ታየኝ እኮ፡ ሀረርና ወለጋ ገጥሞ፡ የ“ኦሮሚያ”ን ሪፐብሊክ ሲመሰርት ችግሩ ግን፡ ግንቦት ሰባትና እኛ ጋር ነው
ልጅ ተክሌ (ኦታዋ)
ብሄርንና ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ክርክር አስቸጋሪ ነው። ሀይማኖት ይብሳል። በንጽጽር፡ ከሀይማኖት ደግሞ ብሄር ለክርክር ይቀላል። ለጥቂት ጽንፈኛ ኦሮሞዎች የምንወረውረው ትችት ወይንም ስላቅ፡ አያሌ ለስላሳ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞዎችን ሊያስቀይም ይሆንብናል። በመርህ ደረጃ፡ ከማናቸውም ብሄር-ቀመስ ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ውይይት ባያስደነግጠኝም፡ መጀመሪያ ይሄ የግንባር/ህብረት ምስረታ ጉዳይ፡ ለጥቆ ደግሞ ከኦነግና ኦብነግ ጋር የሚደረገውን ውይይት ያመጣው ግንቦት ሰባት ነውና፡ ማምጣትም ብቻ አይደለም፡ የተወሰኑ የኦነግ አባላት የሚናገሩትን ሰባራ አረፍተ ነገሮች ይዞ፡ በግነት “ኦነግ የመገንጠል ሀሳቡን ጥሏል” ብሎ ለነገር ያሰፈሰፉትን በባዶ ሜዳ አስጮኋልና፡ መጀመሪያ ግንቦት ሰባትን ትንሽ ለኮፍ አደርገዋለሁ። ከዚያ ወደ ኦነግ እወርዳለሁ።
የዚህ የሰሞኑ የአንድነትና የነጻነት/የመገንጠል ሄይሎች ክርክር ዋናው ችግር፡ ግንቦት ሰባትም ከቅርብ ግዜ ወዲህ፡ የጥንቱ ፖለቲካ ድርጅቶቻችን በሽታ ተጋብቶበት፡ ጥምረት ምስረታውን ቀጥሎበት፡ ግንባር ምስረታ ደግሞ ጀምሯል። እንደኔ እንደኔ የሰለጠነ አስተያየት፡ ይሄ ጥምረት ምስረታ፡ ግንባር ምስረታ፡ ህብረት ምስረታ፡ መድረክ ምስረታ፡ መንደር ምስረታ፡ ፓርቲዎች ስራ መስራት ሲያቅታቸው የሚያመጡት መዝሙር ነው። ከዚህ በፊትም ጽፌበታለሁ። http://ethiopiazare.com/articles/opinion/34-opinion/1430-lij-tekle የግንባር ምስረታውንም ይሁን ከተገንጣይ ሀይሎች የሚደረገውን ውይይት አልጠላውም። ነገር ግን፡ ግንባር ምስረታውም ይሁን የአንድነት መንገድ ጠረጋው እንዲህ ተጋኖ መራገብ አልነበረበትም ባይ ነኝ። ስለተጋነነ ነው፡ ቀድሞውንም ሌሎች ለአመታት ስራ መስራት ያልቻሉ ባለአንድ አባል ፓርቲዎች ብድግ ብለው የኢትዮጵያን አንድነት ተከላካይ መስለው እንዲያብዴ ያደረጋቸው። አንድነት አፍራሹ እመሀል አራት ኪሎ ቁጭ ብሎ፡ አሁን እዚህ እነግንቦት ሰባትን መዋጋት ምን ይባላል? ችግሩ ግን የግንቦት ሰባት ነው። አድፍጦ ስራውን እንደመስራት፡ በያደባባዩ፡ ለእንካሰላንቲያ መነሾ ከሚሆኑ ሀይሎች ጋር ስብሰባና መሀላ ሲያበዛ ነው ችግር የመጣው።
እንጂ፡ ኦነግ አሳስቦኝ አያውቅም። ለኦነግ መድሀኒቱ ስልጣን መስጠት ነው። ምክንያቱም ኦነግ ስልጣን ቢይዝ እንደ መንግስት መስራት ይጀምራል። ገላሳ ዲልቦ፡ ዳውድ ኢብሳ፡ ኢብሳ ጉተማ፡ ሌንጮ ለታ፡ ስልጣን በያዙ ማግስት የሚያተኩሩት፡ እንደኢትዮጵያዊ መሪ ተንቀሳቅሰው የአለምአቀፉን መንግስታት እውቅና ማግኘት ላይ ነው እንጂ፡ ይሄንን ልገንጥል ያንን ልቀጥል የሚል ጦርነት ውስጥ አይገቡም። ምክንያቱም በመገንጠል ከገፉ፡ ግጭት ይቀሰቀሳል። ግጭት ከተቀሰቀሰ ደግሞ፡ ደም ይፈሳል። ደም ከፈሰሰ፡ ስልጣናቸው ይናጋል። ስለዚህ ኦነግ ስልጣን ባይዝ እንጂ፡ ስልጣን ቢይዝ የሚያመጣው ችግር አይታየኝም። ኦነግ፡ ኢትዮጵያን ቢመራ ነው የሚያምርበት፤ ልክ ሕወሀት ኢትዮጵያን ሲመራ እንደሚያምርበት ማለት ነው። ለኛ ማለቴ አይደለም። ለራሳቸውና ለዓለም። እስኪ አስቡት፡ ሕወሀት ትግራይን ይዞ ቢቀጥል የሚኖረውን መልክ። የትግራይ ሪፓብሊክ። በተባበሩት መንግስታት መቀመጫ ተሰጥቷት፡ አቶ መለስ ዜናዊ የትግራይ ጠቅላይ ሚኒስትር ….. ኡኡኡ አይደብርም? ማለቴ አያንሳቸውም? ልክ አቶ አያሌው ጎበዜ የአማራ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ቢሆን እንደሚያስጠላበት ማለቴ ነው። እንኩዋን ለመለስ፡ ለኛም ይደብራል። አሉላ አባነጋ ወይንም ንጉሰ ነገስት ዮሀንስ፡ በተከታታይ የትግራይ ራስና የትግራይ አጼ ሲሆኑ? አይመችም። አጼ ዮሀንስ በሞቱበት ያማትባሉ !! በስመአብ ...
ለኦሞሪያም እንደዚያው። አጼ ዳውድ ኢብሳ፡ ኦሮሚያ የተባለች አገር መሪ ሆኖ፡ አገር ሲፈጥር፡ መንግስት ሲገነባ ከሚኖር፡ በመንግስትነት የረጅም ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን ቢመራ ይቀለዋል። ጎጃምና ጎንደርን፡ ወሎና አፋርን፡ ሀረርና ሲዳሞን ያልያዘ ኦሮሚያ የተባለ አገር ተመችቶት ሲያድር ታየኝ። የማይመስል ነገር፡ ለኦሮሞ አትንገር። ያው ሁሉም የኔ ቢጤ ስራ-ፈት ሆኖ እንጂ፡ የግንቦት ሰባትና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ስብሰባ ማንንም ሊያሰጋ አይገባም ነበር። ቀድሞ ነገር፡ የኔ ግንቦት ሰባት፡ ትግሉን ፈቀቅ ማድረግ ስላቃተው ነው እንዲህ ያለው የስብሰባ ትግል ውስጥ የገባው ብሎ መከራከር ይቻላል። ስለዚህ፡ አያልሰው ደሴም በራሱ ፈቀቅ ማለት ስላልቻል፡ ይሄንን ሲያገኝ፡ ዘራፍ ብሎ ተነሳ። የነኢህአፓና ኢዜፓ ጩኸት የረጅም ግዜ ነውና፡ ይሄ ክስተት ልክ እንደ ነዳጅ ብቻ ነው ያገለገላቸው።
ኦነግ አስግቶኝ አያውቅም። የኦነግ ባንዲራን አይታችሁታል? ከኢትዮጵያ አልራቀም እኮ። ዋርካም ያድርጉበት፡ ሾላ ዛፍ፡ በክብም ይሁን ባራት ማእዘን፡ ያው አረንጓዴ፤ ቢጫ ቀይ ነው። ስለዚህ፡ ኦሮሚያ የምትባል አገር ቢመሰርቱ እንኩዋን፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገርን ከውስጣቸው ሊያወጧት አይችሉም። ያን ለማድረግ፡ ኢትዮጵያን ማጥፋት አለባቸው። ኢትዮጵያን ማጥፋት ደግሞ እነሱም ሰላሳ ምናምን አመት የለፉበትን ትግል ገደል መክተት ነው። እስኪ አስቡት ኢትዮጵያ ከጠፋች፡ ኦሮሚያ ምን ተረፋት? ምንም። ዳውድ ብልጥ ነው። ከመለስም ከኢሳያስም አያንስም። እንደ ኢሳያስም አይሆንም። ሙሉ በሙሉ እንደመለስም አይሆንም። ዳውድ ሸዋን አያርቅም። ሸዋ ከሌለ፡ ሀረርና ወለጋ ሰላም አያድሩም። እንዲሁም አርሲ። እንዲሁም ባሌ። እድሜ ለሸዋ ይበሉ እኚህ ሁሉ። ሸዋም እድሜ ለነሱ ይበል።
ጎበዝ፡ መንግስት መሆንና ድርጅት መሆን አንድ አይደለም። እመኑኝ፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጥግ ይዞ በመታዘብ፡ አንዳንድ ግዜም መሀል ገብቶ በመዘገብ አጭር ነው የሚባል ልምድ አለኝ። ኦነግ ስልጣን ቢይዝ እንደመንግስት ነው የሚንቀሳቀሰው። ኢትዮጵያ የምትባልን ጥንታዊት አገር አፈራርሶ፡ እንደገና ሀምሳ መንግስታት ቢመሰርት፡ መከራ ነው ትርፉ። ለኦነግ ኢትዮጵያን እንዳለች ይዞ ከመጓዝ ውጪ ምርጫ የለውም። ያ ቀን እስኪመጣና ጥርስ እስኪያወጡ ግን፡” ኦሮሞ ተገፍቶ፡” ‘ኦሮሞ ተደፍቶ” እያሉ ከመኳተን ውጪ ምርጫ የላቸውም። ለዚህ ምክንያቱ ግልጽና አጭር ነው። ኦሮሞው ጃዋር መልሶታል። ኦነግ፡ ያለው ስንቅና ትጥቅ የቅኝ ግዛት ርእዮተአለሙ ብቻ ነው። በአቢሲኒያ ቅኝ የተገዛችውን ኦሮሚያን ነጸ እናወጣለን ነው የሚለው። ኦነግ ይሄንን ሀሳብ ከግብ ለማድረስ ምንም ያህል ተግባራዊ ርምጃ አልተራመደም። ሀሳቡ ብቻ አንዳንዴ አየር ላይ፡ አንዳንዴ ምድር ላይ ይሳባል እንጂ። ኦነግ እንደ ድርጅት ምድር ላይ የሰራው ስራ እምብዛም ነው። መንፈሱ ግን፡ ይሄ “ኦሮሞ ቅኝ ተገዝቶ፣ ጡቱ ተቆርጦ” የሚለው፡ በቀላሉ ተስፋፍቷል። ስለዚህ ኦነግ ያለው አማራጭ፡ ደጋፊዎቹ የሚሉትን ይዞ መሄድ ነው። ደጋፊዎቹን መምራት ሳይሆን፡ ደጋፊዎቹን መከተል። “ኦሮሚያ ኦሮሚያ። ቶኩማ ቶኩማ፡ ከኢልመ ኦሮሞ ቶኩማ” እያለ። ኦነግ “ፖፑሊስት” ነው ይለዋል ጃዋር። ኦነግ፡ ልክ “ጡት ቆራጩ ምኒሊክ” ቤተመንግስት እንደደረሰ፡ ያንን መፈክር ይጥልና፡ “ቶኩማ ቶኩማ ከኢልመ ኢትዮጵያ ቶኩማ” ከማለት ውጪ ሌላ ምንም ምርጫ የለውም። ኦሮሞ አንድ ሆኖ አያውቅማ። ኦሮሚያ ራሱ ሌላ ዘጠኝ ፌደራል ክልሎች አይወጡትም? አሁን ግን ያንን ሊል አይችልም። ምክንያቱም ምንም የለውማ።
ከኦነግም ይሁን ከኢህአዴግ ብሄርን መሰረት አድርጎ የሚደረግ ንግግር አያሳስበኝም። እነ ዲባቶ ብርሀኑ ነጋም ይሁኑ እነ አንዳርጋቸው ጽጌም የኢትዮጵያን ጥቅም ጠንቀቀው የሚያውቁ ሰዎች ስለሆኑ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ ይደራደራሉ ወይንም ይዋዋላሉ ብሎ መገመት ያስቸግራል። ስህተት ሊፈጸም ይችላል። ስለዚህም በጨዋ ቋንቋ ማስጠንቀቁ አይከፋም። ግን “ምን ሲደረግ ከኦነግ ጋር ዋላችሁ” ብሎ እዬዬ ለማንም አይበጅም። ኦነግ አሳስቦን አያውቅም። ልድገመውና የኦነግ ሀሳብና መንፈሱ እንጂ። የኦነግ መንፈሱ ይረብሻል። ኦነግ ሊያደርግ የሚችለው ትልቁ ነገር፡ ይረብሻል። ያውካል። በተለይ ዴሞክራሲ ካለ፡ ሰልፍ በሰለፍ ነው የሚያደርገን። ከዚያ ኦነግ በመንግስትነት አመትም መንፈቅም የሚያቆይ ብልሀትም ፖለቲካዊ ስንቅም፡ ታሪካዊ መሰረትም የለውም። ኢትዮጵያን ጠቅሎ ካልያዘ በስተቀር። እነ ህወሀት፡ አናሳዎች ናቸው። ስለዚህ ለህልውናቸው ሲሉ ወጥረው ይሰራሉ። ስልጣን ወይም ሞት ነው። ኦሮሞ አናሳ አይደለም። ኦሮሞ ግንድ ነው፡ መራራ ጉዲና እንዳለው። ግንድ ደግሞ፡ እላዩ ላይ ትንንሽ ግንዶች አሉት። እነዚያን ግንዶች ይዞ የት ሊገባ?
ጓደኛዬ ዳንኤል ኦነግ ስልጣን ቢይዝ፡ ሁለት አመትም አይዘልቅም ነው የሚለው። እንኩዋንስ ሰፊው ኦሮሞ፡ ጅማና ወለጋ እንኩዋን ተስማምቶ አያድርም። አንዱ አክራሪ ጴንጤ ነው። አንዱ እስልምና ይበዛበታል መሰለኝ። ኦሮሞ ሀይማኖቱ ምንድነው? እስልምና ወይስ ክርስትና? ወይስ ዋቄ ፈቻ? ወደ ሀረር ከዘለቅንማ ጉዳዩ ሌላ ይሆናል። መራራ ይሁን ሌላ ምሁር መሰለኝ፡ ከገዳ ስርአት ጋር በተያያዘ፡ የሀይማኖት ጉዳይ የፈጠረውን አንድ ትልቅ ውጥረት ጽፎ አንብቤያለሁ። ያ ብቻ አይደለም፡ እነ ዳኒ ራሳቸው ድሮ፡ በርጫ ነክሰው እንደቀልድ ሜጫና ቱለማን ራሱ በቀላሉ ያጣሉ ነበር። አሁን “ቱለማ እያለ እንዴት ሜጫ ስብሰባ ይመራል?” ብለው። የቱለማው ሰው ይደሰታል። በርጫቸውን ሲጨርሱ፡ እነ ዳኒን ጨብሲ በጨብሲ አድርጎ ይሸኛቸዋል። ኦነግ አንድ ሆኖ የኦሮሚያ ሪፐብሊክን ሊያስተዳደር አይቻለውም። የኢትዮጵያን ሪፐብሊክ እንጂ። ሕወሀትን አታዩም፡ የመጣበት ሌላ፡ የቆመበት ሌላ። ኢትዮጵያን ማፍረስ ቀላል አይደለም። መሸርሸር እንጂ። ሕወሀት ያልቻለው፡ ኦነግ አይቻለውም።
ኦነግ ስልጣን ከያዘ ኢትዮጵያን እንዳለች፡ ከኢህአዴግ እንደተረከበው፡ ከማስተዳደር ውጪ ምንም ምርጫ የለውም። ኢትዮጵያ ፈርሳ ኦሮሞ የምትባል አገር ተመስርቶ ሲያድር እስኪ አስቡት። ከሀረር ወለጋ፡ ከባሌ ሸዋ፡ ያለው የኦሮሚያ ውጥንቅጥ ብቻ ሳይሆን፡ አካባቢው ሁሉ ሊታወክ ነው። ሊታመስ ነው። አለም ደግሞ በቂ ቀውስ አላት። በተሌኢ የአፍሪካ ቀንዱ። ተጨማሪ ቀውስ አትፈልግም። በቡሀ ላይ ቆረቆር። እነ ዳውድም ቢሆን፡ ያው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መሪ፡ ስልጣናቸውን ትንሽም ቢሆን አጣጥመው እንዲሄዱ፡ ኢትዮጵያን እንዳለች ከማስተዳደር ውጪ፡ የአርሲንና የጅማን፡ የሀረርንና የወለጋን፡ የኢሉባቡረንና የሸዋን ውጥንቅጥ ሲያማስሉ መኖር አይሹም። ስለዚህ የአክራሪ ኦሮሞ ነጻነት ታጋዮች እሪታ፡ ይሄንኑ ኢህአዴግ ያመጣውን እንኩዋን እንዳያጡ ነው። ዋጋውን ሰቅለው ተከራክረው፡ የሚፈልጉት ቦታ ላይ ለመቆም ነው፤ ፌደሬሽን። ነጻነት ነጻነት ይሉና፡ ፌደሬሽን ነው ነገሩ። ራሳችንን እናስተዳድር። ኦሮሞን ገንጥሉ ብለን ብንሰጣቸው ራሱ እሺ የሚሉን አይመስለንም።
ስለዚህ፡ ባጠቃላይ በግንባር ምስረታ አስፈላጊነት ባላምንም፡ ግንቦት ሰባት ከኦነግ ጋር የሚያደርገው ውይይት ግን፡ ማንንም ሊያስደነግጥ የሚገባ አይደለም ባይ ነኝ። ያው ስራ ሲጠፋ፡ ትግል ሲጠፋ፡ መላ ሲጠፋ፡ ነገር ሲከፋ ካልሆነ በስተቀር፡ የዚህ የግንባር፡ የህብረት፡ የጥምረት ምስረታ ፋይዳውም አይታየኝም። ግንቦት ሰባት ራሱ ይሄንን አሳምሮ ያውቀዋል። ያለፈው ጥምረት ምስረታ ሂደት ሁለት አመት ፈጀ። ይሄኛው ሌላ ሁለት ሶስት አመት። እነሆ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ግንባር እስኪመሰረቱ አስራ ምናምን አመት ይፈጃል። እስከዚያ፡ ረሀብና፡ እድለኛው ሕወሀት አገር ይፈጃል። ይሄ ፖለቲካ እንደፈረደብኝ ካልገባሁበት በስተቀር እየተበለሻሸ ነው። እስከዚያው ግን፡ አረጋዊ በርሄ ከተማዬ መጥቷልና http://www.ecadforum.com/Amharic/amharic-news/613/ እስኪ እሱ ደግሞ የሚለውን ልስማ። ቅዳሜ። እንጂ፡ ነገሩማ፡ ጥምረትም፡ ህብረትም አያስፈልገውም። “All It took to change Egypt is the paralysis of Cairo” ብሏል እስክንድር ነጋ። ጎበዝ፡ በኦሮምኛም ይሁን በአማርኛ፡ አዲስ አበባን ብቻ እናሽመድምድ።
አርብ፡ ነሀሴ፡ 2011



