አትክልት አሰፋ (ከቫንኩቨር ካናዳ)

አዜብ ያለ መለስ

አሁን…! አሁን…! ባለፈው ሰሞን ነው። ወ/ሮ አዜብ መስፍን መኪና እያሽከረከሩ የትራፊክ ፖሊስ ያስቆማቸዋል። ስህተት ሰርተሻል በማለት ያስቆማቸው ትራፊክ ጥፋቷን ይገልጽላታል። ወ/ሮዋ ጥፋታቸውን አልሸመጠጡም። አዎ አጥፍቻለሁ አንዱን ግን ስታስቆመኝ ተደናግጨ ነው ስህተት የሰራሁት ይላሉ። የትራፊክ ፖለሱም የቅጣት ትኬቱን ጽፎ በጃቸው አስረክቦ የመንጃ ፈቃዳቸውን ይወስዳል። ይሄ በኢትዮጵያ የትራፊክ አሰራር የተለመደ ነው። እናም መንጃ ፈቃድ የሚወሰደው የትራፊክ መምሪያ ተኪዶ፤ ቅጣት ተከፍሎ ነው።

 

 

ወ/ሮ አዜብም መንጃፈቃዳቸውን ለትራፊክ ፖሊስ አስረክበው የማንነታቸውን ሳይገልጹ ወደ ቤታቸው ያመራሉ። እጅግ ይበል ሊያሰኝ ይችላል። የትራፊክ ፖሊሱ የመንጃ ፈቃዱ ባለቤት የማን መሆኗን በሰማ ሰአት ወደላይ ይበለው ወደታች፤ ስኳር ይነሳበት፣ ደም ብዛት አላህ ይወቅ።

 

ችግሩ… አዜብ አይደለችማ!?። ወ/ሮ አዜብማ ያለ መለስ ምንም ናት። አዜብ ያለመለስ ከአስናቀች፣ ከትብለጽ፣ ከጸዳለ በምንም አትለይም። እትየ አዜብ የሚለዩት የህወሀት መሪ፣ የኢህአዴግ ተጠሪ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር የሚባል ባል ስላላቸው ብቻ አይደለም። ከቅርብ ጓደኞቹ እስከ ሩቅ ወዳጆቹ፤ ከ10 አመት ህጻን ልጅ እስከ ሰማኒያ ኣመት አዛውንት በእጁ ያስጨረሰ፣ እጁ በማይነጥፍ የሰው ደም የጨቀዬ አረመኔ ባል ስላላት ጭምር እንጂ።

 

አዜብ ስፔን ሄዳ ሚሊየን ዶላር ብታጠፋ ምን አለበት!?... በአሁኑ ጊዜ እንኳን እሷ ሌላ ተራ የተባሉ የሀብታም ሚስቶችስ ያን ያህል ገንዘብ ያጠፉ የለም እንዴ? ችግሩ ያለው ህዝብ በርሀብ እንዲሰቃይ እና በስራ እጦት እንዲማስን ዋና ተጠያቂ የሆነ ባል ስላላት እንጂ? ጣጣ የሚመጣው እኮ ወ/ሮ አዜብ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል መሆን አለባት ስላለ የምትሆንለት።  ያሻውን የሚያደርግ ባሏ መለስ ላይ እንጂ… መለስ ባይኖር እነ አቶ በረከት ተነስተው አዜብየ ግቢ ለሚቀጥለው ስልጣን ስለምንፈልግሽ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል መሆን አለብሽ የሚሏት ይመስላችኋል?። ለዚያም ነው ያ ትራፊክ ማንነቷን ሳይሆን የማንነቷን ሲያውቅ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመማጸን ወደላይኛው እንድናጋጥጥለት የምለምነው። ስንት ልጆች ይኖሩት ይሆን…?

 

በነገሬ ላይ ወያኔ ባዶ ሶስት የሚሉት የወሬ ጎስም ቡድን ነበረው። መለስ ምላሱን መላእኮች ሌሊት ሌሊት ክንፋቸውን ዘርግተው ይባርኩለታል ብላችሁ ወሬ ንዙ ከተባሉ ወይም ደግሞ ኢህአዴግ በኤሌክትሪክ የሚሰራ መሳሪያ ሊያስገባ ነው። ከአሁን በኋላ በጦርነት ሞት የሚባል አይኖርም፤ የኢትዮጵያ ወታደር ከግብጽ ጋር ቢዋጋ ከመሀል አዲሳባ ሆኖ በኮምፒውተር ነው ጦርነት የሚያደርገው… ብዙ ብዙ አይነት ወሬዎችን ተቀብለው የሚያቀባብሉ። ባዶ ሶስቶች። የሚመለመሉት ከመንደር ቡና አንጫላጭ ወሬኛ እናቶች እስከ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ድረስ ባሉ “አደገኛ”ወሬኞችን በማካተት ነው። ወይንም ደግሞ ምንም ጉዳት የማያደርስ የዋህ ካለ ወሬው ለሱ እንዲደርስ ይደረጋል። እናም ወሬውን ከኋላ ያባርሩታል። ወሬው ጆሯችን ገብቶ እስኪያበቃ አይለቁትም ያባርሩታል።

 

እነኝህ ሰዎች ኢትዮጵያ በነበርኩ ሰአት አንድ ወሬ ማስወራት ጀምረው ነበር። አቶ መለስ ተደብቀውና ራሳቸውን ቀይረው ገበሬ መንደር በመግባት ሰዎችን ያነጋግራሉ የሚል። ድንቅ ወሬ ነበር። ሸጋ። ግን ግን አቶ መለስ በአደባባይ ሰው ስለሚገድሉ፣ ሰው እንዳሻቸው ስለሚያስሩ፣ ሀገርን በጎሳ ከፋፍለው ስለሚያስተዳድሩ ያ ገበሬ ሳያውቃቸው አስተናግዷቸው ይሆናል። ችግሩ ያለው አቶ መለስ ጭምብል አጥልቀው ገበሬ መሀል መግባታቸው ሳይሆን ራሳቸውን አቶ መለስን ሲሆኑ ነው። አቶ መለስ ራሳቸውን ደብቀው እንጂ ራሳቸውን ሆነው ህዝብ መሀል ቀርቶ ግለሰብ ዘንድ አይቀርቡም። ስራቸው ነዋ! ስራቸው ዋጋቸውን ሰጥታቸዋል ተከቦ መኖር። ምን እሳቸው ብቻ ልጆቻቸው ዘመዶቻቸውም ጭምር እንጂ…።

 

እንደ አቶ መለስ ያሉ አምባገነኖች ለራሳቸው እንጂ ለልጆቻቸው እንኳን ግድ የማይሰጣቸው ፍጥረቶች መሆናቸውን በአርባ አመቱ መንበር ጋላቢ ጋዳፊ አየን። ሳዳምንም ተመለከትን፣ ቢን አሊም ታዩ፣ የኛኑ መንግስቱንም ማየት መልካም ነው። በነገራችን ላይ በቅርቡ የኮሎኔል መንግስቱ ልጅ ትምህርት መንግስቱ መሰለችኝ እዚህ ውቧ መንደር ቫንኩቨር ነበረች። ማንንም ሳታይ ማንም ሳያያት በአባቷ ሀጢያት የኋልዮሽ እያየች ትኖራለች።… አምባገነኖች አሁን ባለ ደስታ የኋላ ኋላ ልጆቻቸውን ጭምር ያሳቅቃሉ። እየተሹለከለኩ በየት ልግባ በየት ልውጣ ሲሉ፣ የቅርቡን የኛኑ መንግስቱን አይቶ መማር ምን ያቅታል ጎበዝ፡፤ የመንግስቱ ልጆች በምንም አይነት መለኪያም ያጠፉት ቅንጣት ጥፋት የለም። በምንም አይነት መልኩ ቀናብለው መሄድ ግን  አይችሉም። ጥፋት ቢኖርባቸው እንኳን ከነፍሰ በላው አባታቸው መፈጠራቸው ብቻ ነው። ያለሀጢያታቸው አሁንም ወልደው ከብደው እንኳን ከመሽሎክሎክ አላመለጡም። የቢን አሊም… የጋዳፊም… የሙባረክም… ሁሉም አንድ ነው የሚገጥማቸው።

 

የአቶ መለስ ሴት ልጅ ያኔ ቅንጅት በህዝብ ድጋፍ አይሎ በነበረ ጊዜ ተስፋዋ ጨልሞባት ለአንድ መምህሯ “የአባየ ነገር አለቀለት”  ማለቷን ከመምህሯ ጓደኛ ሰምቼ ነበር። የመለስ ልጅ አድጋለች፣ ነፍስ አውቃለች፣ የአባቷን መጨረሻ ስታይ ምን ትል ይሆን? አሁንማ ለንደን አለላት፣ ዛሬማ ኦሀዮ የራሷ ነው። ሁሉ በእጇ የሆነላት ግንግን የራሷ የግሏ ያልሆነ ህይወት የምትኖር ፍጥረት።

 

ታዲያ የዚህች በአምባገነን የምትማቅቅ ሀገር ተስፋ በማን ላይ ነው? ሀገር ቤት ውስጥ የሚኖረው ህዝብ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ላይ ተስፋውን ጥሎ ወደ ላይኛው ማንጋጠጥ ይዟል። እኛ እዚህ የተደላደለ ኑሮ እያሳደድን የምንገኘው ዲያስፖራዎች ግን ነጋ ጠባ በማይረቡ ጉዳዮች ጭቅጭቅ ይዘናል። አቤት የንትርክ መአት፣ አቤት የስድድብ ብዛት…! አቤት አቤት የሚነሱ ሰንካላና የማይረቡ ንዝንዞች መአት።  እነኝህ ንዝንዞች ታዲያ ኦስሎ ወይም ለንደን እንዳሉት ሁሉ አለያም ታላቋ የሀበሻ መናገሻ ዋሽንግተን ዲሲ ወይ ቶሮንቶ እንዲያም ካለ አትላንታም ሆነ ሎስ አንጀለስ እንዳለው ሁሉ በተመሳሳዩ እዚህ ቫንኩቨርም አለ። ውቧ መንደር ቫንኩቨር። ሸጋዋ… ደጓ ምድር ቫንኩቨር።

ለንደን ሄደው ያዩት የአቢያተ ክርስቲያናት ንትርክ እዚህ አለ። ፖርት ላንድ… ሳንሆዜ… ሲያትል… ስዊድን.. ሳውዝ አፍሪካ ያያችሁት በወያኔው አባ ጳውሎስ ስር ወድቄ ካልሰገድኩ የሚል አርበኛ እዚህ ታገኛላችሁ… ቫንኩቨር

 

ውጭ ሀገር መኖር ትልቁ ጥቅም ነጻነት ነው። እዚህ ስንኖር በምርጫችን ነው። አባ ጳውሎስንም ሆነ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቀርዮስን ለመምረጥ መብቱ ያለን እዚህ በመኖራችን ብቻ ነው። እዚያ ነጻነት የለም እዚያ… ኢትዮጵያ ያለው ምርጫ አባ ጳውሎስ ወይም ስደት ገፋ ካለም ሞት ነው። እዚህ ግን እንደ ቫንኮቨሯ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ካልተሰረክና ካልተጭበረበርክ በስተቀር ነጻነት አለህ። የቫንኩቨሯ ማሪያም ታሪክ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ መነጋገሪያ ነበረች። በገለልተኛ ሽፋን በተሸሸጉ የአባ ጳውሎስ አሽከሮችና በአቡነ መርቀሪዮስ በሚመራው ሲኖዶስ ስር መተዳደር በሚፈልጉ ሰዎች መሀል ሰፊ ክርክር ነበር። የፈረንጅ ዳኛ ገላጋይ የገባበት። ማውራት የፈለኩት ስለቤተ ክርስቲያኗ ጣጣ አይደለም። የሱ ምእራፍ ተዘግቷል። ልናገር የፈለኩት ስለነዚያ ልጅ ተክሌ እንደሚላቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ በዚህም በዚያም ተጠቅመው የወጡ ይህንን አገዛዝ አጥብቀው ስለሚቃወሙና በነጻዋ ምድር ቫንኩቨር ላይ ድብብቆሽ ስለሚጫወቱት እንጂ።

 

እኛ ገለልተኞች ነን..  ለቅንጅትም ለህብረትም ቆመናል… ለኢትዮጵያም የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ እንደማይበጅ ጠንቅቀን አውቀናል። ያሉና ጥርት አድርገው ይሄንን አገዛዝ እንደሚቃወሙ ሲናገሩ የሰማችኋቸው ሰዎች በዚህ በነጻነት ሀገር… ቫንኩቨር… ቤተ ክርስቲያን ገብተው    ጸልዩ በእንተ ርዕሰ ጳጳሳት  አባ ጳውሎስ ሲባል አ…ሜ…ን… ሲሉ ይውላሉ። አባ ጳውሎስ አባቶችን አስደብድቧል፣ አባ ጳውሎስ ባህታዊያንን አስጨፍጭፏል ግማድ ጸጉራቸውን አስላጭቷል፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከተጠለሉበት አምስት ኪሎ ቅድስት ማሪያም ቤክርስቲያን አስጠፍሯል። ሲባል የሰማ የአዲስ አባ ሰው አክ እንትፍ ሲለው እኛ እዚህ ደጋጎቹ ሀገር ቁጭ ብለን እዚያ ላለው ህዝብ አጋዥነታችንን በትንሹ ማሳየት ካቃተን ምን ልንባል ነው። ስቅጥጥ የሚያደርግ ነው።

 

አንዱ ስሙን ቀይሮ በስልክ ሊያናግረኝ ቀጥሮኝ ብሄድ ስሙ ሌላ ወሬው ሌላ…. ገለልተኛ ነን!.... እኛ ቤተክርስቲያኗ ወደ አባ ጳውሎስ እንድትሄድ አንፈልግም…  በማለት ሲደሰኩርልኝ የነበረ ሰው ዛሬ ቤተክርስቲያኗ በጳውሎስ እጅ ወድቃ የቤተክርስቲያኗ አመራር ሆኖ ሲያየኝ ምን እንደሚሰማው አላውቅም። እኔ እሳቀቅለታለሁ። ቤተ ክርስቲያኗ ወደ አባ ጳውሎስ እያመራች ነው ሲባል… እኛ እያለን?… እንዴት ይደረጋል…? በኢንተርኔት ላይ ሲባል ነው የምሰማው እንጂ በፍጹም አይደረግም። ሲል የነበረ የማከብረው ትልቅ ሰው ዛሬ በጳውሎስ ስር ለመተዳደር ብቻ ሳይሆን የህወሀት ካድሬ መሆኑ የሚታማ ቄስ ተሹሞ ሲባርከው በምን አይነት ሞራል እንደሚቀበለው እግዜር ይወቅ። ቫንኩቨር ታዲያ ትችለዋለች ሁሉም አለ ሁሉም የለም። በቫንኩቨር። ልክ እንደ ኔዘርላንዱ ልክ እንደ ሲድኒው…

 

እናንተየ ይሄ በየ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ጉድ ጉድ የሚል ሰው ወይንም አንዴ ለሰበካ ጉባኤ የተመረጠ ሰው ስልጣን አልለቅም ብሎ የሙጥኝ የሚለው ለምን ይሆን?… እዚያ አካባቢ ምን አይነት ጥቅም እንዳለ አላውቅም። ግን ግን ብዙ የሚሸት ነገር አለ!… በገንዘብ የማይጠረጥረው ግልሰብ ቦታዋ ላይ ሲደርስ የሙጥኝ ይላል… የምታከብሩት ሰው በየደብሩ ሲገባ የስራ ዘመኑ ቢያልቅ እንኳ መልቀቅ አይሻም!... ምን ጉድ ነው እዛ ውስጥ ያለው?… ገንዘብ? አይመስለኝም… ስልጣን እንዳይባል ትርፉ እንዘፍ እንዘፍ ነው… የሰው መውደድ እንዳንለው… ሰው በቃ አዲስ ሰበካ ጉባኤ ይምጣ ሲል ትሰማላችሁ…. ሌላ ምን ይሆን?... ይሄንንም ቫንኩቨር ታያላችሁ ልክ እንደ ካልጋሪው ልክ እንደ ዳላሱ…

 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እልህ ታያላችሁ ቡድንም አለ… ጎጥም እንዲሁ… ቫንኩቨር ደጋግ ሰዎች አሉባት ከኔ ቢጤ ኮስማና እስከ ታታላቅ በግልና በቡድን እስከሚሮጡ ጎበዛዛት፤ ቤተክርስቲያንን በጽናት ለማቆም ከሚሮጡት ጀምሮ ለማፍረስና በቡድን በመቧደን እስከሚሽከረከሩ… እነዚያ የዋሆቹ ሀገር ቤት ያሉ አባቶችና ምእመናን ነጻ ያወጡኛል ብለው የሚተማመኑባቸውና የሚጸልዩላቸው እዚህ ውጭ ሀገር ያሉ የቤተክርስቲያን ሰዎች እዚህና እዚያ ሆነው እንደሚናቆሩ ቢያዩ ልባቸው ምን ያህል ያዝን።

 

በቫንኩቨር ታዲያ ፖለቲካም አለ። እንደሌሎቹ ሀገራት ሁሉ። እንደ ኖርዌይ እንደ ሲዊዘርላንድ እንደ ዊኒፕግ ሁሉ። ቫንኩቨርም ፖ…ለ….ቲ…ካ… አለ። በጽኑ ሞራልና ሰብእና ከተገነቡት እስከ ደፋርና እዩኝ እዩኝ ባዩ። ፖለቲካን ወኔ ብቻ ወንዝ አያሻግረውም። ብልህነት ይጠይቃል። የዲያስፖራው ፖለቲካ ችግሩ ወኔ አይደለም ባለ ወኔያሞችማ ሞልተውታል። ብልሀትና መከባባር ማጣት ጠፉ እንጂ… በቫንኩቨር ብልሀት የለም። ነፋሱ እንደነፈሰ ነው። መሮጥ… መሮጥ… ቀጥ ሲል ደግሞ ቀጥ ነው። ከእንደገና መሮጥ… ያው ወያኔ በየስድስት ወሩ እየነቀሰ ሚያስረውና የሚገለው ወይም የሚሰራው ትርኢት ሲኖር እዚህም ሩጫ ነው። በመሰረቱ ፖለቲካ በሜዳው ነው የሚያምረው። እዚያው። እዚህ ሲመጣ ስራችን ትንሽ ነው። ሁላችንም እንደምንስማማው ውጭ ሀገር የሚኖረው ህዝብ ሀገር ቤት ለሚደረግ ፖለቲካ  የገንዘብ ድጋፍ መስጠት ወይም እዚህ ያለንበት ሀገር ላሉ ዜጎችና መንግስታት የዚያን አረመኔ መለስ አገዛዝ ምንነት ማሳወቅ። ይህችን ትንሽ ስራ ለመስራት ንትርኩ ብዙ ነው። ሀገር ቤት ያሉትን ፖለቲከኞች ወያኔ ድራሻቸውን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም አንዴ በሀገር ክህደት ሌላ ጊዜ በዘር ማጥፋት፤ ሲለው ህገመንግስቱን ለመናድ ሲያሻው በአዲሱ ትኬት… ሽብርተኛ ወንጀል ድራሻቸውን እያጠፋ ነው። ለነገሩ እኛ ራሳችንም እዚህ ያለን ዜጎች ከመጠየቅ አንድንም።

አስከዚያኛው ቸር ለናንተ

የናንተው እኔ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ