ክቡር ሚኒስትር (ከሪፖርተር ጋዜጣ)
[በሥራ ምክንያት ውጭ አገር በሔዱ ቁጥር ክቡር ሚኒስትሩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ገብተው በእውቀታቸውና በገንዘባቸው እንዲሠሩና የልማት አጋር እንዲሆኑ ይወተውታሉ። አንድ የዲያስፖራ አባልም ይህን መልዕክት ተቀብሎ ከወንድሙ ጋር አንድ ፋብሪካ ለማቋቋም በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል። ያጋጠመውን ሁሉ በየጊዜው ለክቡር ሚኒስትሩ ይነግራቸዋል]
- ሃሎ! እሺ እየተቀላጠፈልህ ነው አይደል?
- ኧረ ችግር ነው ክቡር ሚኒስትር። እዚህ አዲስ አበባ የሚኖር ወንድም አለኝ፤ ፋብሪካውን ለማቋቋም ያሰብነው ከእሱ ጋር ነው። በዚሁ መሠረትም እሱ መሬት ወስዶ ነበር። ግን ...
- ግን ምን?
- የተሰጠን መሬት ለሌላ ሰውም እንዳለ ተሰጥቷል። ለማልማት ብዬ የመጣሁ ሰውዬ አሁን እንደሌባ ተከስሼ ፍርድ ቤት እውላለሁ።
- ለምን ትከሰሳለህ?
- መሬቱ ለእኛም ለሌሎችም ካርታ ተሠርቶ የተሰጠ ስለሆነ ሌሎቹ የእኛ ነው ብለው ከሰሱን።
- አይዞህ ልማቱ ይደናቀፋል ብለህ አታስብ ይፈታል።
- ኧረ ልማቱ በቀረና ከክስ ነፃ በሆንና የዱሮ ሥራችንን ባከናወንን።
- አይዞህ ይፈታል።
- ይኸው ፍርድ ቤት ስመላለስ ስድስተኛ ወሬ ነውኮ።
- አይዞህ ይፈታል።
- እስቲ በተስፋ እጠብቃለሁ።
- ለመሬት አስተዳደር ኃላፊውም፣ ለቦርድም ማመልከቻ አቅርብ።
- ክቡር ሚኒስትር አቅርቤያለሁ፤ እያዩት ቢሆንም አንድ ከታች ያለ ሰውዬ ቦርዱና ኃላፊው ሲያሰጡህ አያለሁ ብሎኛል።
- ምን ለማለት ፈልጎ ነው?
- ጉቦ ስጠኝ ማለቱ ነው። ሌሎቹ ስለሰጡት በጉቦ አሰጣጥ እያጫረተን ነው።
- አይዞህ ይፈታል። መንግሥትም እየተከታተለው ነው።
- ታች ያለው መንግሥት እኮ ላይ ያለውን መንግሥት እያታለለ ነው።
- አይዞህ ይፈታል። ደርሰንበታል።
- እሺ አመሰግናለሁ ... ክቡር ሚኒስትር።
- ቻው።
- ቻው።
[እንደገና ከሳምንት በኋላ ተደዋወሉ]
- ምን አዲስ ነገር አለ?
- አዲስ ነገርማ አለ ክቡር ሚኒስትር።
- ጎሽ።
- አዲሱ ነገር የባሰ መጥፎ ነው እንጂ።
- እንዴት?
- መሬት በሕጋዊ መንገድ ከሰጠን መሥርያ ቤት ቢሮውን በመወከል ፍርድ ቤት የቀረበው ነገረ ፈጅ ጉቦ ተቀብሎ የራሱን መሥርያ ቤት በመካድ ሲከራከር ዋለ። ዳኞቹ እስኪገርማቸው ድረስ።
- እናስ?
- እናማ አስረክቡ ተብለናል።
- አይዞህ ይፈታል - ይግባኝ በል።
- ይግባኝ ብለን አያስቀርብም ተብለናል።
- አይዞህ ይፈታል - ሰበር በል።
- እስቲ ሰበር ብለናል ... እናያለን።
- ውጤቱን ንገረኝ ግን አይዞህ ይፈታል።
[እንደገና ከሳምንት በኋላ ተደዋወሉ]
- እሺ እንዴት ሆነ?
- ሰበርም አልሆነም።
- እንዴት?
- እንዲያውም የእኔ ጠበቃ ጉቦ ሰጥተውት እኔን ክዶ ከእነሱ መጣበቅ ጀመረ።
- አይዞህ ይፈታል።
- አይ አሁንማ እንዲያውም ያስመጣሁትን የፋብሪካው ማሽን ልሸጠው ነው።
- እንዳትሸጥ - አይዞህ ይፈታል። መንግሥትም እያየው ነው።
- አይ እስቲ ብቻ አሜሪካ ደርሼ ልመጣ አስቤያለሁ።
- ጥሩ ቶሎ ሒድና ተመለስ።
- እሺ ቻው። መመለሴም ያጠራጥረኛል።
- አይዞህ ይፈታል።
- እሺ ብቻ ቻው ክቡር ሚኒስትር።
[ከሳምንት በኋላ ክቡር ሚኒስትሩ ደወሉ። ያነሣው ሰውዬው ሳይሆን የሰውዬው ወንድም ነበር]
- አቤት!
- የእንትና ስልክ ነው አይደል?
- አዎን።
- እሱን ላነጋግረው አንዴ?
- እስር ቤት ነው ያለው። ጠባቂዎቹ ከፈቀዱ ልጠይቃቸው።
- አንዴ ጠባቂዎቹን ላነጋግር። (አስፈቀዱና ሰውዬውን ማነጋገር ጀመሩ)
- ምነው ምነው አሜሪካ ሔደሃል ብዬ አንተ እስር ቤት ገባህ፤ ምክንያቱ ምንድን ነው?
- እኔ እንጃ አልገባኝም።
- እነሱስ በምን ምክንያት አሰርንህ አሉ?
- በአስቸኳይ ወደ አሜሪካ ልመለስ ብዬ የአውሮፕላን ቦታ ስጠይቅ ሞልቷል ተባልኩ። ነገር ግን በቢዝነስ ክላስ ከፈለግክ ቦታ አለ፤ ግን ዋጋ ያስጨምራል አሉኝ።
- እሺ ...
- የሚጨመረውን ገንዘብ ይዤ አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ ግን የለም። ገንዘብህን ያዘው የቀረ ሰው ስላለ በኢኮኖሚ ክላስ መሔድ ትችላለህ አሉኝ። እሺ ብዬ ገንዘቤን ኪሴ ውስጥ ከትቼ ቦርድ ፓስ ይዤ ገባሁ።
- እሺ ...
- ከዛ ከሁለት መቶ ብር በላይ መያዝ አይፈቀድም ብለው አሰሩኝ። ለቲኬት ዋጋ ጭማሪ የያዝኩት ገንዘብ ነበር።
- ከታሰርክ ስንት ቀንህ ነው?
- ሦስተኛ ቀኔ ዛሬ።
- አይዞህ ይፈታል።
- ለነገሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኛ ገንዘብ ጨምር ስላልነው የያዘው እንጂ ለሌላ አይደለም ብለው ስለመሰከሩ ይለቁኝ ይሆናል።
- እሺ ... በል በርታ - አይዞህ ይፈታል።
[ከሳምንት በኋላ እንደገና ተደዋወሉ]
- ጎሽ አሁን ከእስር ቤት ውጭ ነህ አይደል?
- በዋስ ውጭ ሆነህ ተከራከር ተብያለሁ።
- ደስ ይላል አይደል?
- ምኑ ነው ደስ የሚለው ክቡር ሚኒስትር? የቢዝነስ ክላስ ትኬት ያስጨምራል ብለው የያዝኩትን ገንዘብና አየር መንገዱም አምጣ ብለነው ነው ብሎ የመሰከረበትን ጉዳይ ከሁለት መቶ ብር በላይ ይዘሃል ተብዬ ልታሰር? ልንገላታ?
- አይዞህ ይፈታል።
- አሁንማ ተስፋ ቆረጥኩ።
- ይህ ችግርኮ ይፈታል።
- አሁንማ የሚያስቅ ሌላ ችግር ተፈጠረ ደግሞ፤
- ምን ሌላ ችግር?
- ያስመጣኋቸውን ማሽኖች ያስቀመጥኳቸው በወንድሜ መጋዘን ነበር።
- እሺ ...
- አሁን ወንድሜ ምን ችግር እንዳጋጠመው እንጃ የመጋዘኑ በራፍ ታሽጓል የሚል ለጠፉበት።
- እሺ ...
- ማሽኖቼ እዛ ውስጥ አሉ ላስወጣቸው ብል ታሽጓል፤ ታሽጓል ተባልኩ።
- ስንት ቀኑ ነው?
- ሳምንት ሙሉ ... ማሽኖቼን ማየትና መሸጥ አልቻልኩም።
- አይዞህ ይፈታል እደውልልሃለሁ።
[ከሳምንት በኋላ ተደዋወሉ]
- ድምፅህ ጥሩ አይደለም።
- ምን ጥሩ ይሆናል ክቡር ሚኒስትር?
- አይዞህ ይፈታል እያልኩህ። ቤት ሒድና ተኛ።
- መቼ ቤት አለኝና።
- ያ የማውቀው ቤትስ አንዴ ያሳየኸኝ?
- ትናንት ጧት መጥተው በሦስት ቀን ውስጥ እንድታፈርሱት አሉኝ።
- ለልማት ፈልገውት ይሆናል። ያ አካባቢ ሰባት ፎቅ መሆን አለበት ተብሏል መሰለኝ።
- እኮ እኔም የእናት አባቴ ቦታ ስለሆነ ሰባት ፎቅ ልሥራ አልኳቸው።
- ካልካቸው ታዲያ እንዴት እምቢ አሉ?
- እምቢ አሉ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ግማሹን አፍርሰውታል።
- አይዞህ ይፈታል አትጨነቅ።
- ወይ አይዞህ ይፈታል!
- አይዞህ ይፈታል ቻው እደውላለሁ።
[ከሳምንት በኋላ ተደዋወሉ]
- ሃሎ!
- አቤት ክቡር ሚኒስትር።
- ምነው ድምፅህ ጥሩ አይደለም?
- አሁንስ ድምፄም መንፈሴም ጤናዬም ጥሩ አይደለም።
- ምነው?
- ልጆቼና ባለቤቴ በአሜሪካ ችግር ውስጥ ናቸው። መሔድ ነበረብኝ ግን አልቻልኩም።
- እንዴ ሒድ እንጂ።
- ክቡር ሚኒስትር ከሁለት መቶ ብር በላይ ይዘሃል የሚል የወንጀል ክስ እያለ እንዴት እሔዳለሁ?
- ታዲያ ወንድምህን ለምን አትልከውምና አስፈላጊውን ሁሉ ጨርሶ ለምን አይመጣም።
- እኔም እንደዛ አስቤ ሒድ ብዬው ነበር።
- እና ሔደ?
- ለመሔድ ኤርፖርት ሲደርስ እንዳትንቀሳቀስ የእግድ ደብዳቤ ስለመጣልን ከአገር መውጣት አትችልም ተባለ።
- እ ...
- የሚገርምና የሚያሳዝን ነው።
- አይዞህ ይፈታል - እሺ እደውላለሁ።
[ከሳምንት በኋላ ተደዋወሉ፤ ክቡር ሚኒስትሩ ነገሩ እያስፈራቸውና እያሳሰባቸው መጣ]
- እሺ ምን አዲስ ነገር አለ?
- አባቴ ታሟል - ሆስፒታል ስመላለስ ነበር።
- ምን ሆኑ?
- ለሃምሳ ዓመት የያዘው ቤት በሦስት ቀን ውስጥ ሲፈርስ ልቡም መንፈሱም ቆሰለ።
- ቤቱ ሲፈርስ የት ሔዱ? የት ገቡ?
- ለጊዜው ያለው በአንድ ገስት ሃውስ ውስጥ ነው።
- ምነው እህትህ የተከራየችው ቤት አለ አይደለም ወይ?
- አዎን ግን ውላችንን አቋርጠናል ብሎ ኪራይ ቤቶች ቤቱን ነጥቋታል። እንኳን አባቴ እሷም የምትገባበት አጥታለች። ቤት ኪራይ እየፈለጉ ናቸው።
- ብቻ አትጨነቅ - አይዞህ ይፈታል እደውላለሁ።
[ከሳምንት በኋላ እንደገና ተደዋወሉ]
- ሃሎ ክቡር ሚኒስትር፤ ይቅርታ ደውለው ነበር አላየሁትምና አላነሣሁትም።
- ግድ የለም ምን አዲስ ነገር አለ?
- ይኸውልዎት ክቡር ሚኒስትር ማሽኖቼ ወንድሜ መጋዘን ታሽገው እንደነበር ነግሬዎት ነበር?
- ይለቀቅልኝ ብለህ ማመልከትህንም ነግረኸኝ ነበር።
- አዎን ፍርድ ቤት አመልክቼ ማሽኔን እንድወስድ ታዞልኝ ነበር።
- እና ማሽንህን ወሰድክ?
- ልወስድ ስል ጥቆማ ደርሶናል ተብሎ ፖሊስ መጥቶ እንደገና አሽጎት ነበር።
- ለምን?
- ቀረጥ አልተከፈለባቸውም ብሎ።
- እናስ?
- ከቀረጥ ነፃ የሆነ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዳለው ማስረጃ አቀረብኩ።
- እናስ?
- ሊለቀቅ እንደገና ተወሰነ። ግን ...
- ግን ምን?
- ውጭ አገር እያለ ዋና የመንግሥት ጠላት ነበር የሚል ጥቆማ ተሰጠና አሁን ደግሞ ለየት ያለ ችግር እያጋጠመኝ ነው። እኔ ደግሞ እንኳን ልቃወምና ልደግፍ ፖለቲካ የሚሉት ነገር አልወድም።
- መደገፍም መቃወምም መብትህ ነው፤ ከዚህ ጋር አይያያዝም።
- ተያይዞማ እያሰቃየኝ ነውኮ ክቡር ሚኒስትር።
- አትጨነቅ፤ አትሰቃይ! አይዞህ ይፈታል።
- ክቡር ሚኒስትር አሁን አባባልዎ ቀልድ እየመሰለኝ መጣ።
- እንዴት ቀልድ?
- ብሞትም ‹‹አይዞህ ይፈታል›› የሚሉኝ ይመስለኛል።
- አትጨነቅ - አይዞህ ይፈታል!
[ከሳምንት በኋላ ቢደውሉ ቢደውሉ፣ ክቡር ሚኒስትር መልስ አጡ። ማታ ቤታቸው ገብተው በተደጋጋሚ እየሞከሩ ናቸው። አልተሳካም። እሑድ ጧት ከባለቤታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ ወሬ ይዘዋል]
- ፊትህ ጥሩ አይደለም ምን ሆነህ ነው? ስልክ ደግሞ በተደጋጋሚ ትሞክር ነበር?
- አንድ ሰው ጠፋብኝ።
- ምን ዓይነት ሰው?
- ፋብሪካ ለማቋቋም ከውጭ የመጣ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊ ነበር።
- በደህና ነው የጠፋው?
- ችግሮች ያጋጥሙት ነበር።
- ታዲያ ሚኒስትር ሆነህ ምን ረዳኸው?
- በተደጋጋሚ ‹‹አይዞህ ይፈታል›› እያልኩ አበረታታው ነበር።
- በቃል ነው በተግባር?
- እስቲ ያን ጋዜጣ አቀብይኝ። [ክቡር ሚኒስትር የጋዜጣውን ገጾች ማገላበጥ ጀመሩ። መሃል አካባቢ ሲደርሱ ደነገጡ። ፊታቸው ተለዋወጠ። ባለቤታቸውም ደነገጡ።]
- ምን ሆነህ ነው?
- ይኸው።
[በጋዜጣው ሙሉ ገጽ የወጣ የሐዘን መግለጫ ነበር]
‹‹በዚህ ቀን ተወልደው፣ እዚህ ተምረው፣ እዚህ በእንደዚህ ተመርቀው ውጭ አገር ሔደው ተምረውና ሥራ ጀምረው፣ አገሬን ላልማ ብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው መጥተው ፋብሪካ ለማቋቋም ሲሯሯጡ ባጋጠማቸው ድንገተኛ የልብ በሽታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በስልክ፣ በአካል፣ ከአገር ውስጥም፣ ከውጭ አገርም ላጽናናችሁን ሁሉ ምስጋና እናቀርባለን፤ ቤተሰብ።››
- ሟቹን ታውቀው ነበር?
- አዎን።
- ታዲያ ለቅሶ አልደረስክም ደውልላቸውና አጽናናቸዋ።
- ከአሁን በፊት የለፈለፍኩት ማጽናኛም ዋጋ አልነበረውም።
- ምን እያልክ ታጽናናቸው ነበር?
- ‹‹አይዞህ ይፈታል››



