ሉሉ ከበደ

ዘመኑ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1990 ላይ ነበር። ለደርግ የአስተዳደርና የፖለቲካ ድህነት ምስጋን ይግባውና ሐገራችን ከገንጣይና አስገንጣይ ሀይሎች ጋር ታደርግ የነበረው ትንንቅ በኛ ሽንፈት ወደማክተሙ ሲቃረብ፤ ዋናው ምክንያት የወያኔና የሻእቢያ ጦር ከኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጀግናና ሐያል ሆኖ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ጦርሰራዊት በገጠመው የአመራርና የአስተዳደር ቀውስ የውጊያ ሞራሉ ሊጠገን በማይችል መልኩ ስለተጎዳና ውግያውን ስለተወው፤ በሩ ሁሉ ለጠላት ክፍት ሆኖ በመገኘቱ ነበር።

 

ሻዕቢያ አስመራን ሲቆጣጠር፤ ወያኔም ከክፍለ ሐገር ክፍለ ሐገር በግሩም በመኪናም እየሮጠ ሐገሪቱን በሙሉ አዳርሶ ሊቆጣጠር በተቃረበበት ወቅት፤ የጉዳያችን ባለቤቶች ሆነው ብቅ ያሉት አሜሪካኖች፡ ከደርግ በሗላ ያለችውን ኢትዮጵያ እንዴት አድርገው ለራሳቸው እንደሚያበጃጇት፤ ጥሩ ጉዳይ ፈጻሚ አስፈጻሚ ለሚሆናቸው ለማን እንደሚሰጧት መምከር ነበረባቸው።  ክፍል አንድን ስናዘጋጅ ከቆምንበት ጥያቄ እንነሳለን።                                                                        

 

ፖል :- ከኢህአፓ ጋር ያላችሁስ ግንኙነት እንዴት ነው?

 

መለስ፤ ከኢሕአፓ ጋር ግንኙነታችን ጥሩ አይደለም። የአብዮቱ ፍንዳታ ሰሞን ጥሩ ነበሩ ። በቀይ ሽብር  ክፉኛ ጉዳት ደረሰባቸው። ከንግዲበሗላ ያኔ እንደነበሩት አይሆኑም። ሌላው የደርግ አይነት ነው የሆኑት። የአማራውን የበላይነት ነው የሚፈልጉት። አዲስ አበባ ላይ ስልጣኑን ሁሉ ተቆጣጥረው አገሪቱን በተማከለ አሰራር ሊገዙ ይፈልጋሉ። ሁሉም ማርክሲስቶች ናቸው። በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ህዝብ ህብረት የሚለውን መመሪያችንን ይቃረናሉ። አስተሰሳሰባቸውን ካልቀየሩ  እንተባበራቸዋለን ብለን አናስብም። እናም ሕዝቡ ይደግፋቸዋል ብለን አናስብም።

 

ፖል፤ መኢሶንስ ?

 

መለስ፤ መኢሶን በኢትዮጵያ ውስጥ መስክ ላይ ተዋጊዎች የሉትም ። አለን ይላሉ ። ሲያስመስሉ ነው ። በመርህ ደረጃ ከነሱ ጋር እንዳንስማማ የሚያደርገን ነገር የለም ። እንተባበራቸውም ይሆናል ።

 

ፖል፤ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር ያለውስ ዝምድና እንዴት ነው ?

 

መሰስ ፤ አስቸጋሪ ቡድን ናቸው ። ከነሱ ጋርም በቀላሉ ስምምነት ላይ መድረስ እንችላለን ። ግን ጥሩ ድርጅት የላቸውም ። ባሰራራቸው አንተማመንባቸውም ። የተማከለ አመራር የላቸውም ። አንተ ከነሱ ጋር በአንድ ነገር ተስማምቻለሁ ብለህ ታስባለህ ። ከዚያ ሕዝባቸው ስለ ጉዳዩ አንድም ነገር የማያውቅ ሆኖ ታገኘዋለህ ። በኢትዮጵያ ውስጥ ጥንካሬ አላቸው ብለንም አናስብም ። በውጭ ብዙ ያወራሉ ። ግን በውጭ አገር እንኳ የተደራጁ አይደሉም። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኦሮሞ አብዛኛው በቁም ነገር ያያቸዋል ብለን አናስብም ። አንዳንዶቹ ስለ መገንጠል ያወራሉ ። ግን ነጻ ኦሮሚያ እውን ሊሆን አይችልም ። ደርግ ሌላ ሁለት ሶስት ዓመት ከቆየ አገሪቱ መፈራረስ ትጀምራለች ። እናም የተወሰኑ ኦሮሞዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ አንድ ላይ ይመጡ ይሆናል ። ግን ላሁኑ ኢትዮጵያን በአንድነት ማቆየት ፋይዳ እንዳለው ኦሮሞ ተረድቷል ብለን እናስባለን ።

 

ፖል፤ በመገንጠል ላይ አቋማችሁ ምንድ ነው ?

 

መለስ ፤ እኛ ተገንጣዮች አይደለንም ። አንድ የሆነች ኢትዮጵያን እንፈልጋለን ። ነገር ግን የተማከለ የሸዋዎች የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን አንፈልግም ። ከሁለት ሳምንታት በፊት ለኤርትራውያን ያደረከውን ንግግር አንብቤአለሁ ። ያልከውን ነገር በሙሉ እደግፋለሁ ። ካንተ ጋር እስማማለሁ ። በኢትዮጵያ የክልል መንግስት ዋጋ አለው ። ኢትዮጵያ መውደም የለባትም ። ዲሞክራሲን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ባንድነቷ መቆየት አለባት ። ለሁሉም ሕዝብ ነጻነትና የራስ ገዝነት ዋስትና በመስጠት መሰባሰብ አለባት ። እንደዚያም በኢኮኖሚ ታድጋለች ። ይህ የሚሆንበት ብቸኛው መንገድ ፌዴሬሽን ነው ። ፌዴሬሽንን እንደግፋለን ። ደርግ ያደሰረው ጉዳት የሚጠገንበት ብቸኛ መንገድ ይህ ነው ።

 

ፖል ፤ ይህ ነገር ወደ ኤርትራና ወደ የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር ያመጣናል ። ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ትነጋገራለሕ ?

 

መለስ ፤ ከኢሳያስ ጋር ዘወትር እነጋገራለሁ ። አሁን አለመግባባት የለንም ። በ1970 ዎቹ ውስጥ አብረን ሰርተናል ። የከፋ አለመግባባት የለንም ። በ1984 ግንኙነታችን ተቋረጠ ። የተለያየነውም በሶቬት ሕብረት ላይ ባለን የተለያየ አመለካከት ምክንያት ነበር ። እስካሁን እንደሚያምኑት ሶቬት ሕብረት ለወደፊቱ ሞዴልነት ስላለው የጥገና ለውጥ ማካሔድ አለበት ። ሶቬት ሕብረት በኢትዮጵያ ላይ ተሳስቷል ብለው ይከራከራሉ። ከደርግ ይልቅ እነርሱን እንዲረዱ ሶቬቶችን ለማሳመን ይሞክራሉ ። የሶቬት ስርዓት ሞዴልነው ብለው ስለሚያምኑ ያን ኤርትራ ውስጥ ለመተግበር እንደሚችሉ ያስባሉ ። ይህ ሞኝነት ነው ። ምክንያቱም እኛ ትግራይ ውስጥ ተምረናል ። የራሳችን የሆነ ሞዴልን ማጎልበትና እንደራሳችን ሁሄታና ተግባራዊ ልምድ የራሳችንን ስርዓት ተግባር ላይ ማዋል አለብን ። ብዙ ንግግሮችን ተመልክተናል:።ሶቬቶች ጣሊያንና ምስራቅ ጀርመኖችን በመጠቀም ደርግንና የኤርትራን ነጻ አውጪ አንድ ላይ ለማምጣት ሲከሩ ። ምንም ጠብ እንደማይል እንገምት ነበር ። ልክ ነበርን።

 

ለአራት ዓመታት ያህል ከ1984-88 ከኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር ጋር ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት ነበረን ። ከዚያ እንደገና ስምምነት አደረግን ። ሶቬት ህብረትን እኛ ባየንበት መንገድ ማየት ቻሉ ። ህልማቸውን ተዉ ። በጎርባቾቭ ስር በሶቬት ህብረት ምን እንደሆነ አዩ ። በ1988 አፈቤት ላይ ታላቅ ድል ከተቀዳጁ በሗላ ሁለታችንም እንደገና መተባበር ጀመርን ። ይረዱናል ። ግን እኛ እስካሁንም በጣም በራሳችን የቆምን ሀይሎች ነን ። በነርሱ ላይ ጥገኞች አይደለንም ። አሁን መላውን ትግራይ ተቆጣጥረናል ። የእንዳስላሴን ጦርነት በራሳችን ጥንካሬ አሸነፍን ። ባይረዱንም ኖሮ ትንሽ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድ ነበር እንጂ እናሸንፍ ነበር ። ያ ማለት ግን እኛ ሁሉንም ነገር የምንመለከተው እነሱ ከሚያዩበት አኳያ ነው ማለት አይደለም ። ይህን ላረጋግጥልህ እወዳለሁ ።

 

ፖል ፤ ምንድናቸው ልዩነቶቻችሁ ?

 መለስ ፤ የኤርትራ ነጻነት ግንባር ከኛ ይልቅ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉት ። ልዩነቶቻችን ሁሉ ከዚያ ይመነጫሉ ፡፡ ሁኔታቸውም ይገባናል ፡፡ እናዝንላቸዋለንም ። በትግራይ ውስጥ እኛ የተባበረ አንድ የሆነ ሕዝብ ነው ያለን ። ከሕዝባችን እስላሙ አስር ከመቶ አይበልጥም ። እናም ሙስሊሙ መጀመሪያ ትግራዊ ነው ፤ ቀጥሎ ሙስሊም ። በኤርትራ ውስጥ ያ እውነታ የለም ። ሕዝቡ በጣም የተከፋፈለ ነው ። የኤርትራ ሙስሊሞች እራሳቸው የተከፋፈሉ ናቸው ። ቢያንስ ቢያንስ ሶስት ቡድን በውስጣቸው አለ ። ነገሮችን ክርስትያኑ በሚያይበት አይን አይደለም የሚያዩት ። የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር በውስጡ ጥቂት አሉት ። ሙስሊሙን የተባበረው ንቀናቄ አካል ለማድረግ ይሞክራሉ ። ሊሆን ግን አይችልም ። ሻዕቢያ ኤርትራን ለመቆጣጠር በተቃረበ ቁጥር ይሕ ጉዳይ የበለጠ አደገኛ እየሆነ ይመጣል።በኤርትራ ውስጥ ባሉት ክርስቲያኖችና ሱዳን ውስጥ ባሉት ሙስሊሞች መካከል አደገኛ ውጥረት አለ ። ይሕ ደርግ ከኤርትራ ሲወጣ ተለይቶ የሚታወቅ ይሆናል ። በትግራይ ስደተኞች ውስጥ ይህ ችግር የለብንም ። አንድ ላይ የተቆራኙ ናቸው ። ክርስቲያኖች ሙስሊሞቹን አይጠሏቸውም ። እና ሙስሊሞቹም በክርስቲያኖቹ እንደተጨቆኑ አይሰማቸውም ።

 

ፖል ፤ መገንጠልን ከኤርትራውያን ሀሳብ ጋር በማነጻጸር እንዴት ትመለከተዋለህ ?መለስ ፤ የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር ችግር አለበት ። ሕዝቡ ደርግን እጅግ ስለጠላው ሁሉም ተገንጣይ ሆኗል ። ግንባሩ አስመራን እንደያዘ ወዲያውኑ ነጻነት እንዲታወጅ ሕዝቡ ይፈልጋል ። የዚሕን እርምጃ አንዳንድ ችግሮች ኢሳያስ ይረዳል ። ምክንያቱም ባለፈው ዓመት በጉዳዩ ላይ ብዙ አስቧል። ግን ከሕዝቡ ሀይለኛ ግፊት አለበት ። አስቸጋሪ ጉዳይ ነው ለርሱ ።

 

ፖል ፤ የደጋው ክርስቲያኖች እንደሙስሊሙ አፋጣኙን የነጻነት አዋጅ ይደግፉታል ?

 

መለስ ፤ በዚሕ ላይ የተለያየ አመለካከት አለ ። ግን ሕዝቡ ባጠቃላይ ነጻነት እንደሚፈልግ እናስባለን ። ምን ማለት እነደሆነ ላይረዱትም ይችላሉ ፡፡ ይህ ሕዝብ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር ባንድነት መኖርን ይደግፍ የነበረ ነው ። የሸዋ አማሮች ያንን ስሜት አጠፉት ። የደጋው ክርስቲያኖች ከመሪው የበለጠ መታገስ የማይችሉ ሆኑ ። ኢሳያስም ከኢትዮጵያ መገንጠል ጣጣ እንዳለው ስለሚታየው ተቻኩሎ በራሱ ላይ ችግር መፍጠር አይፈልግም ። ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ራሱ ሙሉ ቁጥጥር የለውም ።

 

ፖል ፤ ያንተስ ምርጫ የሚሆነው ምንድ ነው ? ( የኤርትራውን ነጻነት አስመልክቶ ማለቱ ነው )

 

መለስ ፤ ይህንን የምንመለከተው መጀመሪያ ከትግራይ ጥቅም አኳያ ነው ። ቀጥሎ ካጠቃላይ ኢትዮጵያ አንጻር ። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ዝምድናዋን ቀጥላ ማየት እንፈልጋልን ። ትግራይ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት እናውቃለን ። ብቸኛው መንገድም በኤርትራ በኩል ነው ። ኤርትራ ተገነጠለችም አልተገነጠለችም ይህን የባህር መዳረሻ እንፈልገዋለን ። ስለዚህ የቀረበ ትስስር እንዲኖር ግድ ይላል ። በኤርትራ ውስጥ ብዙ የትግራይ ሰዎች አሉ ። ያሳስባቸዋል ። እዚያ እንደውጭ አገር ሰው እንዲስተናገዱ አይፈልጉም ። የደጋው ሰዎች አንድ አይነት ስለሆኑ በኤርትራውያንና በትግራይ ሰዎች መካከል ምን ጊዜም የቀረበ ግንኙነት አለ ። አንድ ታሪክ ነው ያላቸው ። ስለ ኤርትራ እንጨነቃለን ። ምክንያቱም ያ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ እርግጠኞች አይደለንም ። ሕዝቡ እርስ በርሱ መዋጋት ከጀመረ እዚያ ሁሉም ነገር እንዳልነበር ይሆናል ። የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር አስመራን እንደተቆጣጠረ አስቸጋሪ ሁኔታ ይጠብቀዋል ። ምክንያቱም ሕዝቡን በአንድነት አሰባስበው መያዝ አለባቸው ። ጥቂቱ ሙስሊሞች መገንጠልን ይደግፋሉ ። ግን በዚህ ጉዳይ ላይ በውስጣቸው የአንድነት ጥንካሬ የለም ። የኤርትራ ነጻነት ግንባር (ጀብሀ) በኤርትራ ውስጥ ህያው ጥንካሬ የለውም ። ሱዳን ውስጥ ግን አሉ ።

 

ፖል ፤ አስመራ ያለው ሁኔታ ጎንደር ካለው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል የሚል አስተሳሰብ አለኝ ። ደርግ እዚያ ውጊያውን ተቋቁሞ የመቆየቱ ሁኔታ በእጅጉ ተሸርሽሯል ። የሗላ ሗላ ከተማዪቱ በኤርትራ ነጻነት ግንባር እጅ ትወድቃለች ። ምናልባትም ያ ከመሆኑ በፊት የደርግ ሀይል ከነጻ አውጭው ጋር አንዳንድ ስምምነቶችን ድርድሮችን ሊያደርግ የችላል ። ይህ ይሆናል ብለህ ታስባለህ ?

 

መለስ ፤ ታውቃለህ ! ባለፈው ግንቦት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወቅት አስመራ ካለው የደርግ ሰራዊት ጋር ግንኙነት ነበረን ። የተኩስ አቁም ትብብር አደረግን ። የኤርትራው ነጻ አውጭ እንዳደረገው ። የተኩስ አቁም ስምምነት እንደምናደርግና በአህጉሩ ለአዲስ አይነት ግንኙነት መሰረት እንደምንጥል አስበን ነበር ። ከተገናኘናቸው የደርግ ሀይሎች ጋርም ያን ማድረግ እንችል ነበር ። ግን የመንግስቱ ሀይለማሪያም ታማኞች የበላይነቱን አገኙ ። መንግስቱ ጥሩ ነገር እንደሚያደርግላቸው አስበዋል ። ምናልባትም የማእረግና የስራ እድገት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ይሆናል ። እነዚህ ወገኖች እስካሁን አስመራን እንደተቆጣጠሩ እናስባለን ። ለመዳከማቸውም የምናየው ማስረጃ የለም ። ማንም ከኛ ጋር ለመገናኘት የሞከረ የለም ። የኤርትራ ነጻነት ግንባር ወደላይ ከፍ እያለ እየተጓዘ ነው ። ጊንዳአና አምትካላን ከያዙ ከባድ መድፎቻቸውን አምጥተው የአስመራን አየር ማረፊያ መደብደብ ይችላሉ ። ያ ለደርግ ሀይለኛ ምት ነው የሚሆነው ። ለቀው የሚሄዱበትን ጊዜ ያሳጥረዋል ።

 

ፖል ፤ ከዚያ ቀጥሎ ምን ይሆናል ? ገና ካሁኑ የኑሮ ሁኔታ አስመራ ውስጥ አስቸጋሪ ሆኗል ። ኤሌትሪክ የለም ። ውሀ የለም ። ነዳጅ የለም ። በርግጥም አንድ ነገር መሆን አለበት ።

 

መለስ ፤ አናውቅም ። ሁሉም አንድ ላይ ተሰባስቦ ጊዜያዊ መንግስት ማዋቀር አለበት ። ይህን አይነቱን ሁኔታ ማስቀረት ይቻላል ።

 

 ፖል ፤  የኤርትራው ነጻነት ግንባር ባዲስ አበባው ጊዜያዊ መንግስት ውስጥ ይሳተፋል ብለህ ትጠብቃለህ ?

 

መለስ ፤ አናውቅም ። ገንቢሚና እንደሚጀጫወቱ እናስባለን ። በውነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ዝምድናዋን ቀጥላ ማየት እንፈልጋለን ። ይህን ነገር እውን ለማድፈረግ ኢሳያስ ይሰራ እንደሁ አናውቅም ። የኛ አቋም ቀና ነው ። ከኤርትራውያን ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል ። እናም የራስን እድል በራስ የመወስን መብታቸውን እውቅና እንሰጠዋለን  ። ከፈለጉም እስከመገንጠል ። ለሕዝብ ውሳኔ ያላቸውን እቅድ እንደግፋለን ። ምክንያቱም እዚህ ለደረሰ ችግር የተለየ ሌላ መፍትሄ አለ ብለን አናስብም ። በውነት ግን ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ባንድነት ብትቆይ እንመኛለን ። ለኤርትራውያን ይጠቅማል ብለህ በጻፍከው ነገር እስማማለሁ ። 

 

ፖል ፤ ትግራይ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንዴት እንደያስከው ለማወቅ የሚያጓጓ ነገር አለ ። ለምሳሌ ኢኮኖሚው እንዴት ነው የሚንቀሳቀሰው ?

 

መለስ ፤ ገበያ በነጻ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው ። ገበሬዎች ነጻ ናቸው ለመሸጥ ። የጤፍ ዋጋ በኩንታል 120 ብር ነው ። የትዮጵያን ብር ነው የምንጠቀመው ። ምንዛሬውም አንድ ያሜሪካን ዶላር አምስት የኢትዮጵያ ብር ነው ።

 

 ፖል ፤ የባንክ አገልግሎት አላችሁ ? የተከፈተ ባንክ አለ ?

 

መለስ ፤ ደርግ ሲሸሽ በባንክ ያለውን ገንዘብ ሁሉ ይዘውት ሄዱ ። የተከፈተ ባንክ የለንም ። ለስራ እንቅስቃሴ የሚበቃ ገንዘብ ግን አለ ።

 

ፖል ፤ ታክስ ትሰበስባላችሁ ?

 

መለስ ፤ ታክስ የለንም ። በበጎ ፍቃድ መዋጮ ላይ ነው የምንተማመነው ።

 

ፖል ፤ የንግድ ስራ እንዲከናወን ተፈቅዳላችሁ ?

 

መለስ ፤ አዎ ። ሌላ ሳይሆን ትንንሽ ንግዶች ትግራይ ውስጥ አሉ ። የመንግስት አላደረግናቸውም ። ዳቦ ቤቶች ፤ መደብሮች ፤ የእደጥበብ ቤቶች ፤ እንደወትሮው ስራቸውን እየሰሩ ነው ። የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ስራቸውን እየሰሩ ነው ። አሁን አርባ ያህል ናቸው ። የእርዳታ እህል ማመላለሱ ጥሩ ስራ ሆኗቸዋል ። ነዳጅ የማግኘት ከባድ ችግር ግን አለባቸው ። ከሱዳን ነው መምጣት ያለበት ። ከኤርትራ ምንም አናገኝም ። ምክንያቱም የኤርትራው ነጻ አውጭ ለራሱም የለውም ።

 

ፖል ፤ የሚሸጥ ነገር ታመርታላችሁ ? ከትግራይ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው እጣን ነበር እየተሰበሰበ ነው ?

 

መለስ ፤ የእጣን ንግድ ሞቷል ። ወደ ውጭ ስለማይሸጥ ሰዎች አይለቅሙም ። ዛፎቹ ግን እንዳሉ ነው ። መልሰው ሊለሙ ይችላሉ ። በቅርቡ የትግራይ ልማት ማህበር የሚባል ቡድን አቋቁመናል ። በትግራይ ውስጥ የልማት ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ ከውጭ እንደምናሰባስብ ተስፋ እናደርጋለን ። 

 

ፖል ፤ የኤርትራው ነጻ አውጭ በቅርቡ የተወረሱ ንብረቶች ለባለቤቱ ለመመለስ አውጇል ። ይህን እንዴት ተመለከተዋለህ ?

 

መለስ ፤ በኤርትራ ውስጥ ይህ እንዴት እንደሚሰራ አናውቅም ። ጥሩ ውጤት እንደሚኖረው እናስባለን ። በትግራይ ውስጥ ግን ይህ ችግር የለብንም ። መሬትን ለስፋፊ መሬት ባለቤቶች አንመልስም ። የንግድ እርሻም ሆነ ሌላ የኢንዱስትሪ ንግድ ተቋማት የሉንም ።

 

ፖል ፤ የንግድ እርሻ ልማትን ትደግፋለህ ? ከኢትዮጵያ ወይም ከሌላ ቦታ ካፒታል ትግራይ ውስጥ ለማልማት የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ ?

 

መለስ ፤ ስለዚህ ጥያቄ እስካሁን አልወሰንም ። ምክንያቱም ጥያቄውም አልተነሳም ።

 

ፖል ፤ ውጤታማ አስተዳደር በትግራይ ውስጥ አዋቅሬአለሁ ብለሀል ። እንዴት ነው የሚሰራው ። ሕዝባዊ አገልግሎት ትሰጣላችሁ ? ትምህርት ቤቶች እየሰሩ ነው ?

 

መለስ ፤ ሁሉ ነገር የሚሰራው በጉባዔ ነው ። ያካባቢ ኮሚቴዎች ባካባቢ ደረጃ ያሉ ጉዳዮችን ውሳኔ ይሰጣሉ ። ማንኛውም  ሰው ይሳተፋል ። ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር ሙሉ እኩልነት አላቸው ። የሰፈር ኮሚቴዎች ባስተዳደራችን ውስጥ በጣም አስፈላጊ አካላት ናቸው ። ምክንያቱም ጉዳዮች በየደረጃው ውሳኔ ያገኛሉ ። እኛ በምንም ጣልቃ ለመግባት አንሞክርም ። በሕውሀት ውስጥ እራሱ ነገሮች ውሳኔ የሚሰጣቸው አመታዊ ጉባዔ ላይ ነው ። አሁን ትምህርት ቤቶችን መክፈት እየጀመርን ነው ። ብዙ ክሊኒኮችን ከፍተናል ። ጥቂት የስልጠና መርሀግብሮችም አሉን ። እርዳታ ያስፈልገናል ። የውጭ እርዳታ በደስታ እንቀበላለን ።

 

ፖል ፤ ከቤተክርስቲያን ጋር ያለህ ግንኙነት እንዴት ነው ?

 

መለስ ፤ እንደምታውቀው በትግራይ ውስጥ ቤተክርስትያን በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ። መቸም ቤተክርስቲያንን ተቃውመን አናውቅም ። ድጋፏንም እንሻለን ። የአዲስ አበባውን ፓትሪያርክ የመቀበል ያለመቀበል ክርክር ነበር ። አቡነ ቴዎፍሎስ ከተወገዱ በሗላ አብዛኛዎቹ ካህናት ደርግ የሾመውን ፓትሪያርክ መቀበል አይፈልጉም ። ምክንያቱም የስልጣን ሀይል እንደሌላቸው ይገነዘባሉ ። ለአዳዲስ ካህናት ሲመት ስልጣን እንዲኖራቸው ወደ አሌክሳንደሪያ ለመሄድ ፈልገው ነበር ። ይህ ግን ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ተብሎ ተወሰነ ። ምክንያቱም ቤተክርስቲያኒቱ እንደገና ራሷን በግብጾች ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ተጽእኖ ስር መጣል አልፈለገችም ። ያጥያቄ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በሗላ ተመልሶ ነበር ። ስለዚህ ጳጳሳቱ በትግራይ ውስጥ የአዳዲስ ካህናትን ሲመት ማጽደቅ የሚያስችል ህገመመሪያ አወጡ ። ካህናት መሳሪያ አንግበው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ግንባር ውስጥ ማገልገል አለባቸው የለባቸውም የሚል ክርክር ነበር ። ጳጳሳቱ ሗላ ላይ ሲወስኑ ፤ ደርግ ሴጣንን የሚወክል እስከሆነ ድረስ ሴጣንን በሚቻለው ነገር ሁሉ መዋጋት አግባብነት ያለው በመሆኑ ፤ ዲያቆናትና ካህናት ከወያኔ ጋር ተሰልፈው ሴጣንን መውጋት ትክክል ሆኖ ስለተገኘ የተወሰኑ ካህናት አድርገውታል ።

 

ፖል ፤ ከኢቫንጀሊካል ቤተሰብ እንደወጣህ ተነግሮኛል ፤ እውነት ነው ?                       

ይቀጥላል

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ