20210302 adwa

እስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ)

(ክፍል ሁለት - ካለፈው ሣምንት የቀጠለ)

ቅዳሜ ረፋዱ ላይ ጀምበር ለመጥለቅ ዳር ዳር ትላለች። የግንቦት አናት ሰርሳሪ ፀሐይ ዘንድሮ በደመና ለዝቦ ነው የሰነበተው። ከእኩለ ቀን አንስቶ የከተማዋ አየር ቀዝቀዝ ብሎ ውሏል። አንዳንዴም መለስተኛ ካፊያ መጠት ሄደት ይላል። 

 

የብሥራተ ገብርኤል ሰፈር ነዋሪ እንደወትሮው የግቢ በሩን ቀርቅሮ በየቤቱ ውስጥ ተከቷል። ትናንሽም ትላልቅም ቤቶች በረዣዥም የአጥር ግንብ የተከለሉ ናቸው። በቁራሽ የእርሻ መሬት ደም ሲቀባባ የኖረ ሕዝብ፣ ከቤቱ ይልቅ አጥሩን አጥብቆ ይሰራል። ውጤቱ ጥሩ አልሆነም። ረዣዥሞቹ አጥሮች በነባሩ የኢትዮጵያዊያን ማሕበራዊ ሕይወት ላይ የቆሙ ግድቦች ሆነዋል። የሰፈርተኛው ትስስር እንደ ፈረንጆቹ የላላ ለመሆን ትንሽ ነው የቀረው። የጥንቱ አብሮነት ለአዲሱ ባይተዋርነት ሸብረክ ብሏል።

 

እንዲህም ሆኖ፣ ኢትዮጵያዊያን አሁንም በሰርጎቻቸው፣ በለቅሶቻቸውና በአምልኮታቸው እንደተሳሰሩ ናቸው። የጥንቱ ዕድር አልተበጣጠሰም። የብስራተ ገብርኤል ነዋሪ አብሮ ይሰርጋል፣ ተደጋግፎ ይላቀሳል፣ ተሰባስቦ ፈጣሪውን ያመልካል።

 

የቅዳሜው የእድር ጡሩንባ ግን፣ ሰፈርተኛውን በእጅጉ ግራ አጋባ። ሰዓቱ ተዛብቷል። ጥሩምባው አየሩን የሰነጠቀው ከረፋዱ 12 ሰዓት ገደማ ነው። ተሰምቶ አይታወቅም። የእድር ጥሪ ከሌሊቱ 11 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ነው። ዛሬ ምን ተፈጠረ? ነዋሪው በጉጉት ከየቤቱ ብቅ አለ።

 

”እድርተኞች፣ ነገ፣ ግንቦት 20፣ ከጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ በመስቀል አደባባይ የሕዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ሰላማዊ ሰልፍ ስለሚደረግ እንድትገኙ ተብላችኋል፣” እያሉ አደበላለቁት የእድሩ ለፋፊ፣ ትከሻቸው ላይ ባንጠለጠሉት የድምፅ ማጉያ።

 

ኧረ፣ እድር ከቶ ስለሕዳሴው ግድብ (የዓባይ ግድብ) ምን አገባው? ሰልፉስ እውነት ለግድቡ ነው ወይስ ለኢሕአዴግ ድል? ማን ይጠየቅ? ማንስ ይመልስ? የብስራተ ገብርኤል ነዋሪ ከንፈሩን በቁጭት እየመጠጠ ወደየቤቱ ገባ። ነውር የጠፋበት ዘመን።

 

ቀበሌዎች በበኩላቸው፣ እያንዳንዱን በር እያንኳኩ ወረቀት በትነዋል፡ ”ከ18 ዓመት በላይ የሆነ እንዳይቀር” ብለዋል። በግዴታ ይሁን በውዴታ አልለየም። በትምህርት ቤቶችም ሲቀሰቀስ ሰነባብቷል። ተማሪዎቹ ግን ከ18 ዓመት በታች ናቸው። ግንቦት 20 አልተነሳም። ለዓባይ ግድብ እንዲወጡ ነው የተነገራቸው። ”ገለልተኛ” የሴቶችና የወጣቶች ማሕበራት ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ረጭተዋል። የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አባላት በቡድን እንዲወጡ ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷል። የቀረ ወየውለት። ለእነዚህ ምክንያት መንገር አላስፈለገም። በቀጭን ትዕዛዝ ግልብጥ ብለው ይወጣሉ። ዝንፍ ቢሉ ጉሮሮዋቸው እንደሚዘጋ ያውቁታል። ለጥቂት ቀናትም የመንገድ ለመንገድ ቅስቀሳ ተደርጓል፣ ትርፉ ከሕዝብ ግልምጫ ብዙም ባያልፍም። ሆኖም፣ አንድም ሰው ትርጉም አለው። በእንጥብጣቢ በርሜል ይሞላል። ስለዚህም፣ በአራቱም ማዕዘን ተወጥሯል።

 

የግንቦት 20 ዕለት፣ የማይናቅ ቁጥር ያለው ሕዝብ በመስቀል አደባባይ ተገኝቷል። አንድ ሚሊዮን ተብሎ የታለመው ግን ቅዠት ሆኖ ቀርቷል።

 

ግልፅ ባልሆነ ምክንያት፣ ሰላማዊ ሰልፉን በቶሎ ለመበተን ጥድፊያ ነበር። በሁለት ዓረፍተ ነገር የምትዘጋ ጥያቄን ግማሽ ሰዓት የሚያላዝኑባት መለስ ዜናዊ፣ የአምስት ደቂቃ ብቻ ንግግር አደረጉ። በ20 ዓመታት ውስጥ አጭሩ ንግግራቸው መሆኑ ነው። አዲስ ክብረወሰን። (ብዙዎች ልምድ እንዲያደርጉት ተመኝተውላቸዋል) በጥቅሉ፣ ሰላማዊ ሰልፉ ሁለት ሰዓታት እንኳን አልቆየም።

 

ለምን?

 

ተቃውሞ ስለተፈራ። መጀመሪያውንም፣ ፈራ ተባ እየተባለ የተጠራ ሰልፍ ነበር። ሕዝብ ወደ አደባባይ ገብቶ አልለቅም ቢልስ? የግብፅ ታሂርር አደባባይ ተፈጠረ ማለት አይደለም እንዴ? ዘንድሮ ሕዝብን በመጨፍጨፍ መበተን አይቻልም። በአረብ ሀገራት አይተነዋል። አደባባይ የተቀመጠ ህዝብን ደግሞ መጨፍጨፍ አያመችም። ኢሕአዴግ መውደቂያውን አመቻችቶ ነበር። አደጋው እነመለስን አልጠፋቸውም፤ ብዙ ያውቃሉ። በሕልውናቸው ቁማር የተጫወቱት፣ አጋጣሚውን መጠቀም የሚችል የተደራጀ ሕዝብ የለም ብለው ስላመኑ ነው። አልተሳሳቱም። የሞከረ እንኳን አልነበረም። ሰልፉ ቶሎ የተበተነው ለምናልባቱ መሆኑ ነው። ማንም ስለምንም መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አይችልም። ያቺ ቀዳዳ መደፈን ነበረባት።

 

ኢኮኖሚዬ 11 ከመቶ አደገ የሚል መሪ ፈገግታ ከፊቱ ሊጠፋ አይችልም። ከዚህ በላይ ብዙ ሊፈልግ አይችልም። የመለስ ፊት ግን ብዙም ሳይፈታ ነው ሰላማዊ ሰልፉ የተጠናቀቀው። ሐሳባቸው ሌላ ቦታ የሄደ ይመስላል። እርግጥ፣ የሀገር መሪ ሆኖ የሚታሰብ አይጠፋም። ቀልብን የሚሰልብ ጉዳይ የሚያጋጥመው ግን፣ አልፎ አልፎ ነው።

 

ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋር ሰሞኑን ተጋፍጦ የሚገኘው ጉዳይ ቀልብን ሊስብ የሚችል ብቻ ተብሎ ሊታለፍ የሚችል አይደለም። አንድ ደረጃ ከፍ ይላል። ቅሌት ቢባል ይመጥነዋል። ፈረንጆች ”Scandal” ይሉታል። መለስ ጭው ብለው የጠፉ ቢመስሉ አይገርምም።

 

8.5 ቢሊዮን ዶላር ከባድ ገንዘብ ነው። ዘንድሮ እንኳን ለኢትዮጵያ ለአሜሪካ ይከብዳታል። ላለፉት 5 እና 6 ዓመታት በኢኮኖሚው ተዓምር አስመዝግበናል እየተባለ፣ ሐገራችን በዚህ ዓመት ወደ ውጭ ከምትላካቸው ምርቶች የምትጠብቀው ከ2 ቢሊዮን ዶላር ትንሽ ነው ከፍ የሚለው። 8.5 ቢሊዮን ዶላሩ ከ4 ዓመታት ድምር ልፋታችን ጋር የሚስተካከል ነው፤ እንደ ሐገር ሆነን። ታዲያ፣ ይሄ ቅሌት መባል ይነሰው እንዴ?

 

ከኢትዮጵያ ላይ ስለተዘረፈው 8.5 ቢሊዮን ዶላር ዛሬ ብዘረዝር የቀባሪ አርጂ ያደርገኛል። ሁሉም ያውቀዋል። ዘረፋው ዜና አይደለም። ዜናው በተባበሩት መንግሥታት በኩል ለመውጣት መብቃቱ። ጥርጣሬያችን አሁን በማስረጃ ተደግፏል። ኢሕአዴግ ከዚህ በኋላ ማስረጃ ሊጠይቀን አይችልም።

 

ከ8.5 ቢሊዮን ዶላሩ ላይ ከ60 እስከ 65 ከመቶ የሚሆነው ገንዘብ ከሀገር የወጣው ከውጭ ንግድ ጋር በተያያዘ መልኩ እንደሆነ በተመድ ሪፖርት ተቀምጧል። የነጋዴዎች እጅ አለበት ማለት ነው። ይሄ ብዙ አያከራክርም። ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ መኖሪያ ቤቶች በአሜሪካ የገዙ ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች እንዳሉ ይታወቃል። ንግዳቸው ግን ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ገንዘብ እንዳሸሹ ግልፅ ነው። ድምር አቅማቸው ግን እምብዛም እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር ነው። (የአላሙዲንን አቅም አያካትትም።) በጣም ተለጥጦ ከ2 እና ከ3 መቶ ሚሊዮን ዶላር አይዘልም። እንዲያውም፣ 400 ሚሊዮን ዶላሩን እንኳን በእነሱ ላይ ብናሳብብ፣ 8 ቢሊዮን ዶላር ይቀራል። ለዚህ ገንዘብ ተጠያቂዎቹ በስልጣን ላይ ያሉት አንዳንድ የኢሕአዴግ መሪዎች ናቸው። ሌላ ተጠርጣሪ የለም። ያለ ቀይ መስመር ደሃ ሀገራቸውን አድምተዋል።

 

ግንቦት 20 ዕለት የመለስን ቀልብ የሳበው ይህ ጉዳይ ነበር ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። መንግሥታቸው ብዙ ብዙ ጥያቄዎች አሉበት።

 


ፀሐፊውን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!