሚኖረው ህዝብ እንደ ቱኒዚያ፣ ግብጽና፣ ሊቢያ ህዝብ አንጀቱ እርር ብሎ በቃኝ! ከዚህ በኋላ እምቢ ለነጻነቴ የሚልበት ሰዓት ላይ ነውን? እርር እንዳትሉብኝ ለስለስ አድርጌ ላብራራው

 

በአሁኑ ሰዓት ወያኔ ህዝቡን ለማረጋጋትና ነውጥ እንዳያመጣበት በመስጋት  መስላል ደመወዝ ጨምሯል፣ ዋጋ ንረት አብዛኛውን ገበሬ የሆነውንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች አስጨንቋል በማለት ለአጭር ጊዜም ቢሆን እርጋታ እንዲያደርጉ በሚያደርግ መልኩ ለማቃለል እየተፍጨረጨረ ነው። በእርግጥም ይህ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ቢገባኝም የህዝብ ትዝታ አጭር እንደመሆኑ የተወሰኑ ለነጻነት ጥያቄ የሚተናነቁ ሰዎችን ማለትም ባብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችን ሊከፍልና፣ የሀይል ሚዛን ሊያሳጣ ይችላል የሚለውን ስጋቴን ማንሳት ፈለኩ።

 

የሚጨመሩ ነጥቦችን ጨማምረን ወደ ዋናው መቼ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ አሁን ከሆነ ግዴታ መጀመር ያለበት አሁን ነው። ማዕቅ ጨርቅ የለውም፤ ወደ ሀገር ቤት ነው ጉዟችን። ማለቴ የአተገባበር ቅደም ተከተላችንን መከተል ማለት ነው። የኛ አካሄድ እንደ አረቡ አለም ላይሆን ይችላልና የራሳችንን መንገድ በማቀናጀት ፍጹም ሰላማዊ ሊሆን በሚችልና የአለሙ ማህበረሰብ ሊረዳን በሚችልበት መልኩ ካልተጓዝንና አሜሪካ በጋዳፊ ላይ አፏን ለመክፈት ሳምንት እንደወሰደባት ሁሉ ለኛም ቢሆን ትግስትን የተጎናጸፈ አካሄድ ማጥናት ይበጃል።

 

ስድት መጥተናል፤ ይህ ድርጊት የሚሰጠው ጊዜ ካለና ሁለት ሶስት ወር የሚቆይበት ሁኔታ ካለ አሁንም ስራ የሚጀመረው አሁን ነው። እንዴት? ለሚለው የአረቡ አብዮት በመገናኛ ብዙሀን እጅግ በጣም እጅግ እገዛ አግኝቷል። በተጨማሪም አረቡ በኢንተርኔት፣ ስልክ የማህበራዊ ህይወት እለታዊ መገናኛ ዘዴዎች፤ ፌስ ቡክን ይጠቅሷል ተጠቃሚ የሆነው ከእኛዎቹ ይልቃል። ስለሆነም ባለችን ጊዜ ተጠቅመን ስራ ለመጀመር በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቻችን የኢንተርኔት ተጠቃሚ፣ የቲዩተር አባል፣ የቴክስት ባለሙያ፣ በተለይ ኢሳት የተባለውን ቲቪ ተከታታይና የሳተላይት ዲሽ ባለቤት ማድረግ የራሱን ቤተሰብ በመርዳት ተመልካች እንዲሆኑ ማድረግ እዚህ ውጭ ሀገር ያለን ሰዎች ከፍተኛ ሀላፊነት ነው፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚደርሱ ራዲዮኖች እንዲደመጡ ማበረታታት  በተጓዳኝ ጣቢያዎቹ ጣፋጭ መሰናዶችን እንዲያቀርቡ ማድረግ፤ አሰልቺ ከሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ፍጹም ልዩ አቀራረቦችን ከመከተልም በላይ የሙሉ ሰአት ሰራተኞች እንዲኖሩትና ከኢቲቪ ፕሮግራሞችም ሀገር ቤት ያለው ህዝብ የሚከታተላቸውን ፕሮግራሞች በተለይ አይዶል፣ ድራማና የመሳሰሉትን ቀጥታ ሊያስተላልፍ የሚችልበትን ትልም መቀየስ የተመልካችን ትኩረት ከመሳብ አኳያ እገዛው ብዙ ይመስለኛል።  ራዲዮኖቹና ቲቪው በጥንካሬና በሀይል እንዲሰራ ሰፊ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ላይ የተጠናከረ ስራ መስራትን በዋናነት ማየት ግድ ይላል።

 

ሰባተኛው መጣ፤ የህዝባዊ አመጹ የሚጀመር ከሆነና ውጭ ያለው አጋዥ ከሆነ ከስሜታዊነት የጸዳና ግብታዊ አካሄድን ከቅንጅቱ ዘመን ተምረን ሁሉም በሙያውና በችሎታው ለመስራት መትጋቱ አስፈላጊ ሳይሆን አይቀርም። ሰልፍ በሚዎጡና በማይወጡ መካከል የኢትዮጵያዊነት ሰጭና ነሽነት ወይም የባለቤትነት ጭፍን አካሄድ በተለይ ቀስቃሽ ወይንም በአስተባባሪ ወገኖች እንዳይንጸባረቅ በቂ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መስለው ይታዩኛል። በቅንጅት ዘመን በእውነት ሀገራቸውን የሚወዱ ነገር ግን ህዝብ ጋር ያላቸው አቅርቦት ሰውን የሚያሸሽ ባህሪ ያላቸው ግለሰቦች ምን ያህል የትግሉን ጎዳና እንዳራቆተው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነውና የሞራል ሰብእናቸው ያልተናጋ ወገኖች አስፈላጊ ይመስሉኛል። እንደኛ ባደባባይ ባይወጡም ጓዳ ጓዳውን ስለዚያች ሀገር የሚጨነቁ፣ የሚለፉ፣ የሚፍጨረጨሩ፤ ድምጽ ሳያሰሙና እዩኝ እዩኝ ሳይሉ ብዙ ሊያግዙ የሚችሉ ወገኖች ያኔ ብቅ ማለታቸው አይቀርምና በድረ ገጽና ፓልቶክ ድምጹ የሚሰማው ወገን ራሱን አንደኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ብዙ የሚባለውንና በመጮህ የማይታወቀውን ህዝብ እንዳያስቀይም ስጋቴን መደበቅ አልቻልኩም። ካልሆነ አሁን ሀገራችን ያለችበት ደረጃ እንኳን ለጠብ ለፍቅርም አትመች ነው ያሉት የአራት ኪሎዋ…።

 

ቸሩ ቸር ያሰማችሁ   

 

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ