የሰኔ 1997 ጭፍጨፋ ሲታወስ (ወህኒ ቤት የተፃፈ)
እስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ)
ሰሞኑን መፅሐፍ ለማሳተም ታች ላይ እያልኹ ነው። ያልታተሙ ሁለት ሶስት መጻሕፍት በእጄ አሉ። እድሜ ለኢሕአዴግ፣ ለመፃፍ ብዙ ጊዜ አግኝቻለኹ። የተጠቀምኹባቸውም ይመስለኛል፡፡ ለሕትመት የሚገቡት ግን እነዚህ መፃሕፍት አይደሉም። በቂ ምክንያት አለው።
«ለኢሠፓ አባላት እንኳን የተትረፈረፈ ዲሞክራሲ አለባት» ተብላ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተወደሰችው ኢትዮጵያ፣ መፃሕፍትም በነፃ እንዳይታተሙባት የተከለከለባት ሀገር ናት። ዲስኩሩ ሌላ፣ እውነታው ሌላ። ከእውነታው ሰለባዎች መካከል አንዱ ደግሞ እኔና ሠርክዓለም እንገኛለን፡፡ መፃሕፍት እንዳናሳትም ተከልክለናል።
በአጭሩ ላውጋችሁ።
ጊዜው ሐምሌ 1999 ዓ.ም። ከእስር ከተለቀቅን ጥቂት ወራት ብቻ ተቆጥረዋል። ሳምንት እንኳን አላረፍንም። እስር ቤት ያገባደድነውን መፅሐፋችንን ለአዲሱ ዓመት ለማድረስ እሩጫ ላይ ነን። ኮምፒዩተር ተገዛ (የነበሩን በሙሉ በመንግሥት ተወርሰዋል)፤ ፀሐፊ ተቀጠረና የቤታችንን አንዷን ክፍል ጊዜያዊ ቢሮ አደረግናት። ጧት ሁለት ሰዓት ተኩል ስራ ይጀመራል፤ ስድስት ተኩል ምሳ ይወጣል፣ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ድረስ ስራ ይሰራል፡፡ ብዙ ጊዜ እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ይቆያል። እረፍት የለም።
ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ፀሐፊዋ አቃታት። የኮምፒዩተር ፀሐፊዎች ዘና ብለው ነው መስራት የለመዱት። የእኛን ጥድፊያና ውጥረት አልቻለችውም። ተሰናብታ ሄደች። ሌላ ፍለጋ አልሄድንም። መፅሐፍ መስራት ልምድ ወዳላት አንድ ወዳጃችን ሄድን። በጥቂት ጊዜ አቀላጥፋ አጠናቀቀችው።
ማተሚያ ቤት ስናፈላልግ፣ የግል የመንግሥት አላልንም። እስከ ነሐሴ መጨረሻ የሚያደርሱልንን ብቻ ለመለየት ሞከርን። የመንግሥቶቹ በሙሉ ከአዲስ ዓመት በኋላ ቀጠሩን። የትምህርት መፃሕፍት በማተም ተወጥረዋል። ከግሎቹ ውስጥ አማራጮች ነበሩ። አዲስ ማሽን ያስገባውን መርጠን፣ 6ዐ ሺ ብር ቀብድ ተከፍሎ ስራው ተጀመረ። ቀሪው 6ዐ ሺ ብር ስራው ሲያልቅ እንዲከፈል ተስማማን።
ማተሚያ ቤቱ ለሥራው ትልቅ ቦታ ሰጠው። ያኔ 12ዐ ሺ ብር ትልቅ ገንዘብ ነበር። ቴክስቶቹ ፊልም ተነሱ፤ ተሰባጥረው ተቀመጡ። ከ6ዐዐ ገጾች በላይ ያለው መፅሐፍ በመሆኑ፣ ይህ ስራ 15 ቀናት ፈጀ። ተደከመበት። የመፅሐፉ ሽፋን በጎን እየተጣደፈ ነው። ባለ 4 ቀለም ስለሆነ፣ ከፊል ስራው ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት ተልኳል። ከ1ዐ ቀናት በኋላ ተጠናቆ ሕትመት ተጀመረ። ቶሎ ቶሎ እየተመላለስን መከታተል ነበረብን። አንድ ቀለም፣ ሁለት ቀለም፣ ሶስተኛ ቀለም ድረስ ሄደ። ቴክስቱም ተጀመረ። ወደ 1ዐ ገጾች ታተሙ። እውነትም ለአዲስ ዓመት ሊደርስ ነው።
በመካከሉ ግን፣ ያልተጠበቀ የስልክ ጥሪ አቃጨለ።
«አቤት!» አልኹኝ፤ በእጄ ላይ የያዝኹትን ሻይ ቁጭ አድርጌ።
«እስክንድር፣ እፈልግሀለኹ» አለኝ የማተሚያ ቤቱ ባለቤት።
ከሠርክዓለም ጋር ተያይዘን ወደ ማተሚያ ቤቱ ከነፍን። ባለቤቱ ከምርት ክፍል ሥራ አስኪያጁ ጋር ሆኖ ተቀበለን።
«ምነው?» ብላ ጠየቀችው ሠርክዓለም።
«ሕትመት እንድናቋርጥ ታዘናል፣» አለ ባለቤቱ፤ አንገቱን ደፋ አድርጎ።
«በማን?» ብላ ጠየቀችው። ከ1983 በኋላ፣ መፅሐፍ እንዳይታተም ስንሰማ ይሄ የመጀመሪያ መሆኑ ነው። ተገረምን!
«ደህንነቶች እዚህ ድረስ መጥተው ወደ ውጭ ይዘውኝ ከሄዱ በኋላ፣ ሕትመቱን ካላቆምኽ በሕይወትህ ላይ መፍረድ ነው፣» ብለውኛል አለ ወጣቱ ባለቤት፤ ፊቱን ቁምጭጭ አድርጎ።
«የሚያስጠይቅ ነገር ካለው እኛ አለን። በስማችን ነው እኮ የሚወጣው። አታሚ የሚጠየቀው ፀሐፊው ካልታወቀ ብቻ መሆኑን በአዋጁ በግልፅ ተቀምጧል። አንተን የሚመለከትኽ ነገር የለም፣» አልኹት።
«ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያለኽን ግንኙነት አቋርጥ ተብያለኹ፡፡ ተረዱኝ። ቤተሰቤን አስደንግጠዋል፣» ብሎ መለሰልን።
ማፈግፈግ አስፈለገ። ቤተሰቡን ግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል፡፡ 6ዐ ሺውን ብር እንዳለ መለሰልን። የሕትመቱን ወጪ እሱ ይክሰር፣ ደህንነት ይካሰው አላውቅም። ፊልሞቹን በሙሉ አስረከበኝ፡፡ አሁን ድረስ አሉ።
ስንወጣ፣ በር ላይ የደህንነት መኪና ቆማ ጠበቀችን። ሶስት ደህንነቶች እውስጧ ተቀምጠዋል። በቁጣ አፈጠጡብን። አንዱ መገናኛ አንስቶ መነጋገር ጀመረ። ማስፈራሪያ መሆኑ ነው፡፡ ፊታችንን አዙረን መንገዳችንን ቀጠልን።
ከሶስት ዓመታት በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደማተሚያ ቤት ላመራ ነው፡፡ አሁን ግን የማሳትመው በኢንተርኔት ላይ የወጡት ፅሁፎቼን ነው። አዲስ ነገር አይደለም። በኢትዮጵያ ውስጥ የተነበቡም ያልተነበቡም አሉበት። በመፅሐፍ መልክ እንዳይታተሙ ክልከላ እንደማይኖር ተስፋ አደርጋለኹ።
እስከዚያው ድረስ ግን፣ ከታፈነው መፅሐፍ ውስጥ ለሕዝብ ልናካፍል የምንፈልገው አንድ ምዕራፍ አለ።
በምርጫ 97 ሳቢያ፣ በሰኔና በጥቅምት ወራት የተጨፈጨፉትን ንፁሀን ዜጎች ጉዳይ እንዲያጣራ በፓርላማ ተሰይሞ የነበረው ኮሚሽን ቃሊቲ ወህኒ ቤት መጥቶ አነጋግሮን (በምርጫው ሳቢያ የታሰርነውን) ነበር። ይህንን ታሪካዊ ስብሰባ በተሟላ ገፅታው ለታሪክ መዝግበን አስቀምጠነዋል።
ዘንድሮ፣ የሰኔ 1 ተጨፍጫፊዎች በአግባቡ አልተዘከሩም የሚል ስሜት አለን። በጋዜጣም ሆነ በሌሎች ሚዲያ ብዙም አልታወሱም፣ አልታሰቡም። በእኛ በኩል፣ ከታፈነፈው መፅሐፋችን ውስጥ ቀንጭበን ይፋ የምናደርገው የዚያ ታሪካዊ ስብሰባ ዘገባ ለዘንድሮ ማስታወሻቸው በረከት ይሁንልን።
አጣሪ ኮሚሽኑ በቃሊቲ ወህኒ ቤት
ከታፈነው መፅሐፍ የተቀነጨበ
«ወደውጭ ትሄዳላችኹና ተዘጋጁ» ተባልን፡፡ ለባብሰን ጠበቅናቸው። 8 ሰዓት ላይ መጥተው መኪና ላይ ጫኑን። ከግቢ ስንወጣ፣ መኪናዋ ወደግራ ተጠምዝዛ ወደ ፍ/ቤት አቅጣጫ በረረች። ጥበቃው ከባድ ነው። ከኋላችን ፌዴራል ፖሊስ ይከተለናል። መንገድ ላይም በርካታ ፌዴራል ፖሊሶች ቆመዋል። አንዳንዶቹ ክላሽንኮቭ ታጥቀዋል። ውጥረት ነግሷል።
የጫኑን መኪናዎች ፍ/ቤት ቅጥር ግቢ እንደደረሱ፣ ወርደን ወደ አዳራሹ እንድንገባ ታዘዝን። መጀመሪያ የወረደው የእኛ ቡድን ነበር። ግቢውን አቋርጠን ወደ አዳራሹ ገባን፡፡ አዳራሹ ውስጥ ማንም አልነበረም። ከኋላችን የተከተሉን የእነ ዶ/ር ብርሃኑ ቡድን ነበር። ፈጠን ፈጠን ብለው ደረሱብን።
«ካሜራ ሊይዙ ይችላሉ። እንዳይቀርፁን እንጠንቀቅ» አለ አንድ ድምፅ ከኋላችን። ባለንበት ቆመን ዞር አልን። የዶ/ር ብርሃኑ ቡድን ደርሶብናል።«ሳንነጋገር ምን ብለን ነው የምንገባው? ማን ነው የሚፈልገን?» በማለት ዶ/ር ብርሃኑ ጮኽ ብለው ጠየቁ። ወደ ውስጥ ገባ ያልነው፣ ወደውጭ ወጥተን፣ መተላለፊያው ላይ ዶ/ር ብርሃኑን ከበብናቸው።«ምንም የነገሩን ነገር የለም እኮ። ዝም ብለው ነው እኮ ነድተው ያመጡን» አሉ ዶ/ር ብርሃኑ።
ከኋላችን ሴቶች እስረኞች ደረሱብን። ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ንግሥት ገብረህይወት፣ ሰብለ ታደሰ ብቻ ነበር የመጡት። ሠርክዓለም የለችም። ደነገጥኹ። ምን ሆና ነው? ታመመች እንዴ? (በኋላ ላይ አመጧት)
«መግባት የለብንም። ለምንድን ነው የምንገባው? ማን ነው የሚፈልገን?» ብለው ብርቱካንም ተቃውሟቸውን ገለፁ፡፡ ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር ለመነጋገር ዕድሉ እንዳልነበራቸው አውቃለኹ። ሳይነጋገሩ የያዙት የጋራ አቋም ነበር። መተላለፊያው ተጠበበ።
ፖሊሶቹ ግራ ተጋቡ። ኃላፊያቸውን ጠሩ። አበበ ዘሚካኤል የሚባሉ የወህኒ ቤቱ አንድ ኃላፊ መጡ።
«ምንድን ነው?» አሉ አበበ ፊታቸውን ኮስተር አድርገው።
«ለምንድን ነው የመጣነው?» ብለው ጠየቁ ብርቱካን ከፍ ባለ ድምፅ።
«አጣሪ ኮሚሽኑ ነው የፈለጋችኹ» አሉ አበበ ንዴታቸውን ለመቆጣጠር እየታገሉ።
«አስገድዳችኹ ልታቀርቡን ትችላላችሁ እንዴ? እኛን አስገድዶ ለማቅረብ የሚችለው እኮ ፍ/ቤት ብቻ ነው» ብለው ብርቱካን መለሱላቸው። ብርቱካን ፊት ላይ ቁጣ ይነበባል።
«ወደ ውስጥ ገብታችኹ ተቀመጡና ጥያቄያችኹን ልታቀርቡ ትችላላችኹ» አሉ አበበ እጃቸውን ወደ አዳራሹ እያወዛወዙ።
«ካሜራ የያዙ ሰዎች ያለፍላጐታችን ቢቀርፁንስ?» ሲሉ ጠየቁ ዶ/ር ብርሃኑ። ዶ/ር ብርሃኑ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት ጣልቃ መግባታቸው እንደነበር ተሰማኝ።
«ያለፍላጐታችሁ አትነሱም። ወደውስጥ ግቡና ቁጭ በሉ። ልታነጋግሯቸው ካልፈለጋችኹ፣ መመለስ ትችላላችኹ። የሚያስገድዳችኹ የለም» አሉ አበበ። ይሄኔ፣ የወህኒ ቤቱ አዛዥ አቶ አብርሃም ወልደአረጋዊ መጡ። ወደፊት ሊያልፉ ሞከሩ። ሊሳካላቸው ግን አልቻለም።
«ጥሩ፣ እንገባለን። ያለፍላጐታችን ካሜራ አንቀረፅም። ማነጋገር ካልፈለግንም መውጣት እንችላለን ማለት ነው?»
«አዎ» አሉ አበበ።
«ካሜራ እንደሌለ መጀመሪያ ይታይ» አለ አንድ ድምፅ ከወደኋላ በኩል። ታየ። ካሜራ የያዘ ሰው አዳራሽ ውስጥ አልነበረም።
«እሺ እንግባ፣ የሚሉትን ሰምተን እንወጣለን» አሉ ዶ/ር ብርሃኑ፡፡ እነ ዶ/ር ብርሃኑ፣ ብርቱካንና ፕ/ር መሥፍን ፊት ፊት እየመሩ፣ ቀሪዎቻችን ተከትለናቸው ገባን (ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ሆስፒታል ስለነበሩ፣ አብረውን አልነበሩም)። ሰዓቴን ተመለከትኹ 8፡19 ይላል። ቁጭ ብለን ብዙም ሳንቆይ፣ ፊት ለፊታችን ካለው መጋረጃ ጀርባ፣ 7 ሰዎች መጥተው በተዘጋጀላቸው ወንበር ላይ ቁጭ አሉ። ከመካከላቸው አንዱ የቄስ ልብስ የለበሱ ናቸው፡፡ ሌላኛው ሰው፣ የካቶሊክ ቄስ መሆናቸውን የሚያሳይ የደንብ ልብስ አድርገዋል። አንዷ ሴት ናቸው።
በሰዎቹ ላይ የዚያ ሁሉ ተከሳሾች ትኩረት ያረፈባቸው መሆኑ የተወሰነ ጭንቀት እንዳሳደረባቸው ያስታውቅ ነበር።ሰብሳቢያቸው ከእኛ በስተግራ በኩል ባለችው የመጀመሪያ ወንበር ላይ ቁጭ አሉ፡፡ በዕድሜ ከሌሎቹ ያንሳሉ። ሱፍ በሱፍ አድርገዋል። ቀጭን ክራቫትም አስረዋል። «ዕድሜያቸው ስንት ይሆን?» ብዬ ራሴን ጠየቅኹኝ። ከ30ዎቹ የሚያልፉ አይመስልም። ሰብሳቢው መናገር ጀመሩ።
ይቀጥላል
ፀሐፊውን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.