ታደለ መኩሪያ (April 29, 2008)

ለዘመናት በሕግ ሲተዳደር የኖረን ሕዝብ በየጊዜው ሀገር ወለድ አምባገነኖች እየተነሱ ሲጨቁኑት ብሩህ ራዕይ ያላቸውን ዜጎች ሲያጠፉ ታይቷል።

 

ይህቺን ታሪክ ያላት ሀገር መሪ አልባ ሕግና ሥርዓት የጎደላት መስላ እንድትታይ አድርገዋታል። በቅርቡ በፓርላማና ቀበሌ ማሟያ ስም በሀገር አቀፍ የተካሄደው ምርጫ ጥሩ ምስክር ነው። ‘እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው’ መሰል ምርጫ በማስፈራራት በድብደባና ወከባ ተጠናቋል። ቀደም ሲል ለውድድሩ ቀርበው የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድብደባውንና አፈናውን በመፍራት አቋርጠው ሲወጡ መራጩም ሕዝብ የዜግነት መብቱን እንዳይወጣ ተስፋ ቆርጦ ከቤት እንዲውል ተደርጓል። ይህን መሰሉ ድርጊት እስከመቼ ይቀጥላል? የሕዝቡስ ዝምታ መቼስ ያበቃል?

 

በሀገር ውስጥ በሠላማዊ ትግል ለውጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ድርጅቶች የሠላም ዘንባባ ይዘው በጋራ ተባብረን ሀገራችንን ከኋላ ቀርነት፣ ከረሃብና ሰቆቃ እናውጣት፣ የዘር ክፍፍሉን እናቁም ብለው የወያኔን መንግሥት ቢማጸኑም፤ ጥያቄቸው ከወንጀል ተቆጥሮ ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል። “ድምፃችን ይከበር!” ብለው ሰልፍ የወጡትም በመከላከያው ሠራዊት ከተገደሉና ከቆሰሉ በኋላ የታሰሩት የሕዝብ መሪዎች ከነአካቴው በወያኔ ብሶ ለድፍረታቸው ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርገዋል። እንቢተኝነቱና ትዕቢቱ ምእላተ ሕዝቡን መናቁ ዋና ምንጩ የመከላከያ ሠራዊቱ ተጠሪነቱ ለወያኔው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እንጂ ለሕዝብ ያለመሆኑ ነው።

 

በሰኔና ኅዳር 1997 ዓመተ ምህረት ምርጫውን አስመልክቶ ለተነሳው አንባጓሮ የመከላከያው ሠራዊት ታንክ መትረየስና ክላሽኮቭ ጠመንጃ ተጠቅሞ ጦር ሜዳ መሰል ጭፍጨፋ በወገኑ ላይ መፈጸሙ ያንን የሚያረጋግጥ ነው።

 

ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ነፃ ሳይወጡ የቀድሞው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በተባበሩት መንግሥታት ስር ኮሪያና ኮንጎ ዘምቶ በውትድርና ሞያውና ሥነ-ምግባሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያገኘ ሠራዊት ዛሬ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲሰ አበባ የዓለም ሕዝብ እያየው በታንክና በመትረየስ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ተማሪዎች፣ አረጋውያንን፣ … ወዘተ ተኩሶ ሲገድል ማየት የሚያሳዝን፣ የሚያሳፍር፣ የሚያስፈራ፣ የሕዝብ መከላከያ ሠራዊት ያለመሆኑን የሚያሳይ ነው።

 

የእኛን ዓይነት የምርጫ ውዝግብ በኬንያ በተከሰተ ወቅት የመከላከያው ሠራዊቱ እጁን አላስገባም። ይህም የሚያሳየው የሠለጠነና ደረጃውን የጠበቀ የሕዝብ ሠራዊት መሆኑን ነው።

 

ይህ የወያኔ የመከላከያ ሠራዊት በሥልጠናው ወቅት ያልተገለጸለት ሐቅ አለ። ይሄውም ከታጠቀው የወገቡ ቀበቶ እስከ ቦንብ ጣዩ አውሮፕላን እናት አባቱ ያለጫማ ባዶ እግራቸውን እየሄዱ ከእህቱና ወንድሙ አፍ እየቀሙ በከፈሉት ግብር መገዛቱን ነው።

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ታርዞ፣ ተርቦና ተጠምቶ በውጪ ምንዛሬ የመከላከያ ሠራዊቱን ማስታጠቁ ራሱን መልሶ እንዲያጠቃው አይደለም። ልጆቹንም ወደ መከላከያው ኃይል እንዲቀላቀሉ መፍቀዱ ሃገርን እንዲያገለግሉ፣ ወሰንን እንዲያስከብሩ፣ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲያኮሩት እንጂ፤ ለሥልጣን ጥመኞች ዘብ እንዲቆም አይደለም።

 

በአሁኑ ወቅት በሠላም የሚቀሳቀሱት የፖለቲካ ድርጅቶች የሀገራችንን ችግር በሠላምና በዲሞክራሲ መንገድ እንፍታ ሲሉ፤ እርስ በእርሳችን በአንጡራ ሀብታችን ከውጭ አገር በገዛነው መሣሪያ አንጨራረስ ማለታቸው ነው። ለሥልጣን ሽኩቻ ለሚደረገው እሰጥ አገባ አንድ ወታደር እንኳን አይሙት፤ እርሱም ለሀገር መከላከያ በታጠቀው መሣሪያ በሕዝብ ላይ አያዙር ማለት ነው።

 

ለአንዳፍታ ቆም ብለን ከግንቦት 1997 ዓ.ም. ወዲህ ሕዝቡ በሠላማዊ መንገድ መንግሥት መለወጥ ይቻላል ብሎ ጦርነትን ካወገዘ በኋላ ወያኔ ለሕዝብ ድምፅ አልገዛም በማለቱ ስንት ወገን በሠራዊቱ ተገደለ? ስንት ሠራዊትስ ሞተ? ምን ያህል ንብረትስ ወደመ?

 

ለምሳሌ በኦጋዴን፣ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብ፣ በምስራቅ በአራቱም ማዕዘናት የሚካሄደው ልማት አይደለም ጦርነት ነው። የምንሰማውና የምናየው ጥጋብ አይደለም፤ ረሃብ ነው። የሱማሊያን ወሰን ተሻግሮ የዘመተው የመከላከያ ሠራዊትስ? በለስ ቀናው? በሞቃዲሾ ጎዳናዎች እሬሳው እንደውሻ ሬሳ ሲጎተት ነው የምናየው። ግንቦት 1997 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ውጤቱ ተከብሮ ቢሆን ኖሮ ይህ በደል ይደርስበት ነበርን?

 

እ.ኤ.አ. 1994 ዓ.ም. የአሜሪካ ሠራዊት አባል የሆነ አንድ ግለሰብ እንደዛሪዎቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባሎች በሞቃዲሾ ጎዳና በመጎተቱ ምንም ሳታመነታ ኃያሏ አሜሪካ ጓዟን ጠቅልላ ለመውጣት ተገድዳለች። ይህም የሚያሳየው ለዜጎቻቸው የቱን ያህል ክብር እንዳላቸው ነው። ወያኔ ግን ለሠራዊቱ ግድ የሌለው ገና ሺዎች ሬሳቸው እሰከሚጎተቱ ነው የሚጠብቀው። የመከላከያው ሠራዊትስ ነግ በኔ ያለማለቱ ለምንድነው? ሕዝቡስ ልጆቹን በሰው አገር ልኮ የሚስጨርስበትን የወያኔን መንግሥት ያለመጠየቁ? ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈጸመው የቆራጥ መሪ መጥፋት፣ የእያንዳንዱ ግለሰብ ለመብቱ ያለመቆም ሌሎች በከፈሉት መስዋዕትነት ነፃ እወጣለሁ ብሎ በመታሰቡ ነው።

 

ታደለ መኩሪያ

April 29, 2008

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ