እስክንድር ነጋ - (አዲስ አበባ)

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሰሞኑን ተወጥረው ሰነባብተዋል፡፡ የመንግሥታቸው ወጪ ከገቢው መንጥቆ ማምለጡ አዲስ ዜና አይደለም፡፡ ትንሹ ቡሽ እንደ ... 2ዐዐዐ . ከክሊንተን ስልጣን ሲረከቡ፣ የአሜሪካ መንግሥት በካዝናው ትርፍ ገንዘብ ነበረው፡፡ ገቢው ከወጪው ይበልጥ ነበር፡፡ 21ዐ፣ ዓመታዊ የባጀት ጉድለቱ 1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሄዷል፡፡ በየዓመቱ የተጠራቀመው ጉድለትና ብድር ተደማምሮ ዘንድሮ 14 ትሪሊዮን ዶላር በላይ አሻቅቧል፡፡ ይሄ ነው ብሔራዊ ዕዳ ማለት፡፡ ሸክሙ አሜሪካን እያንገዳገዳት ነው፡፡

 

አብዛኛው ዕዳ የተቆለለው ቢንላደን በለኮሰው የሽብርና የፀረ ሽብር ጦርነት ነው፡፡ አስደናቂነቱም እዚህ ላይ ነው፡፡ በታሪክ፣ ከስረው የተፈረካከሱ ታላላቅ መንግሥታት በብዛት ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ እንኳን ሶቭየት ሕብረት አለች፡፡ የገነባችውን የጦር ኃይል መሸከም አቅቷት ለውድቀት ተዳርጋለች፡፡

የአሜሪካ የተለየ ነው፡፡ እርግጥ፣ ገና አልወደቀችም፤ አልከሰረችም፡፡ ጫፍ ላይ ግን ደርሳለች፡፡ በአንድ ሰው መዘዝ፡፡ ድንቅ ነው፡፡ በታሪክ የመጀመሪያው ነው፡፡

 ታዲያ፣ ኦባማ ለወረሱት ዕዳ እንጂ ለሶሪያ ግዜ ባይኖራቸው እንዴት ይፈረድባቸዋል? ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካን እንዲህ ደብቷት አያውቅም፡፡

 የሶሪያ ሕዝባዊ አብዮት ከተቀጣጠለ ይኸው አምስት ወራት አልፈውታል፡፡ የጀመረ ሰሞን፣ ከምር የወሰደው አልነበረም፡፡ የትንሹ አሳድ መንግሥት ከማይገፉት የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች እንደአንዱ ነበር የሚቆጠረው፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ አልነበረበትም፡፡ ሕዝቡ የተከፋፈለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በብሔር ነው፣ በሶሪያ ደግሞ በኃይማኖት ነው፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ ሱኒ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያሉት አሊዋ የሚባሉ የሙስሊም ክፍያ ናቸው፡፡ አይጥና ድመት ናቸው፡፡ ለእነአሳድ የተመቸ ነው፡፡ Air-tight ይሉታል ፈረንጆች፡፡ መፈናፈኛ  የለም ለማለት ነው፡፡ የተከፋፈለ ህዝብ ለአብዮት አይሆንም፣ ብለው ተነተኑ የፖለቲካ ምሁሮቹ፡፡ ግብፅ ሌላ፣ ሶሪያ ሌላ፡፡

በሂደት ግን፣ ትንታኔውና ሂደቱ የቀንና የሌሊት ያህል ተለያዩ፡፡ አይፈነዳም የተባለው ሕዝባዊ ቁጣ ፈነዳ፡፡ አይተባበርም የተባለው ሕዝብ ተባበረ፡፡ አይዘልቅም የተባለው ሰላማዊ ሰልፍ ዘለቀ፡፡ አይከፋፈልም የተባለው የሶሪያ ጦር ተከፋፈለ፡፡ አይደራደሩም የተባሉት አሳድ አንገት ደፉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኞቹም ድራሻቸው ጠፋ፡፡ ግራ ተጋብተዋል፡፡ ለውጥ አይመጣባትም የተባለችው ሶሪያ ለውጥ አይቀሬ ሆኖባት፡፡ ሚዛኑ ከእነ አሳድ ወደ ሕዝቡ እያጋለ ነው፡፡

ይሄኔ ነው እንግዲህ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሩጫ የሚጀምረው፡፡ በግብፅ አይተነዋል፡፡ ቀደም ሲልም፣ በቱኒዚያና በሊቢያ፡፡ የኃይል ሚዛን ታይቶ ነው ሕዝብ የሚታገዘው፡፡ ዲሞክራሲ ሁለተኛ አጀንዳ ነው፡፡ በዲፕሎማሲው ዓለም ይህ ስም አለው፡፡ Realpoltick  ይሉታል፡፡ መንግሥት ሲያይል ከመንግሥት ጋር፣ ሕዝብ ሲያይል ከሕዝብ ጋር መቆም ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ እውነት ከኃይል ጋር ነው ያለው ማለት ነው፡፡ Might is night ይሉታል እነሱ፡፡ ቀላል ነው፡፡ ዋጋ አያስከፍልም፡፡ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ አካሄድ ነው፡፡

ለወትሮው፣ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ተሳትፎ ሲያስፈልግ፣ አሜሪካ ፊት ፊት ትቀድማለች፡፡ የዓለማችን ብቸኛዋ ኃያል መንግሥት ናት፡፡ አይገርምም፡፡ እንድትመራ ይጠበቅባታል፡፡ በተለይ አውሮፓውያን እርስ በእርስ ስለማይስማሙ (ስለሚፎካከሩ) አብረው ለመሥራት የአሜሪካንን አመራር ይፈልጋሉ፡፡ ገላጋያቸው ናት፡፡ እሷ ከሌለች ጊዜያቸውን እርስ በእርስ በመናከስ ያጠፋሉ፡፡ እኔ ልምራ፣ እኔ ልምራ በሚል፡፡ እዚሁ እኛው ሀገር በኢሕአዴግ ውስጥ እንደተኮተኮተው ባሕል ማለት ነው፡፡ / ነጋሶ ጊዳዳ ሰሞኑን በወጣው መጽሐፋቸው ቁልጭ አድርገው አስቀምጠውታል፡፡

እንዲህ ነው፡፡

የሕወኃት አመራር መከፋፈል አባዱላ ገመዳን አስጨንቆ ነበር፤ 1993፡፡ «የብአዴን ተሰሚነት እየጨመረ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ፣ የአማራና የኦሮሞ ጦርነት ይቀሰቅሳል፤» በማለት ኦህዴድን ቀስቅሰዋል፤ ገና ሠራዊቱን ሳይለቁ፡፡ ሕገወጥ ቅስቀሳ ነበር፡፡ ሠራዊቱ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገባ ሕገ-መንግሥቱ ይከለክላል፡፡ ኦህዴድና ብአዴን ተስማምተው የሚኖሩት አንዱ የመሪነቱን አክሊል እስካልጨበጠ ድረስ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ የአባዱላ መፍትሔ፣ መለስን በመደገፍ ብአዴንን መቋቋም የሚል ነበር፡፡ መለስ በዚህች ቀዳዳ ሾለኩ፡፡ ተጠቀሙ፡፡ አሜሪካ፣ በአውሮፓዊያን መካከል ባለው ተመሳሳይ ክፍተት ገዝፋ ኖራለች፡፡ ተጠቅማለች፡፡

አሜሪካ ዲሞክራሲን ለማስፋፋት ብዙ የለፋችና መስዋዕትነት የከፈለች ሀገር ናት፡፡ በተለይ በአንደኛውና በሁለኛው የዓለም ጦርነቶች ዲሞክራሲን ያዳነች ሀገር ናት፡፡ ውለታዋ የሚረሳ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚም ቢሆን፣ ገና አልወደቀችም፡፡ ዓመታዊ ምርቷ ወደ 15 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ እሷን የምትከተለው ቻይና ገና 4 ትሪሊዮን ዶላር አልደረሰችም፡፡ አሜሪካ ጡንቻው አላት፡፡ ችግሩ፣ አንፃራዊ ኃይሏ እየኮሰሰ መሄዱ ላይ ነው፡፡ ለግዜው ግን፣  የሚፎካከራት ሀገር የለም፡፡

ለዚህ ነው፣ ባለፈው ሰሞን በሊቢያ ጉዳይ የውኃ ሽታ መሆኗ ብዙዎችን ያስገረመው፡፡ የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ፊታውራሪ ፈረንሳይ ነበረች፡፡

«እንዴ፣ አሜሪካ ምን ነካትተብለው ተጠይቀው ነበር ኦባማ፡፡

እሳቸው ምንም አላሉም፡፡ እንዲያውም ያፈሩም መስለው ነበር፡፡

«ከኋላ ሆነን መምራትን እንመርጣለን፣» ብለው ረዳቶቻቸው መልሰውላቸዋል፡፡ ዓለም ሳቀባቸው፡፡ ከኋላ ሆኖ መምራት? ምን ማለት ነው? የአሜሪካ ወግ አጥባቂዎች በእጅጉ በገኑ፡፡ «አሁንም ኃያል ነን፡፡ ኦባማ ናቸው መምራት የተሳናቸው፤» ባይ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ልክ ሊያስገቧቸው ዝተዋል፡፡

ኦባማ ግን፤ የሰሟቸው አይመስሉም፡፡ ሊቢያን በሶሪያ ደግመውታል፡፡ አሁንም «ከኋላ ሆኖ መምራትን» ነው የመረጡት፡፡

ከባለፈው ዓርብ አንስቶ፣ ለአሳድ ታማኝ የሆኑ ወታደሮች ሐማ በምትባል የሶሪያ ከተማ ውስጥ ብዙ ሰው ጨርሰዋል፡፡ ሕዝብን በታንክ ደብድበዋል፡፡ ይህ አውሬአዊ ድርጊት የሕዝቡን ቁጣ ጨምሮታል፡፡ ወደቤቱ አልገባም፡፡ ጭራሽኑ ቤታቸው የነበሩት መንገድ ላይ ያሉትን ተቀላቅለዋቸዋል፡፡ ሕዝቡ አሳድን ሳያወርድ ወደቤቱ እንደማይመለስ ግልፅ ሆኗል፡፡ ለውጥ የግድ መምጣት አለበት፡፡ ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብም ዝም ብሎ መመልከት እየተሳነው ነው፡፡

በዚህ ሳምንት፣ የአሳድን መንግሥት በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ለማስወገዝ አውሮፓዊያን መሪ ተዋናያን ሆነዋል፡፡ አሜሪካ፣ ተመልካች ናት፡፡ ኋላው ፊት፣ ፊቱ ኋላ ቆሟል፡፡

ነገሮች ቢለዋወጡ፣ በኢትዮጵያስ ይደገም ይሆን? አውሮፓዊያን አሜሪካንን ተክተው ዓለምአቀፉን ማሕበረሰብ ይመሩ ይሆን?

ሐሳብ የሚጭሩ ምልክቶች አሉ፡፡ በምርጫ 2ዐዐ2 የአሜሪካ ድምፅ ብዙም አልተሰማም፡፡ ታች ላይ ሲል የነበረው የእንግሊዝ ኢምባሲ ነበር፡፡ ችግሩ፣ ቅድመ ሊቢያ፣ ሚጢጢዋን እንግሊዝ እንደ ኃያላን መንግሥት የሚቆጥራት መጥፋቱ ነበር እንጂ፡፡ ያኔ የኦባማ አስተዳደርም ሆነ በኢትዮጵያ የሾማቸው አምባሳደሩ አዲስ ነበሩ፡፡ በምርጫው ሰዓት ለመጥፋታቸው እንደምክንያትም ቀርቧል፡፡

አምባሳደሩ ለመላመድ ብዙ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ከዓመት በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መገናኛ ብዙሃን ፊት ሲቀርቡ፣ «እኔ የማተኩረው በልማትና ኤድስ ላይ ነው፣» አሉ፡፡ የዓለምአቀፉን መሪነት ሚና ሀገራቸው ላለመፈለጓ ወይም ላለመቻሏ እንደምልክት ሆኖ ግን አልተወሰደም፡፡ በተቃዋሚዎች ላይ ተስፋ ስለቆረጡ ነው ተባለላቸው፡፡ በሊቢያ ዙሪያ የነበረው ትንሽ ጥርጣሬ ጫረ፡፡ የሶሪያው እያጠናከረው ነው፡፡

በዓረብ ሀገሮች የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ቁጣ፣ ፈረንጆች፣ « ዓረብ ስፕሪንግ» ብለውታል፡፡ ስፕሪንግ ማለት በጋቸው ነው፡፡ እንደ እኛ 1 ወራት አይዘልቅም፡፡ በእነሱ 4 ወራት ገደማ ይቆያል፡፡ ስፕሪንግ፣ ሞቃታምም ብርዳማም አይደለም፡፡ መካከለኛ ነው፡፡ በጣም ይወዱታል፡፡ የውጭውን አየር በነፃነት የሚተነፍሱት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ የዓረብ ስፕሪንግ ሲሉ፣ ጥሩ ጊዜ መጣ ማለታቸው ነው፡፡ የነፃነት አየር የሚተነፈስበት፡፡ እፎይ የሚባልበት፡፡

ይህ አየር በዓረቡ ዓለም ተወስኖ የሚቀር አይደለም፡፡ ወደአፍሪቃም ይመጣል፡፡ ከወዲሁ «የአፍሪቃ ስፕሪንግ» እያሉት ነው፡፡ መምጣቱ አያነጋግርም፡፡ መቼ? የሚለው ነው እንጂ ያልለየው፡፡ በብዙ መልኩ፣ ግብፅ በዓረቡ ዓለም ያላትን ቦታ ኢትዮጵያ በጥቁር አፍሪቃ አላት፡፡ የዓረብ ስፕሪንግ የተባለው ግብፅ ሲገባ ነበር፡፡ በተመሳሳይ፣ የአፍሪቃ ስፕሪንግ እውን የሚሆነው ኢትዮጵያ ከገባ ነው፡፡

ግብፅ፣ በዓረቡ አለም ትልቁ የአምባገነኖች ምሽግ ነበረች፡፡ ምሽግ ተንዷል፡፡ በጥቁር አፍሪቃ፣ ትልቁ ምሽግ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በግብፅ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር አሜሪካ አግዛለች፤ አርፍዳም ቢሆን፡፡ አቅሙ (ወይም ፍላጎቱ) የከዳት በሊቢያና በሶሪያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ሽግግር ድጋፍ ያስፈልጋታል፡፡

ታዲያ እስከዚያ አሜሪካ ታገግም ይሆን? ወይስ አውሮፓውያን ይተኳት ይሆን?

]]]

ፀሐፊውን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ