‹‹ህዝቡ ሠላማዊ ለውጥ ይፈልጋል፤ ጊዜው የለውጥ ነው››
እስክንድር ነጋ
እስክንድር - በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ ከ20 ዓመት በፊት ኢህአደግ ሥልጣን ሲይዝ በአፍሪካ ዴሞክራሲያዊት አገር ቦትስዋና ብቻ ነበረች፡፡ ከ20 ዓመት በኋላ ከግማሽ በላይ ደሞክራሲያዊ አገሮች ሆነዋል፡፡ ይህ እንግዲህ አረቦችን ሳንጨምር ማለት ነው፡፡ እስካለፈው ግማሽ ዓመት ድረስ በሰሜን አፍሪካ የዴሞክራሲ በሮች ዝግ ነበሩ፡፡ ዛሬ ቱኒዚያና ግብጽ ዴሞክራት አገሮች ሆነዋል፡፡ ግብጽና ቱኒዚያ ላይ የሆነውን አይቶ የሞሮኮ መንግሥት በፈቃደኝነት ተሃድሶ ጀምሯል፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ካልተጓዝን ግብጽና ቱኒዚያ የሆነው በሞሮኮም ይደገማል በሚል የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጀምረዋል፡፡ አልጀሪያም የተወሰነ ሪፎርም አድርጋለች፡፡ ሊቢያኖች በመንገድ ላይ ናቸው፡፡ ጦርነት ላይ ናቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚያሰፍኑ አያጠራጥርም፡፡ የቀረው የአፍሪካ ቀንድ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድን ስንመለከት አንድም ዴሞክራሲያዊ አገር የለም ።
ቅድም እንዳልኩህ በአፍሪካ ከግማሽ በላይ ዴሞክራሲያዊ ሃገሮች ተፈጥረዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቆጨዋል፡፡ ራሱን የሚያወዳድረው ከአውሮፓውያን ጋር አይደለም፡፡ ካደጉትና ከበለፀጉት ጋር አይደለም፡፡ ይህችን አገር እያወዳደረ ያለው ከኬንያ ጋር ነው፡፡ ይህችን አገር እያወዳደረ ያለው ከማላዊ ጋር ነው፡፡ ይህችን አገር እያወዳደረ ያለው ከቤኒን ጋር ነው፡፡ ከታንዛኒያ ጋር ነው፡፡ እነዚህ አገሮች በምንም መለኪያ ከኢትዮጵያ የተሻሉ አይደሉም፡፡ በሥልጣኔ የሚበልጡን አይደሉም፡፡ እንደውም ኢትዮጵያ እነዚህን አገሮች ለነጻነት ያበቃች አገር ናት፡፡ ከእኛ በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ ከኋላ ተነስተው መቅደማቸው ለብዙዎቹ ኢትዮጵያውን የእግር እሳት ሆኖባቸዋል፡፡ በማሊና በማላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ከተቻለ በኢትዮጵያ ውስጥ መገንባት የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ ኢህአዴግ እንደሚለን የሽግግር ዘመን አያስፈልገንም፡፡ ኢህአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ውስጥ ሆኖ እንደሚከራከረው ከአንድ አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የሽግግር ወቅት ያስፈልገናል የሚለው ፍጹም የተሳሳተና ከእውነት ውጪ የሚነዛ ወሬ ነው፡፡ የሽግግር ዘመን ባለማስፈለጉ ባለፉት 20 ዓመት በርካታ አገሮች በቀጥታ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ችለዋል፡፡ በሌላው አፍሪካ አገሮች የተደረገውን አይቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ይህችንም አገር ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ይፈልጋል፡፡
ይህንን ለማድረግ ምን ያስፈልጋል ይላሉ?
እስክንድር - ይህንን ለማምጣት ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ያ እውን ሆኖ ለማየት አልታደልንም፡፡ ለዚህ ተጠያቂው የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ናቸው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሕዝቡ ራሱ የተጠያቂነት ድርሻ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን እየመረጠ እየተቀላቀለ ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ ከፖለቲካ ድርጅቶች ሊርቅ የቻለው በውስጣቸው ባለው ሽኩቻ እንደኘ አምናለሁ፡፡ ይህ እልባት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በዚህ በኩል የፖለቲካ ድርጅቶች ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ይህ ሊፈታ ከተቻለ አገሪቱ ወደ ተፈለገው አቅጣጫ መጓዝ ትችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ረፍዶባታል፡፡ ጐረቤት አገር ኬንያ ዴሞክራት መሆን ከቻለች ኢትዮጵያም መሆን ትችላለች።
ወደ ኋላ ልመልስዎት እና ፈረንጆች 200 ዓመት ተጉዘው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተዋል፡፡ እኛ ጅምር ላይ ነን ይባላል፡፡ በርካታ የቴክኒዎሎጂ ውጤቶችን ኮፒ ማድረግ ከቻልን ዲሞክራሲን ኮፒ ለማድረግ አይቻልም? የሽግግር ወቅት ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው?
እስክንድር- ሽግግር የግድ ቢሆን ኖሮ ከግማሽ በላይ የአፍሪካ አገሮች የዓለም አቀፍ መስፈርት አሟልተው ዲሞክራሲያዊ አገሮች ባልተባሉ ነበር፡፡ ጋና ዲሞክራት አገር ሆናለች፡፡ ጋና ከነፃነት በኃላ የገጠማትን ችግር ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ንኩሩህማ አምባገነንዊ ሥርዓት ለመመስረት ሞክሮ ነበር፡፡ወታደራዊ መንግስት ተካው፡፡ ወታደራዊ መንግስት ተፈራረቀባት፡፡ በመጨረሻ ግን የሽግግር ጊዜ ሳያስፈለጋት በቀጥታ ዴሞክራሲያዊ ሃገር ነው የሆነችው፡፡ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር በአፍሪካ አህጉር ከቦስትዋና በስተቀር አንድም ዲሞክራሲያዊ አገር አልነበረም፡፡ በአስር ዓመት ውስጥ ግን ከአፍሪካ አገሮች ከግማሽ በላይ ዲሞክራሲዊ ሆኑ፡፡ የሽግግር ወቅት አላስፈለጋቸውም፡፡ የሽግግር ወቅት የግድ ቢሆን ኖሮ ዲሞክራሲያዊ ባልሆኑ ነበር፡፡ ሶሻሊዝም እስከተሸነፈበት ወቅት ድረስ በጣም ጥቂት አገራት ብቻ ነበሩ ዲሞክራሲያዊ የነበሩት፡፡ ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ በኋላ ግን የነበረው አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡ ዴሞክራሲ አንደሰደድ እሳት ተስፋፋ፡፡ ብራዚል፣ አርጀንቲና ቺሊ ዴሞክራሲያዊ አገሮች ሆኑ፡፡ በዓለም ላይ የፋሽስት አገር ምሳሌ የነበረችው አገር እኮ ቺሊ ነበረች፡፡ የሽግግር ወቅት ሳያስፈልጋት ስኬታማ ዲሞክራሲያዊ አገር ሆናለች፡፡ ዛሬ በጥሩ ምሳሌነቷ የምትጠቀስ ናት፡፡ ዲሞክራሲያዊ ለመሆን ባህል የላቸውም የተባሉት ፖላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ስሎቫኪያ፣ ሩማኒያ፣ ዩክሬን ዲሞክራሲያዊ ሆነዋል፡፡ እነዚህ አገሮች አውሮፓ ውስጥ ቢሆኑም “ባህላቸው አይፈቅድላቸውም፤ ኢኮኖሚያቸው ገና ነው” ይባሉ ነበር፡፡ የባህል አብዮት ያስፈልጋቸዋል፤ ኢኮኖሚያቸውም ማደግ አለበት ተብሎ ሲተነተን ነበር፡፡ ዛሬ ግን ዲሞክራሲያዊነታቸውን የሚጠራጠር የለም፡፡ ከዓለም አገሮች ውስጥ ደሃ ከሚባሉት አንዷ ማላዊ ናት፡፡ ማላዊ ከኢትዮጵያ የባሰች ድሃ ናት፡፡ ማላዊ ዛሬ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም የዲሞክራሲ ምሳሌ ልትሆን ችላለች፡፡ እነዚህ አገሮች ለዚህ ሲበቁ የሽግግር ወቅት አላስፈለጋቸውም፡፡ ብዙ ዓመት አልፈጀባቸው፣ አስር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዲሞክራሲን ገንብተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ግን 20 ዓመት በሥልጣን ላይ ቆይቶ ጠንካራ የአፈና ተቋማትን እየገነባ ስለ ጅምር ያወራልናል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ እነዚህ አገሮች የተቀየሩት ከገጠሟት መሪዎች ወደ ሥልጣን በመጡ ፓርቲዎች ጥንካሬ ወይስ በህዝብ ንቁ ተሳትፎ?
እስክንድር - የሰው ልጅ በሰው ልጅነቱ የሚሆነውና የሚስማማው ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያኖችም ከዚህ ውጪ ልንሆን አንችልም፡፡ ለማሊ የሽግግር ዘመን እንዳላስፈለጋት ለኢትዮጵያም አላስፈልጋትም፡፡ የጐደለው የኢሕአዴግ አመራር ቅንነት ነው፡፡ የእነሱ ቅንነት ቢኖር ኖሮ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ትሆን ነበር፡፡ እነሱ ናቸው ደንቃራ የሆኑት፡፡ ይህ ግልጽ መሆን አለበት።
የሰሜን አፍሪካ አገሮች በአንድ ላይ ሆ ብሎ ሥርዓት ሲቀይር የተመለከቱ አንዳንድ ግለሰቦች የሚሰጡት አስተያየት አለ፡፡ “በዚህ በ20 ዓመት ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ በቋንቋ በጐሳ በክልል በጥቅማጥቅም ከፋፍሎታል፡፡ የዘረጋው የስለላ መዋቅር ህዝብ አንድ ቋንቋ እንዳይናገር አድርጐል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንግዲህ ምን ጊዜም በአንድ ላይ ተነስቶ የሥርዓት ለውጥ ሊያመጣ አይችልም የለውጥ ኃይል አይሆንም የሚሉ አሉና እርስዎ ምን ይላሉ?
እስክንድር - ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ በርካታ ምሁሮች በኢንተርኔት አንስተውት የነበረ ነው፡፡ በግብጽና በቱኒዚያ ውስጥ ስኬታማ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመሄድ እድሉ የጠበበ ነው፤ ቢሄድም ችግር ያስከትላል የሚሉ መላምቶች ተስተጋብተዋል፡፡ በሶርያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ግን ምላሽ የሰጠ ይመስለኛል፡፡ የሶሪያን የፖለቲካ ህይወት የተመለከትክ እንደሆነ ልክ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው ዓይነት ክፍፍል የሚታይበት ነበር፡፡ ግብጽና ቱኒዚያ አብዮት ሲፈነዳ ወደ ሶሪያ አይሄድም፤ የሶሪያ ህዝብ የተከፋፈለ ነው ተባለ፡፡ እውነት ነው፡፡ በገዢው አሊያቶች በብዙኃኑ ሱኒና በሺያቶች መካከል የጐላ መከፋፈል ይታይ ነበር፡፡ ሦስቱ ማህበረሰቦች ተባብረው የዲሞክራሲ ጥያቄ ሊያነሱ አይችሉም ተብሎ በምሁራን ሲተነተን ነበር፡፡
የአረቡ ዓለም ጥያቄ ሶሪያን አልፎት ይሄዳል ተብሏል፡፡ ከግብጽ በኋላ ወደ ሳውዲ ሊሄድ ይችላል ተብሏል፡፡ ብዙኃኑ ሱኒ ነው፡፡ እነሱ የባህልና የብሔር ክፍፍል የለባቸውም፤ ህዝቡ ተባብሮ የዲሞክራሲ ጥያቄ ያነሳባቸዋል ተብሎ በምሁሮች፣ በፖለቲከኞች በጋዜጠኞች ይተነተን ነበር፡፡ እንደተመለከትነው ግን ሳውድ አረቢያ ውስጥ ከመነሳቱ በፊት በሶሪያ ውስጥ ተነሳ፡፡ ያ ተከፋፍሏል፣ በጠላትነት ይተያያል የተባለው እና ተስፋ የተቆረጠበት ህዝብ አንድ ህዝብ ሆኖ የሶሪያን መንግሥት እያስጨነቀው ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብቱን በሠላማዊ መንገድ እየጠየቀ ነው፡፡ የጥይት ናዳ እየወረደበት፣ በታንክ እየተደበደበ፣ ልዩነቱን ወደ ጐን ትቶ መብቱን እየጠየቀ ነው፡፡ ዛሬ አሊያቶችና ሱኒዎች ጐን ለጐን ቆመዋል፡፡ ኦሳድን ግራ የገባው ይኼ ነው፡፡ በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ውስጥ ተቃውሞ ከመነሳቱ በፊት በቅድሚያ ብጥብጡ የተነሳው በአሊያቶች ከተማ ውስጥ ነው፡፡ አሳድን ይህ የእኔ ከተማ ነው በሚለው ከተማ ውስጥ የሶሪያ የዲሞክራሲ ጥያቄ ተቀጣጠለ፡፡ ተንታኞች ምሁራን ፖለቲከኞች ግራ ነው የተጋቡት፡፡ ህዝብ ሲነቃ2 ህዝብ አይኑ ሲከፍት ስለአንድነቱ እንጂ ስለልዩነቱ ማሰቡን ያቆማል፡፡ አንድነቱን ትቶ ስለልዩነቱ የሚያስብ ህዝብ ተስፋ የቆረጠ ህዝብ ነው፡፡ የጨለመበት ህዝብ ነው፡፡ ተስፋ ያለው ህዝብ አይከፋፈልም፤ ይተባበራል፡፡ በሶሪያ ውስጥ የታየው ይኸው ነው፡፡ ሙባረክ በህዝብ ውስጥ ያለውን ልዩነት ተጠቅሞ ለመከፋፈል ሞክሯል፡፡ ከግብጽ ህዝብ 10% ክርስቲያን ነው፡፡ 90% ሙስሊሚ ነው፡፡ ይህንን ማህበረሰብ በማጋጨት የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሞክሮ ነበር፡፡ አልተሳካለትም፡፡ ይህ አልሳካለት ሲል ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለመከፋፈል ሞክሮ ነበር፡፡ እኛ አገር በብሔር እንደራጃለን አንደራጅም እንደሚሉት፣ እስልምናን ከፖለቲካ ጋር በማጣመር ወይም መለያየት የሚፈልጉ አሉ፡፡እስላሚስትና ሴኩላሪስቶች ይባላሉ፡፡ ሰፊ ልቁነቶች አላቸው፡፡ ልዩነታዠውን ሙባረክ ሊጠቀምበት ሞክሯል፡፡ እነሱ ግን መብቶቻችን ይከበሩ እንጂ ልዩነቶቻችን እንፈታለን፤ ተቻችለን እንኖራለን አሉት፡፡ ችግራችን ልዩነቶቻችን አይደሉም የሚል ድምጽ አሰሙ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም የብሔር፣ የሃይማኖትና የአካባቢ ልዩነቶቻችን በሰላማዉ መንገድ የዲሞክራሲ ጥያቄ ከማንሳት አያስቀሩንም፡፡ ወደ ሌሎች አፍሪካ አገሮችም ስንሄድ እንደ እኛው ህብረብሔራዊ አገሮች ናቸው፡፡ ቤኒን፤ ማላዊ፤ ማሊ፤ ኬኒያን ብንመለከት እንደኛው ናቸው፡፡ የተለያየ ሃይማኖት፣ የተለያየ ቋንቋና ጐሳ ያላቸው አገሮች ናቸው።
ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት ያገዳቸው ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም የብሔር፣ የቋንቋ፣ የኃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች የጋራ ጥያቄዎቻችንን በሰላማዊ መንገድ ከማንሳት እንቅፋት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እነዚህን ልዩነቶችን በኢትዮጵያዊነታችን በሰው ልጅነታችን ከመተሳሰር አይለዩንም፡፡ ሌሎች አገሮች ካላቸው የተሻለ አቅም አለን፡፡ አብሮ የመኖር ልምድ አለን፤ የተሻለ የማድረግ አቅሙ አለን ብዬ አምናለሁ።
ፀሐፊውን ለማግኘት፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



