የአንድነት ፓርቲ በቅርቡ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔው፣ ዶር ነጋሶ ጊዳዳን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። ይህን አስመልክቶ አጭር አስተያየት የሰጠው አፍቃሪ ኢሕአዴጉ አይጋ ፎረም፣ የቅንጅት ነገር እንዳበቃለት ይናገራል።

 

 

“With Gebru Asrat leading ARENA and Dr Negasso leading UDJ, MEDREK may finally shed its “tseguri hemeq” inherited from Kinjit! It will also mean EPRDF will have a formidable opposition that can talk the way it talks come next time! That is if (it is a big if) the two leaders choose to do so! Oh what a turn of events for Kinjit!” ሲል ነበር አይጋ ፎረም የቀለደው።

 

አይጋ «ቅንጅት» ሲል ስለማን መናገሩ እንደሆነ ብዙም የማውቀው ነገር የለኝም። ነገር ግን የአንድነት ፓርቲ፣ ዶር ነጋሶን በሊቀመንበርነት በመምረጡ ከቅንጅት የወረሳቸው እሴቶችን እንዳራገፈ አድርጎ ሊነግረን ይፈልጋል። የአንድነት ፓርቲም ኢሕአዴግን እየመሰለ እንደሆነም ለማሳየት ይከጅለዋል።

 

ስለቅንጅት በምንናገርበት ጊዜ ከሶስት አቅጣጫዎች አስተያየቶችን ልንሰጥ እንችላለን። በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና በማግኘቱ አንጻር ነገሮችን ካየናቸው፣ ያኔ የአራት ድርጅቶች ስብስብ የነበረው፣ በምርጫ ተወዳድሮ ታሪካዊ ውጤት ያስመዘገበው ቅንጅት የለም ማለት ይቻላል። ኢሕአዴግ የቀድሞ የቅንጅት አመራር አባላትን አስሮ፣ ቅንጅት የሚለውን ስም በገንዘብ ለገዛቸው ሎሌዎቹ፣ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ሰጥቶ፣ በአሁኑ ወቅት “ቅንጅት” በሚል ድርጅት ስር፣ ሕዝብ ተሰባስቦ እንዳይንቀሳቀስ አድርጓል። አሁን በምርጫ ቦርድ «ቅንጅት» ተብሎ የሚታወቀው በተግባር የኢሕአዴግ ሌላው ክፍል የሆነውና በአቶ መለስ የሚታዘዘው የአየለ ጫሚሶ ቡድን ነው።

 

«ቅንጅት» ማለት የቅንጅት መሪዎች ማለት እንደሆነ አድርጎ የመውሰድ ሁኔታም ሊኖር ይችላል። «ቅንጅት» ማለት በርግጥ የቅንጅት መሪዎች ማለት ከሆነ፣ በእርግጥ «ቅንጅት» ሞቷል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያኔ አንጋፋ የቅንጅት መሪ የነበሩ የት እንዳሉ ልጥቀስ፡

 

1. ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል (የቅንጅት ሊቀመንበር)፦ ከቃሊቲ እሥር ቤት መፈታት በኋላ፣ በቅንጅት ውስጥ ለተፈጠረው ከፍተኛ የመበጣበጥ ምክንያት በመሆን ትግሉን ክፉኛ የጎዱ ሰው ናቸው። በቅንጅት ውስጥ ያደረጉት ስህተቶች ሳያንሳቸው አሁን ደግሞ በመኢአድ ውስጥ ችግርና ውዝግብ እየፈጠሩ ነው። ሰማኒያ አመት ሊሞላቸው እንደሚችል አስባለሁ። ጡረታ ወጥተው፣ ፖለቲካውን ለወጣቶች አሳልፈው ለምን እንደማይቀመጡ አይገባኝም።

 

2. ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ (የቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር)፦ ለሁለት ጊዜ ወደ ቃሊቲ ከወረደች በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት በዋሺንግተን ዲሲ የከፍተኛ ትምህርት እየተከታተለች ናት። በመሆኑ ለጊዜው በፖለቲካው ትግል ውስጥ እምብዛም እየተንቀሳቀስች አይደለም።

 

3. አቶ ልደቱ አያሌው (የቅንጅት ምክትል ሊቀመንበር)፦ ቅንጅቱ ብዙ ገፍቶ ሳይሄድ ከቅንጅት በመውጣት፣ ሶስተኛ መንገድ በሚል ኢዴፓ የተሰኘውን ድርጅት እየመራ ሲታገል ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት እርሱም ለከፍተኛ የትምህርት እድል በለንደን ይገኛል።

 

4. አቶ ሙሉነህ እዮዔል (የቅንጅት ዋና ጸሃፊ)፦ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቆ፣ ነዋሪነቱን በአሜሪካን አድርጎ፣ ግንቦት ሰባት ተብሎ በሚታወቀው ድርጅት ውስጥ እየተንቀሳቀስኩኝ ነው ይላል።

 

5. ዶር ብርሃኑ ነጋ (የአዲስ አበባ ከተማ ተመራጭ ከንቲባ)፦ የሰላማዊ ትግል አይሰራም በሚል፣ ግንቦት ሰባት የተሰኘን ድርጅት መስርተው እርሳቸውም እንቀሳቀሳለሁ እያሉ ነው። ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ አድርገው በዩኒቨርሲቲ መምህረነትም ያገለግላሉ።

 

6. ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም (የቅንጅት አባት ይባሉ የነበረ)፣ ዶር ያቆብ ኃይለ ማሪያም (የቅንጅት የውጭ ግንኙነት ሃላፊ)፣ ዶር በፈቃዱ ደግፌ (የቅንጅት የፋይናንስ ሃላፊ)፣ እንዲሁም በርካቶች መጻሕፍት ከመጻፍ፣ አንዳንድ ጽሁፎችን በጋዜጦችና በድረ ገጾች ከማቅረብ ውጭ ከፖለቲካው ወጥተዋል ማለት ይቻላል።

 

እንግዲህ ያኔ የቅንጅት አመራር የነበሩ ወገኖች፣ አሁን የት እንዳሉ በምናይበት ጊዜ፣ በርግጥ ቅንጅት ማለት መሪዎቹ ማለት ከሆነ፣ ቅንጅት የለም፣ ቅንጅት ሞቷል ወይንም ቅንጅት ተሰዷል ማለት ይቻላል።

 

ነገር ግን ቅንጅት ማለት በምርጫ ቦርድ እውቅና ማግኘት፣ ወይንም ግለሰቦች ማለት አደደለም። ቅንጅትን ያኔ ቅንጅት ያስኘው በምርጫ ቦርድ መታወቁ ወይንም የሚመሩት ግለሰቦች ሳይሆን፣ ይዞ የተነሳው አጀንዳዎቹ ነበሩ። ቅንጅት ሕዝቡ ለኢትዮጵያዊነቱ፣ ለአንድነቱ፣ ለነጻነቱ፣ ለክብሩ የሚያደርገውን ትግል የሚያመላክት ንቅናቄ ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያኔ እንዳለቸው ቅንጅት መንፈስ ነው።

 

ለዚህም ነው፣ እነ አቶ ኃይሉ ሻውል የሕዝብን ሃላፊነት ሲጥሉ፣ እነ ዶር ብርሃኑ ነጋ ስደትን ሲመርጡ፣ ገዢው ፓርቲ በሚቆጣጠረው ምርጫ ቦርድ የቅንጅትን ስም ለአያለ ጫሚሶ ቡድን ሲሰጥ፣ ያኔ በቅንጅት ስም ሲደረግ የነበረው የኢትዮጵያዊነትና የዲሞክራሲ ትግል፣ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሥር የቀጠለው። የሕዝብ የዲሞክራሲ ጥማት መቼም ሊሞት አይችልም። የሕዝብ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መቼም ቢሆን ሊታፈን አይችልም። ቅንጅት ማለት ይሄ ነው።

 

ዶር ነጋሶ ጊዳዳ የቅንጅት ወራሽ የሆነውን የአንድነት ፓርቲን ለመምራት ሲመረጡ፣ እርሳቸው የኢሕአዴግን ፖለቲካዎች አልፈልግም ብለው፣ አንድነት ወደ ሚያራምደው የ«ቅንጅት» ፖለቲካ በመምጣታቸው ነው። ዶር ነጋሶ የአንድነት መሪ ሲሆኑ፣ የአንድነት ፓርቲን (ማለት የቀድሞ የቅንጅት) መርህዎችና እሴቶችን በመቀበላቸው ነው። ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ ካስቀመጣቸው ራእዮቹ መካከል የተወሰኑትን ልጥቀስ፦

 

• የአንድነት ፓርቲ አሁን ያለውን በዘር ላይ የተመሰረተ ከፋፋይና ጎጂ የፌደራል አወቃቀር ይቃወማል። የድርጅቱን የፖለቲካ ፕሮግራምና ራእይ ባቀፈው ሰነድ በ4.1.3 .ሀ «የፌደራል አወቃቀሩ እንደ ሁኔታው መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ አስተዳዳራዊና የልማት አመችነትን፣ ቋንቋን ባህልን፣ ታሪክንና ሌሎች ማህበራዊ ትሥሮችን መሰረት ያደረገ ይሆናል” የሚል እናነባለን። ፍጹም በዘር ላይ ብቻ ካታኮረው፣ ከፋፋይና ጎጂ ከሆነው፣ አሁን ካለው ከሕወሃት ፌዴራል አወቃቀር የተለየ የፌደራል አወቃቅር ነው ።

 

• አንቀጽ 4.3 ሀ «ለመንግስት አገልግሎት የሚውል ካልሆነ በቀር ማንኛውም የገጠር መሬትና የከተማ ቦታ የኢትዮጵያውያን የግል ሃብት ይሆናል” ሲል አንድነት ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሚያራምደው መሬት የመንግስት ነው ከሚለው ፖለቲካ የተለየ ፖለቲካ ነው።

 

• ሕወሃት/ኢሕአዴግ ኤርትራን ያስገነጠለ፣ ኢትዮጵያን የባህር አልባ አድርጎ ለጅቡቲ ቱጃሮች አገራችንን ጥገኛና ባሪያ ያደረገ ነው። እስከአሁን ድረስ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ፖሊሲ አሰብ የኢትዮጵያ እንዳልሆነች ነው። የአንድነት ፓርቲ በፕሮግራሙ ስለ ወደብ ሲያትት ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት መሆን እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጣል። «ከኢትዮጵያ አብይ የውጭ ጉዳዮች በቀዳሚነት የሚታየው የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሰላማዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲረጋገጥ ጽኑ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ይደረጋል” ይላል አንቀጽ፡4.7.መ።

 

እንግዲህ ይህን አይነት ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ የሚንቀሳቀስ ድርጅትን፣ ኢሕአዴግን እንደመሰለ አድርጎ አይጋ ፎረም ሲጽፍ፣ መሳቂያ ከመሆን በስተቀር ብዙ የሚቀይረው አተሳሰብ ይኖራል ብዬ አላስብም።

 

«ቅንጅት» አልሞተም። የቅንጅት መንፈስ አልጠፋም። የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱንና ነጻነቱን፣ ክብሩንና አንድነቱን ለማረጋገጥ፣ የተሸከመውን የግፍ አገዛዝና የመከራ ቀንበር ከአናቱ ላይ ለማራገፍ፣ ከመቼውም በበለጠ የቆረጠበትና የተዘጋጀበት ጊዜ ነው።

 

ሕወሃት/ኢሕአዴግ፣ ጦር ሃይሉን፣ የደህንነት ክፍሉን፣ ሜዲያውንና ኢኮኖሚውን በመቆጣጠሩ የገጸፈና ለዘላለም የሚኖር፣ በሌላ አባባል ያሸነፈ አድርገው እነ አይጋ ፎረም ሊጽፉ ይችላሉ። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየን ያለነው የሕወሃት/ኢሕአዴግ የከሰረ የዘር ፖለቲካ ተቀባያነቱ እየወደቀ ሲሄድ፣ በቅንጅት ጎልቶ የወጣው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የበለጠ እያበበና ኢትዮጵያውያን በዘር አንከፋፈልም ብለው በአንድነት ሲሰባባሱ ነው። በዜጎች ዘንድ ያለውን የአስተሳሰብ ትግል፣ የዜጎችን ልብ የመማረክ ትግል ካየን፣ እያሽነፈ ያለው የኋላ ቀሩ የሕወሃት/ኢሕአዴግ የዘር ፖለቲካ ሳይሆን የ«ቅንጅት» የኢትዮያዊነት ፖለቲካ ነው!

 

«ቅንጅት» ሞቷል እያሉ፣ ሕዝብ ይዞት በተነሳው መሰረታዊ የዲሞክራሲና የአንድነቱ ጥያቄ ላይ ከማሾፍ፣ ልቦና ገዝቶ ከወዲሁ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ በአስቸኳይ መስጠቱ ይበጃል።

 


ግርማ ካሣ

 

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ